ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለባሕር ላይ ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቀረቡ።
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሰኔ 10/2012 ዓ. ም. ባሕር ሐይሎችን፣ ዓሣ አጥማጆችን እና የማመላለሽ አገልግሎት ሠራተኞች እና በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ተሰማርተው ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር አስታውሰው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት፣ በተለይም ዓሣ አጥማጆችን አመስግነዋቸዋል።
የቫቲካን ዜና፤
ቅዱስነታቸው ለባሕር ላይ ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ጽሕፈት ቤት በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የባሕር ላይ ሠራተኞችን በርካታ ችግሮች ያጋጠማቸው መሆኑን ገልጸው፣ በአስቸጋሪው ወቅት ሕዝብን ለመመገብ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በማከልም የባሕር ኃይል መከላከያ እና ዓሣ አጥማጆች የአገርን ደህንነት በመጠበቅ እና ዕለታዊ ምግብን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማቅረብ ከፍተኛ አገልግሎት የሚያበረክቱ መሆን አስታውሰዋል።
የባሕር ላይ እንቅስቃሴ መቆም፣
በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የባሕር ላይ ሠራተኞች መስዋዕት እንዲከፍሉ በማድረግ፣ በአገልግሎታቸውም ለውጦችን እንዳስከተለባቸው መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ለረጅም ጊዜ ያህል መርከቦች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ መደረጋቸው፣ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች እና የልዩ ልዩ አገር ዜጎች ለወራት ያህል ተለያይተው እንዲቆዩ መገደዳቸው በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን የፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ድርጅት እንዳስታወቀው፣ ባሁኑ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ቁጥራቸው ከ150,000 እስከ 200,000 የሚደርሱ የባሕር ላይ መንገደኞች ወደ ፈለጉበት ሥፍራ እንዳይደርሱ ታግደው የሚገኙ መሆኑን አስታውቋል። ሪፖርቱ በማከልም ከባሕር ላይ ተጓዦቹ መካከል አብዛኛዎቹ የጉዞ ገደባቸውን እና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የፈጸሙ ቢሆንም ከመርከብ እንዳይወርዱ ታግደዋል ብሏል። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ድካም እና የጤና መቃወስ የደረሰባቸው መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል።
የባሕር ላይ መንገደኞች አልተረሱም፣
በችግሮች ውስጥ የሚገኙትን የባሕር ላይ መንገደኞችን በመልዕክታቸው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መንገደኞቹ ብቻቸውን እንዳልሆኑ እና እንዳልተዘነጉ ገልጸው፣ በረጅም ጉዞ ምክንያት ለብዙ ጊዜ ከቤተሰብ ተለይተው ቢገኙም በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በመካከላቸው በሚገኙ የባሕር ላይ ሐዋርያዊ አገልግሎት በኩል በጸሎት ዘወትር የሚታወሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ዓሣ አጥማጆች መሆናቸውን በመገንዘብ መጽናናት ያስፈልጋል ብለዋል።
የእመቤታችን ማርያም ጥበቃ ዘውትር አለ፣
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለባሕር ላይ ሠራተኞች እና ተጓዦች ተስፋን፣ መጽናናትን እና ብርታትን በጸሎታቸው ተመኝተው፣ በመካከላቸው ሐዋርያዊ እንክብካቤን እና መንፈሳዊ ድጋፍ በማበርከት ላይ ለሚገኙትም ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። ባሕር ላይ ለሚገኙት በሙሉ ሥራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እግዚአብሔር እንዲባርክ በጸሎት ጠይቀው፣ የባሕር ኮኮብ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር እንድትጠብቃቸው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
“ስቴላ ማሪስ”
“ስቴላ ማሪስ” የተባለ ሐዋርያዊ ድርጅት ለባሕር ላይ መንገደኞች፣ ባሕር ኃይል ሠራዊት፣ ዓሣ አጥማጆች እና በተለያዩ አገልግሎቶች ለተሰማሩት በሙሉ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በስኮትላንድ፣ ግላስጎው የተመሠረተው ይህ ድርጅት በዓለም ዙሪያ በባሕር ላይ እና በወደቦች አካባቢ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በማቅረብ ላይ የሚገኝ ካቶሊካዊ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ ባሁኑ ጊዜ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ 216 ካህናት እንዳሉት የሚታወቅ ሲሆን፣ ከ30 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በ311 ወደቦች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑ ታውቋል።