ፈልግ

ስሪላንካ. . . ስሪላንካ. . . 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታመመ ዓለም ውስጥ እየኖርን ጤናማ ነን ማለት አንችልም አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ ግንቦት 28/2012 ዓ. ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን ምክንያት በማድረግ፣ ለኮሎምቢያው ፕሬዚደንት አቶ ኢቫን ዱኬ ማርኬዝ መልዕክት መላካቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት ሥነ-ምህዳር እየወደመ በዝምታ መመልከት የለብንም ብለው፣ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከጥፋት መከላከል እና አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ የጋራ ሃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል። የዘንድሮን ዓለም አቀፍ የአከባቢ ቀን ክብረ በዓል እንድታስተናግድ የታጨችው፣ የላቲን አሜሪካ አገር ኮሎምቢያ ብትሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓሉ በሃሳብ ደረጃ ተከብሮ እንዲውል መደረጉ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን በሚከበርበት ወቅት በሩስያ፣ ሳይቤሪያ ግዛት ውስጥ የተከሰተው የአካባቢ አደጋ፣ የር. ሊ. ጳ. ፍራንሲችስኮስን መልዕክት የበለጠ ጠንካራ ያደረገው መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኮሎምቢያው ፕሬዚደንት አቶ ኢቫን ዱኬ ማርኬዝ የላኩት መልዕክት፣ በአካባቢ ላይ ለሚደርስ ጉዳት እና ውድመት አስፈላጊው የመከላከል ሥራ በፍጥነት እንዲሠራ የሚያሳስብ ነው ተብሏል። “በእናት ምድራችን ላይ የደረሰው ከባድ አደጋ እኛንም ክፉኛ አቁስሎናል” በማለት ገልጸዋል። ለሥነ-ምህዳር የሚደረግ እንክብካቤ ፈጣን ትርፍን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማካበት ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን፣ የረጅም ጊዜ ውጤትን ያገናዘበ እና በርካታ ሕይወትን ከጥፋት ተከላክሎ በማቆየት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ተፈጥሮ ሲበዘበዝ ፈጽሞ ዝም ማለት የለብንም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኮሎምቢያው ፕሬዚደንት የላኩት የሦስት ገጽ መልዕክታቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በማለት ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ ካደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የመነጨ መሆኑ ሲታወቅ፣ ይህ መልዕክታቸው ዛሬም ቢሆን እንደ አዲስ የሚጠቀስ መሆኑ ታውቋል። የአካባቢ ጥበቃ እና የፕላኔታችን ብዝሀ-ሕይወትን ማክበር የሁላችንን ሃላፊነት የሚሻ ወቅታዊ ርዕሠ ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በታመመ ዓለም ውስጥ እየኖርን ጤናሞች ነን ብለን ራስን ማታለል አንችልም ብለው በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ለሚደርስ አደጋ እያንዳንዳችን ተጠያቂ ሊንሆን ይገባል በማለት በአጽንዖት አሳስበዋል። በምድራችን ላይ ለሚደርስ ጥፋት እና በውስጧ በሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ የሚፈጸም ብዝበዛ ወደ ፊት እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋን እንደሚያስከፍለን እያወቅን በዝምታ መቀመጥ የለብንም ብለዋል። ለእድገት እና ብልጽግና በሚል ሰበብ ምድራችን ስትመዘበር እያየን በግድ የለሽነት የምንመለከትበት ወቅት ላይ አይደለንም ብለዋል።

ቆራጥ ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፣

ዘንድሮ ተክብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በየአካባቢያችን እንድናከብር ተገድደናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጋራ የምንኖርባት ምድራችንን ከውድመት በማዳን ለመጭው ትውልድ ምቹ ሆና እንድትገኝ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው ይህን ማድረግ የምንችለው ቅን ልብ እና ፍላጎት ሲኖረን ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል። ለጋራ ምድራችን አስፈላጊውን እንክብካቤን ማድረግ እንድንችል “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦን እና ምክሮችን እንደሚሰጥ ያስታወቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን ከምንሰጠው እንክብካቤ እና ጥበቃ በተጨማሪ በማኅበረሰቡ መካከል ተረስተው እና ተገልለው የቀሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እርዳታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ፣ በሥነ-ምህዳር ጥበቃ እና እንክብካቤ ተግባር ላይ ለሚሳተፉት በሙሉ ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክታቸው፣ ጥረታቸው ሁል ጊዜ ለሕይወት ምቹ የሆነች ዓለምን ለመገንባት እና ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚመለከት ሰብአዊ ማህበረሰብን መገንባት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

06 June 2020, 16:32