ፈልግ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ ከወንድማቸው ጆርጅ ራትሲንጌር ጋር፤      የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ ከወንድማቸው ጆርጅ ራትሲንጌር ጋር፤  

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ ከጀርመን ቆይታ በኋላ ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ተነገረ።

በጠና የታመሙ ወንድማቸውን፣ ሞንሲኞር ጆርጅ ራትሲንጌር ሊጠይቁ ወደ ትውልድ አገራቸው ጀርመን የተጓዙት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በጀርመን ካደረጉት የጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ቫቲካን በሰላም መመለሳቸው ታውቋል። ባለፉት ቀናት በእንግድነት ከቆዩባት የሬግኔስቡርግ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተነስተው ወደ ሙኒክ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ላይ ወደ ሮም አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸው እና ከአርባ አምስት ደቂቃ የመኪና ጉዞ በኋላ በቫቲካን ወደ ሚገኘው “ማቴር ኤክሌሲያ” ገዳም በሰላም መድረሳቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ ባለፈው ሐሙስ በጀርመን ወደ ሙኒክ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በብጹዕ አቡነ ሩዶልፍ ቮድሬሆልዘር አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑ ይታወሳል። የ96 ዓመት ዕድሜ ወንድማቸውን ሞንሲኞር ጆርጅ ራትሲንጌርን ከጠየቋቸው በኋላ አንዳንድ ቤተሰቦቻቸውንም የጎበኟቸው መሆኑ ታውቋል። ቀጥለውም የወላጆቻቸውን መካነ መቃብር እና የዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት ዓመታት የተስተናገዱበትን የታላቅ እህታቸው መኖሪያን ለመጎብኘት መቻላቸው ታውቋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከዚህም በተጨማሪ በጀርመን የቅድስት መንበር እንደራሴ ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ኒኮላ ኤተሮቪች ጋር መገናኘታቸውንም ቫቲካን ኒውስ አስታውቋል።     

22 June 2020, 16:10