ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ያደርገው ትግል የጸሎት ተምሳሌት ነው” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደምያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ እና ስድስተኛ ክፍል የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በዚሁ “የክርስቲያን ጸሎት” በሚል አርዕስት ቅዱስነታቸው በተከታታይ በማደረግ ላይ በሚገኙት የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ያደርገው ትግል የጸሎት ተምሳሌት ነው” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በዕለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ

ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብ ግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። በዚያን ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለ ሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ ልለቅህም” አለው። ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ።ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም፣ ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው። ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። ሰውዬውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው። ስለዚህ ያዕቆብ፣እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው (ዘፍጥረት 32፡25-30።

 

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አደራችሁ!

በጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬም እንቀጥላለን። የዘፍጥረት መጽሐፍ ከብዙ ዘመናት በፊት የነበሩ ሰዎች የፈጸሙትን ክስተቶች በመግለጽ በእኛ ሕይወት ውስጥ ማንፀባረቅ የምንችልባቸውን ታሪኮችን ይነግረናል። በተከታታይ በነበሩ አባቶች ታሪክ ውስጥ እንዲሁ ብልሃት እና የላቀ ችሎታ ያዳበረውን ያዕቆብ የሚባለውን ሰው እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው ጋር ስለነበረው አስቸጋሪ ግንኙነት ይነግረናል። ከልጅነት ጊዜ ጀምሮ በመካከላቸው ፉክክር ነበረ፣ እናም እስከመጨረሻው የተፈታ ጉዳይ አልነበረም። ያዕቆብ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን ነገር ግን የአባታቸውን የይስሐቅን በረከትና ብኩርና ለማግኘት ተንኮል ተጠቅሟል (ዘፍ 25፡19-34)። ይህ ተንኮለኛ ሰው ሊሠራባቸው ከሚችላቸው ረዥም ተከታታይ ዘዴዎች ውስጥ የመጀመሪያው ነው።

ከወንድሙ ርቆ ለመሸሽ ስለተገደደ በህይወቱ ሁሉ ስኬታማነት ያለው ይመስላል። እሱ በንግድ ችሎታ የተካነ ነው፣ እጅግ የበዛ መንጋ ባለቤት በመሆን ራሱን እጅግ ያበለፀገ ሰው ሆነ። በርህራሄ እና በትዕግስት እሱ በእውነት እጅግ በጣም በፍቅር የወደዳትን ርብቃን ማግባት ችሎ ነበር። ያዕቆብ - በዘመናችን እንደምንለው “ራሱን የሰራ” ሰው ዓይነት ነበር። በብልሃቱ የሚፈልገውን ሁሉ ለማግኘት ችሏል።

ከዕለታት አንድ ቀን እሱ ሁልጊዜ መጥፎ ግንኙነት የነበረው ወንድም ዔሳው ከሚኖርበት የትውልድ አገር የቀረበ አንድ ጥሪ ሰማ። ያዕቆብ የትውልድ አገሩ ውስጥ በምትገኘው የበቦቅ ወንዝ አተጠገብ እስኪደርስ ድረስ ከብዙ ሰዎች እና እንስሳት ጋር ረዥም ጉዞን ያካሂዳል። እዚህ ጋር የዘፍጥረት መጽሐፍ የማይረሳ ትዝታ ይሰጠናል (ዘፍጥረት 32: 23-33)። አባታችን የሆነው ያዕቆብ ሕዝቡን ሁሉ እና እንስሳትን በሙሉ ይዞ ጅረቱን ከተሻገረ በኋላ ብቻውን በባዕድ አገር ላይ እንደሚቆይ ያብራራል። እናም ያሰላስላል: በሚቀጥለው ቀን ምን ይጠብቀዋል? ወንድሙ ዔሳው ምን ዓይነት አመለካከት ይኖረዋል? የያዕቆብ አእምሮ ዐውሎ ነፋስ በሚመስሉ ሐሳቦች ይሞላል። እናም እየጨለመ ሲመጣ ድንገት አንድ እንግዳ ሰው ይይዘውና ከእርሱ ጋር መታገል ይጀምራል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ይህንን በተመለከተ ሲያብራራ “የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ወግ የእምነት ተጋድሎና የጽናት አሸናፊነትን የጸሎት ተምሳሌት አድርጎ ወስዷል” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቁ. 2573) በማለት ይናገራል።

ያዕቆብ ተቀናቃኙን በጭራሽ አለቅም ብሎ ሌሊቱን በሙሉ ሲታገል አደረ። በመጨረሻም የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብ ግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። ከዚያ በኋላ እስከ ቀሪው የሕይወት ዘመኑ ድረስ እያነከሰ ነበር የሚራመደው። በዚህ ምስጢራዊ ትግል ከእርሱ ጋር ሲታገል የነበረው ሰው ስሙን ከጠየቀው በኋላ “ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው (ዘፍጥረት 32፡28)። ከዚያም ያዕቆብ ከእርሱ ጋር ሲታገል የነበረውን ደግሞ “ስምህን ንገረኝ” በማለት ይጠይቀዋል። ሌላኛው ግን ስሙን አልነገረውም፣ ይልቁንም ይባርከዋል። ያዕቆብም እግዚአብሔርን “ፊት ለፊት” እንደተገናኘ ተረዳ (ዘፍጥረት 32፡29-30)።

ከእግዚአብሔር ጋር መታገል- የጸሎት ተምሳሌት ነው። በሌሎች ጊዜያት ያዕቆብ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር መቻሉን፣ ጓደኛው እና የቅርብ ወዳጁ አድርጎ መመልከቱን አሳይቷል። ነገር ግን ያን ምሽት ለጉዳት በዳረገው ረዥም የሆነ ትግል ያዕቆብ ከዚህ ቀደም የነበረውን ግንኙነት ሲቀየር እናያለን። ቀድሞ እንደ ነበረው ዓይነት አሁን የሁኔታው ጌታ እርሱ አይደለም፣ እሱ ከእንግዲህ ወዲህ ስልታዊ እና ስሌታዊ ሰው አይደለም። የሚንቀጠቀጥና የሚፈራ ሟች የሆነ ሰው እንዲሆን በማድረግ እግዚአብሔር ወደ እውነታው ይመልሰዋል። አሁን ያዕቆብ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ድክመቱንና በደሉን ብቻ ነበር። ተስፋ የቆረጠው እና እያነከሰ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚሄድ በአዲሱ ልብ የእግዚአብሔርን በረከት የተቀበለው ይህ ያዕቆብ ነው። በመጀመሪያ እሱ እራሱን የሚያምን ሰው ነበር። በራሱ ብልህነት ታምኗል። እርሱ ለችግር የማይበገር እና ምህረት የማያደርግ ሰው ነበር፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የጠፋውን አዳን።

ሁላችንም በሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ቀጠሮ አለን። እኛ ባልጠበቅንበት ጊዜ ያስደንቀናል ፣ እራሳችንን በእውነት ብቻችንን እንደ ሆንን አድርገን እናገኘዋለን። በዚያኑ ምሽት ካልታወቀ ሰው ጋር በምናደርገው ትግል እኛ ሚስኪን የሆንን ሰዎች መሆናችንን እንገነዘባለን። ነገር ግን ፣ በዚያ ቅጽበት በትክክል መፍራት የለብንም ምክንያቱም እግዚአብሔር የመላውን ሕይወታችንን ትርጉም የያዘ አዲስ ስም ይሰጠናልና። እርሱም በእርሱ እንዲለውጣቸው ለሚፈቅዱለት ሰዎች የሚሰጥ ታላቅ በረከት ይሆናል። ይህ ለእኛ አምላክ እንዲለወጠን የሚያደርግ አስደሳች ግብዣ ነው። እርሱ እንዴት ማድረግ እንዳለበት ያውቃል ፣ ምክንያቱም እያንዳንዳችንን ያውቃልና። “ጌታ ሆይ ፣ ታውቀኛለህ፣ ለውጠኝ” ልንለው ይገባል።

10 June 2020, 11:49