ፈልግ

ፖርቹጋላዊው ዲፕሎማት አቶ ሶሳ ሜንዲስ ፖርቹጋላዊው ዲፕሎማት አቶ ሶሳ ሜንዲስ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የሕሊና ነፃነት ሁል ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ መከበር ይኖርበታል አሉ!

ፖርቹጋላዊው ዲፕሎማት አቶ ሶሳ ሜንዲስ ምክንያት የተመሰረተው እና በእየ አመቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሰኔ 17 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የህሊና ቀን መታሰቢያ የሚከበር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህንን የመታሰቢያ ቀን አስመልክተው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሰተላለፉት መልእክት የሕሊና ነፃነት ሁል ጊዜም ሆነ በየትኛውም ስፍራ መከበር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት በሰኔ 10/2012 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት በቫቲካን ካደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ሲሆን በየአመቱ እ.አ.አ በሰኔ 17 ቀን “የሕሊና ቀን” በመባል እንደ ሚከበር አክለው ገልጸዋል።

“የሕሊና ቀን” የሚከበረው የዛሬ ሰማኒያ ዓመታት በፊት ህሊናውን ለመከተል የወሰነው እና በሺዎች የሚቆጠሩ የአይሁዳዊያንን እና ሌሎች ስደት የደረሰባቸውን ሰዎች ሕይወት ለመታደግ የወሰነው የፖርቹጋላዊው ዲፕሎማት አሪስዲስ ደ ሶሳ ሜንዲስ በሰጠው ምስክርነት ምክንያት የተመሰረተ ቀን ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት “የሕሊና ነፃነት ሁል ጊዜም ሆነ በየትኛውም ቦታ መከበር እንዳለበት” ጥሪ አቅርበዋል። “እያንዳንዱ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል የእውቀት ብርሃን የሆነውን ህሊና ወጥነት ባለው መልኩ ምሳሌ ይስጥ” ብለዋል።

የሕሊና ተግባር

የአሪስዲስ ደ ሶሳ ሜንዲስ የህሊና ተግባር እርሱ ይከተለው ከነበረው የካቶሊክ እምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ እንደ ነበር በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ችግረኞችን ለመርዳት ባደርገው ጥረት በወቅቱ የነበረው መንግሥት የሰጠውን ቀጥተኛ ትዕዛዛት ችላ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሶሳ ሜንዴስ ምንም እንኳን እርሱ የፈጸመው ተግባር እጅግ ብዙ የሆነ መዘዝ እንደ ሚያመጣ የሚያውቅ ቢሆንም ቅሉ ዜግነቱ፣ ዘሩ፣ ሃይማኖት ወይም የፖለቲካ አመለካከቱ ምንም ይሁን ምን ለሁሉም ስደተኞች ቪዛ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልጸዋል።

“እኔ ሌላ እርምጃ መውሰድ አልችልም ነበር”

የዚህ ዓይነቱ ሰብዓዊ ተግባር እና የድፍረት ስሜት እርሱ ከቀሪው ዓለም እንዲገለል እና እንዲወገድ ያደርገው ተግባር መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ በፈጸመው በጎ ተግባር የተነሳ ይሰራው የነበረውን ዲፕሎማትነት ሥራውን ለመቀጠል ባለመቻሉ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሚችልበት ሥራ እንኳን እንዳያገኝ መከልከሉን ገልጸው የእርሱ ልጆች በጊዜው ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ እንዳያገኙ ተከልክለው እንደ ነበረ ገልጸዋል።

ቀሪውን ዕድሜውን በሙሉ ስሙን ለማንፃት ሲሞክር የኖረው ሲሆን ነገር ግን በወቅቱ በፖርቹጋሎች የፖለቲካ ስርዓት ችላ መባሉ ይታወሳል።

አሪስዲስ ደ ሶሳ ሜንዲስ በከፍተኛ ድህነት ሲማቅቅ ከኖረ በኋላ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 3/1954 ዓ.ም በሊዝበን በሚገኘው የፍራንችስካዊያን ሆሲፒታል ውስጥ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል። ነገር ግን በህይወቱ መገባደጃ ላይም እንኳ ድርጊቶቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ሰዎችን ሕይወት ለማዳን የተደርገ ትክክለኛ ተግባር መሆኑን ያውቅ ነበር። እሱ ራሱ እንደተናገረው “እኔ ከዚህ የተለየ እርምጃ መውሰድ አልችልም ነበር፣ ስለሆነም የደረሰብኝን ነገር ሁሉ በፍቅር እቀበላለሁ” ማለቱ ይታወሳል።

17 June 2020, 19:52