ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የጸሎፍትሃት ሥነ ሥርዓት ሲመሩ፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የጸሎፍትሃት ሥነ ሥርዓት ሲመሩ፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪን ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዓርብ ጠዋት ሐምሌ 10/2012 ዓ. ም. ያረፉትን ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪን በማስታወስ የሐዘን መግለጫ መልዕክት አስተላለፉ። ለብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ወንድም፣ ለክቡር አቶ ቭላዲስሎው በላኩት የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተው በሐዘን ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በትውልድ ፖላንዳዊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ በቤተክርስቲያን በገለገሉባቸው ዓመታት ከቀድሞ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ጋር በቅርበት የሠሩ መሆናቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ካቶሊካዊ ትምህርት አስተባባሪ ጽሕፈትን በመምራት ያገለገሉ መሆናቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ፤
ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ፤

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቴሌግራም መልዕክታቸው፣ ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ በሮም በሚገኙ ሁለት ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ዩኒቨርሲቲ የሕገ ቀኖና መምህር ሆነው ማስተማራቸውን አስታውሰው፣ ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ ቅድስት መንበርን በየዋህነት እና በቸርነት ያገለገሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ በቅድሚያ በቅድስት መንበር የሐዋርያዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ አለቃ በመሆን፣ ቀጥለውም በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ካቶሊካዊ ትምህርት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት መሪ ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ ካርዲናል ዜኖን በተመደቡባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ለክኅነታዊ ጥሪ ምስክርነት የሰጡ፣ ለወንጌል ያላቸውን ታማኝነት በመግለጽ ቤተክርስቲያንን ለማሳደግ በትጋት የሠሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

“ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በማቀርበው ጸሎቴ፣ ለሐዋርያቱ የገባላቸውን ዘለዓለማዊ በረከት እንዲያወርሳቸው እና በሐዘን ውስጥ ለሚገኙትም መጽናናን እመኝላቸዋለሁ” በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል። ለብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ የሚደረግ የጸሎተ ፍትሃት ሥነ ሥርዓት፣ በቅድስት መንበር የካርዲናሎች መማክርት ምክትል አለቃ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ሐምሌ 11/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መፈጸሙ ታውቋል። በጸሎቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተው የስንብት ጸሎት ሥነ ሥርዓት መምራታቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 11/1939 ዓ. ም. በፖላንድ አገር ብሮድኪ ከተማ ተወልደው፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በግንቦት 27/1963 ዓ. ም. የምስጢረ ክህነት ጸጋ መቀበላቸውን ከፖላንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤው ከተላከ የሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል። ቀጥለውም በአገራቸው በሚገኝ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ቆሞስ ሆነው ካገለገሉ በኋላ ወደ ሮም ተልከው በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ተከታትለው የዶክተርነት ማዕረግ መቀበላቸው ታውቋል። 

ብጹዕ ካርዲናል ዜኖን ግሮከለስኪ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1972 ዓ. ም. እስከ 1999 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ አለቃ ሆነው በሠሩባቸው ዓመታት፣ ከምክር ቤቱ ሰባት አባላት ጋር በመሆን እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1983 ዓ. ም. የቀረበውን የቤተክርስቲያኒቱን ሕገ ቀኖና አንቀጾችን ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር በመሆን በዝርዝር መመልከታቸው ታውቋል። ቀጥለውም በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት የካቶሊካዊ ትምህርት አስተባባሪ ጽሕፈት መሪ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል። በኋላም በሮም በሚገኙ ሁለት ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ዩኒቨርሲቲ የሕገ ቀኖና መምህር ሆነው ማስተማራቸው ሲታወስ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በሮም የሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ቻንስሌር ሆነው ማገልገላቸውን ከሕይወት ታሪካቸው ለማወቅ ተችሏል።                      

18 July 2020, 19:26