ፈልግ

የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ በዓል እሁድ ዕለት ይከበራል። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ በዓል እሁድ ዕለት ይከበራል። 

የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ በዓል እሁድ ዕለት ይከበራል።

የጎሮጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው እሁድ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚታሰብበት አመታዊ በዓል እንደ ሚከበር የተገለጸ ሲሆን ይህ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በምያሳርጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በታላቅ መንፈሳዊነት የከበራል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ክቡር የሆነው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚዘከርበት አመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔት በእየ አመቱ እንደ ሚከበር ይታወቃል። ይህ ታላቅ እና ክቡር የሆነ በዓል በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከበር ሲሆን በቅድሚያ በቫቲካ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ምስዋዕተ ቅዳሴ ያሳርጋሉ በመቀጠልም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ቅዱስነታቸው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው የክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደም በተመለከተ አስተንትኖ ያደርጋሉ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ራት ላይ የመሰረተውን ቅዱስ ቁርባንን ለመዘከር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በእየ አመቱ የእምነታችን መዕከል የሆነውን የክርስቶስ ክቡር ሥጋ እና ክቡር ደሙን በደስታ በመዘከር እርሱ ለእኛ መንፈሳዊ ምግብ እና መጠጥ እንዲሆን ስለሰጠን፣ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር የሆነ ደሙ አምልኮና ስግደት የምናደርገውም በዚሁ ምክንያት ነው።

እግዚኣብሔር አብ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ ለሰዎች የሕይወት እንጀራ ይሆነን ዘንድ ከሰማይ ወደ ምድር ልኮታል። በዚህም ምክንያት ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን መስዋዕት በማድረግ ሥጋውን እና ደሙን ለእኛ የሰጠን።

ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ ነኝ (. . .) ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” ብሎ እንደ ነበረ ይታወሳል። በእርግጥ ኢየሱስ እኛን ከኃጢአት ባርነት ለማውጣት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ወደ ተስፋይቱ ምድር የምናደርገውን ጉዞ በድጋሚ አለምልሞታል። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ ዓለም በሕይወት እንዲኖር ያደርጋል፣ይህንን ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም የሚቀበል ሰው በኢየሱስ ውስጥ ይኖራል ኢየሱስም በእርሱ ይኖራል፣ ኢየሱስን መምሰል ማለት ደግሞ እርሱን መሆን ማለት ነው፣ በልጁ አማካይነት የእግዚኣብሔር ልጅ መሆን ማለት ነው።

በኢየሱስ ሞት አማካይነት ተስፋ ቆርጠው ወደ ኤማሁስ በመጓዝ ላይ የነበሩ የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንጀራውን በቆረሰ ጊዜ እንዳወቁት እና እንደ ቀረቡት ሁሉ እኛንም በቅዱስ ቍርባኑ አማካይነት ወደ እኛ በመቅረብ እምነታችንን በመንፈሳዊ ምግብ ይመግባል፣ ተስፋችንን እና ፍቅራችንን ያለመልማል፣ በመካራዎች እና በፈተናዎቻችን ወቅቶች ሁሉ ያጽናናናል፣ ለፍትህና ለሰላም መስፍን እንድንሥራ ይረዳናል።

ክርስቶስ እኛ ትእዛዛቱን በተግባር መኖር እንችል ዘንድ ለመርዳት መንፍሳዊ ጥንካሬን እናገኝ ዘንድ በቅዱስ ቁርባኑ አማካይነት ራሱን በመስዋዕትነት ያቀርባል። እርሱ እንደ ሚወደን እኛም እንድንዋደድ፣ እንግዳ ተቀባይ የሆነ ማኅበረሰብ እንሆን ዘንድና ለሰው ልጆች ፋጎቶች በተለይም ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ፣ ለድኾች እና ርዳታችንን ለሚሹ ሰዎችን ሁሉ ለመርዳት እንድንዘጋጅ ያግዘናል።

የክርስቶን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን መመገብ ማለት የራሳችን የግል ፍላጎቶች ወደ ጎን በመተው በተቃራኒው ጌታ ይመራን ዘንድ ራሳችንን ለጌታ ፈቃድ ማስገዛት ማለት ነው። በዚህ መልኩ ከኢየሱስ ዘንድ በነጻ የተሰጠን ፍቅር፣ በመንፈስ ቅዱስ ርዳታ አማካይነት ለእግዚኣብሔር እና ለእህት ወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል።

ቅዱስ የሆነውን የኢየሱስን ሥጋ እና ክቡር ደም መቀበል ማለት ኢየሱስን መምሰል ማለት ነው፣ ይህም የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንድንቀርብ ያደርገናል። “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” (1ኛ ቆሮንጦስ  10፡16-17)።

10 June 2020, 18:28