ፈልግ

ካህን በመስዋዕተ ቅዳሴ አገልግሎት ላይ፤ ካህን በመስዋዕተ ቅዳሴ አገልግሎት ላይ፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሮም ሰበካ ካህናት በወረርሽኙ ወቅት ምዕመናንን በማጽናናታቸው አመሰገኑ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ እሑድ ግንቦት 23/2012 ዓ. ም. የተከበረውን በዓለ ሃምሳ ወይም “ጴንጤቆስጤ” ዕለት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ለሮም ሰበካ ካህናት በላኩት መልዕክት፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ካህናት በኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ባጋጠሟቸው በርካታ ችግሮች ሳይሸነፉ፣ ችግሩን በዝምታ ሳይመለከቱ ከምዕመናኖቻቸው ጋር በመሆናቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣው የማኅበራዊ ርቀት ደንብ ቤተሰባዊ አንድነት የበለጠ እንዲጨምር አግዟል ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

የሮም ሀገረ ስብከት እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ የሆኑት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሮም ኣሰበካ ካህናት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ከምዕመናን ጋር ሆነው ህመማቸውን እና ሐዘናቸውንም የተካፈሉ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ካህናቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ አገልጋዮች እንደ መሆናቸው መጠን ፣ ችግሮችን ሳይፈሩ ከምዕምናን ጎን በመቆም ዕለታዊ ችግራቸውን በመጋራት ሲያጽናኑ እና ሲያበረታቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የአንድ ቤተሰብ አባልነትን ማጠናከር፣

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሮም ሰበካ ካህናት በላኩት መልዕክታቸው፣ በብርሃነ ትንሳኤው ወቅት የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት በጋራ ለማቅረብ የተመኙ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሳይሳካላቸው መቅረቱን ገልጸዋል። ቢሆንም ለእያንዳንዱ ካህን በላኩት መልዕክት አማካይነት፣ ካህናት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናቸው ከሚያገለግሏቸው ምዕመናን ሳይርቁ፣ መንፈሳዊ ጉዞን በኅብረት በመጓዝ አንድነታቸውን እንዲያረጋግጡ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። በማከልም በእነዚህ አስጨናቂ ወራት ውስጥ ከበርካታ ካህናት የምስክርነት መልዕክቶችን የተቀበሉ መሆኑንም አስታውሰዋል።

እንደ ቀደምት ደቀ መዛሙርት፣

ለካህናት በላኩት መልዕክታቸው የቀደምት ሐዋርያት ሕይወት ልምድ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያቱ ከሕዝቡ ተለይተው የስጋት እና የፍራቻ ሕይወት መኖራቸውን አስረድተው፣ ኢየሱስም “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” ባላቸው ጊዜ በደስታ የተሞሉ መሆኑን አስታስውሰዋል። የዘመናችንን ሰዎች በተለይም በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ድሆችን የሚያጋጥም ደስታ፣ ተስፋ፣ ሐዘን እና ስቃይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን እንዳጋጠማቸው “ደስታ እና ተስፋ” የተሰኘውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ አስረድተው፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የተደነገገውን ማኅበራዊ ርቀት የመጠበቅ ደንብ በምዕመናን እና በካህናት መካከል ያለውን ቤተሰባዊ አንድነት ይበልጥ በማጠናከር የተልዕኮ ጥሪን በተግባር እንዲወጡት ማድረጉን አስረድተዋል።

በስጋት እና ፍርሃት መካከል መገኘት፣

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው እጅግ አስፈሪ ጊዜ አልፎ አሁን በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እስካሁን የተከፈሉ መስዋዕትነቶች ከንቱ ሆነው እንዳይቀሩ አሁንም ጥበብ ፣ ማስተዋል እና የጋራ ቁርጠኝነት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። ሳናውቀው እና ሳንጠብቀው ከባድ ጉዳት ደርሶብናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የእምነታችን አጋር የሆኑ ቤተሰቦቻችንን፣ ጎረቤቶቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ የቁምስናችን ምዕመናን እና ካህናት በሞት አጥተናል ብለዋል። የቅርብ ወዳጅ እና ቤተሰብ የሆኑንትን በአግባቡ ለመሰናበት ዕድል ያላገኙ ሰዎች ጥልቅ ሐዘን ተመልክተናል ብለው፣ የጤና ባለሞያዎች ጭንቀት እና ሞት እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ፍራሃት እና ስጋትንም ለመመልከት በቅተናል ብለዋል።

በብቸኝነት ለመቆየት መገደድ፣

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው አካላዊ ስቃይ ብቻ ሳይሆን ከተቀረው ማኅበረሰብ ተነጥሎ በብቸኝነት መቀመጥን፣ በተለይም አቅመ ደካማ የሆኑ አዛውንት ረዳት አጥተው ብቻቸውን ሲሰቃዩ፣ በሰዎች መካከል አመጾችን እና የፍቅር መሻከርን ተመልከተናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሥራ ገበታቸው  የተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚበሉትን አጥተው ሲራቡ እና ሲጨነቁ መመልከታቸውን አስታውሰዋል።  

የምናደርገውን አጥተን ተጨንቀናል፣

የደረስብን መከራ የሰውን ልጅ ውስንነት ገሃድ አድርጎታል ያሉት ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይም እንቅፋት ፈጥሯል ብለው፣ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ችግሮችን በጋራ ሆነን ለማሸንፍም አቅም እንዳነሰን ተመልክተናል ብለዋል።  

ሁላችን በአንድ ጀልባ ተሳፍረናል፣

ይህን በመሰል አስጨናቂ ወቅት ላይ ስንገኝ ምቹ መንገድ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ወረርሽኙ ወደ አንድ ግለሰብ ወይም ወደ አንድ ማኅበረሰብ ብቻ የመጣ ሳይሆን ሁላችንን ሊያጠቃን የመጣ ወረርሽኝ መሆኑን አስረድተዋል።

አዳዲስ መንገዶችን መክፈት ያስፈልጋል፣

ወደ ፊት የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት፣ እግዚአብሔር የሚለንን በጥሞና በማዳመጥ ፣ በተስፋ በመሞላት፣ እርሱ ባዘጋጀልን መንገድ መጓዝ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ከዚህ አስጨናቂ ጊዜ ከወጣን በኋላ የምንጓዝበት መንገድ ከቀድሞ የተለየ ይሆናል ብለዋል። የምንጓዝበት መንገድ ፈጽሞ ከችግር ነጻ ሊሆን እንደማይችል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አሳስበዋል።  

02 June 2020, 18:08