ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ስኮላስ ኦከሬንት ለተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መልዕክት አስተላለፉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስኮላስ ኦኩሬንት የተሰኘ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን፣ በድረ ገጽ የቪዲዮ መገናኛ በኩል ያዘጋጀውን ስብሰባ ለተካፈሉት አባላት የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ዓርብ ግንቦት 28/2012 ዓ. ም. ይፋ በሆነው የቪዲዮ መልዕክት ቅዱስነታቸው፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሆነው በድረ ገጽ የቪዲዮ መገናኛ በኩል ስብሰባውን ለተካፈሉ ወጣቶች፣ ቤተሰቦች እና መምህራን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው ስኮላስ ኦከሬንት የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ለሚገኙ ወጣቶች የሕይወት ትርጉም ለይተው እንዲውቁ መንገድ በማሳየት እንዲረዳቸው አደራ ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

“ከረጅም ዓመታት ጥረት በኋላ ዛሬ የጓደኛሞች፣ የወንድሞች እና የእህቶች ማኅበር ተብለን ለመጠራት መብቃታችን ከፍተኛ ደስታን የሚሰጥ ነው” በማለት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። “ስኮላስ” የተሰኘ ፋውንዴሽን በችግር ጊዜ በሁለት መምህራን አማካይነት ሳይታሰብ የተጀመረ ማኅበር መሆኑን አስታውሰው፣ በወቅቱ የነበረው ማኅበራዊ ቀውስ አመጽን አስከትሎ ያለፈ ቢሆንም፣ በትምህርት አማካይነት ሰዎች የአንድነትን እና የመረዳዳት ትርጉምን እና ውበትን ለማወቅ መቻላቸውን አስታውሰዋል።

ማኅበራዊ ቀውስ እና ውበቱ፣

የስኮላስ ፋውንዴሽን ሃሳብ እና ገጠመኝ ሦስት ምስሎች በአእምሮአችን እንዲቀረጹ አድርጓል ያሉት ቅዱስነታቸው እነርሱም “ጎዳና” በተሰኘ የፌሊኒ ድርሰት ላይ የተጠቀሰው “ሞኝ” ሰው፣ የ “ቅዱስ ማቴዎስ ጥሪ” የሚል ርዕሥ የተሰጠው የካራቫጆ የቅብ ስዕል እና “ሞኙ” የተሰኘ ሩሲያዊ ደራሲ የዶስቶቭስኪ ልብ ወለድ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ማኅበራዊ ቀውሶች የተገለጹባቸው እነዚህ ሦስቱ ታሪኮች፣ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሃላፊነት አደጋ ላይ መውደቁን የሚገልጹ ናቸው ብለው፣ ማኅበራዊ ቀውሶችን በአግባቡ ተከታትለው መፍትሄ ካልፈለጉላቸው የሰው ልጅ የሚሄድበት አቅጣጭ ሊጠፋበት እንደሚችል አስረድተዋል። በመሆኑም ሰዎች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ወደ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ብቻቸውን መግባት የለባቸውም ብለዋል።

ማኅበራዊ ቀውስ ሲያጋጥም ፍርሃት ይይዘናል፣ በዚህም የተነሳ ራስን መደበቅ፣ የሕይወት ትርጉም ማጣት፣ የተጠሩበትን ዓላማ መዘንጋት እና የነገሮችን ውበት የመመልከት ችሎታ ማጣት ሊያጋጥም ይችላል ብለው፣ የሩሲያዊው ደራሲ፣ ዶስቶቭስኪ ልብ ወለድ በመጥቀስ፣ ውበት ዓለምን ሊያድን ይችላል ብለዋል። “ስኮላስ” ፋውንዴሽን በችግር ወቅት መመስረቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ቢሆንም ባሕል ሳይንቅ እና ሳይቃወም፣ በተለይም የወጣቶችን የልብ ትርታ በማዳመጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል። 

ትምህርትን ማዳረስ፣

ትምህርት ስለ አንድ ነገር ማወቅ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ትምህርት ማለት ሌሎችን ማድመጥ፣ ባሕልን መፍጠር እና በባሕል መኖር ማለት ነው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በትምህርት ማድመጥ፣ ባሕልን መፍጠር እና በባሕል መኖር ከሌለ ትምህርት ሊያስተምር አይቻልም ብለዋል። ትምህርት የሃሳብ ቋንቋን፣ ስሜትን እና ተግባርን በማዋሃድ የአእምሮ፣ የልብ እና የእጅ ቋንቋን መናገር መቻል አለበት ብለዋል።  

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ግንኙነት፣

ከተለያዩ አገራት የመጡ ተማሪዎች እና መምህራን፣ ከምስራቅ እና ከምዕራብ የዓለማችን ክፍሎች ወደ ስኮላስ ድርጅት መጥተው ሲማማሩ፣ ሲጫወቱ እና ሲደንሱ የታዘቡት ቅዱስነታቸው እርስ በእርስ በመገናኘ፣ በምስራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል የባሕል ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው እንደገለጹት ሕጻናት እና ወጣቶች ከጎልማሶች በሚቀስሙት የሕይወት ልምድ በልባቸው ውስጥ ያለውን ምኞት እና ሕልም በመካከላቸው መለዋወጥ መልካም መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ካልተደረገ ጠንካራ መሠረት ያለው ታሪክ፣ ተስፋ፣ እድገት እና ትንቢት ሊኖር አይችልም ብለዋል። የስኮላስ ፋውንዴሽን ተማሪዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በተማሪዎች መካከል የሚታይ የጋራ ሕይወት ወደ ተቀሩት የዓለማችን ክፍሎች መድረስ አለበት ብለው፣ በዚህም ሁሉም ሰው ብዙ እውነታዎችን ፣ ቋንቋዎችን እና እምነቶችን ሊማር ይችላል ብለው፣ የሚማሩት ስለ ቁሳዊ ዓለም ብቻ ሳይሆን ስለ ሕይወትም ጭምር ነው ብለዋል።

የማበረታቻ ቃላት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ስኮላስ ኦኩሬንት” ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ስብሰባን በድረ ገጽ የቪዲዮ መገናኛ በኩል ለተካፈሉት ወጣቶች፣ ቤተሰቦች እና መምህራን በላኩት የማበረታቻ መልዕታቸው፣ መታወቅ ያለባቸው ሦስት ቃላትን፣ እነርሱም ምስጋና ፣ ትርጉም እና ውበት መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን ሦስት ቃላት እንዳይዘነጉ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፣ የስኮስላስ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን መስራች መምህራን በልባቸው ውስጥ የያዙትን ለሌሎች በነጻ እንደሰጡ ሁሉ እኛም ያለንን በደስታ ለሌሎች እያካፈልን፣ የሚያጋጥመንን ማኅበራዊ ቀውስ ለማሸነፍ በሕብረት መራመድ ይገባል ብለዋል።  

“ስኮላስ ኦኩሬንት” ፋውንዴሽን፣

ጳጳሳዊ መብት ያለው ስኮላስ ኦኩሬንት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ ትምህርትን እና የባሕል ግንኙነትን በማሳደግ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተማሪዎችን በቴክኖሎጂ፣ በአትሌቲክስ እና በስነ ጥበብ በኩል እንዲገናኙ የሚያደርግ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በ190 አገሮች ውስጥ የሚገኝ እና በግምት ወደ ግማሽ ሚሊዮን በሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ዘርፈ ብዙ የትምህርት አውታረ መረቦች ያሉት መሆኑ ታውቋል።

08 June 2020, 16:18