ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔር ስለሚጠብቀን በፍጹም መፍራት አይኖርብንም አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰኔ 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እርሳቸው ዘወትር እሁድ ዕለት በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የሚያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ለመከታተል ለተሰበሰቡ ምዕመናን ያደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ “ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ አውጁት፤ ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ” (ማቴዎስ 10፡26-33) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል  ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “እግዚአብሔር ስለሚጠብቀን በፍጹም መፍራት አይኖርብንም” ማለታቸው ተግልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ እሑድ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 10፡26-33) ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው ጥሪ የሚያስከትለው ፍሃት እንዳይኖር፣ በህይወት ፈተናዎች ላይ ጠንካራ እና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው በማውሳት ስለሚጠብቃቸው መከራ አስቀድሞ ያስጠነቅቃቸዋል። የዛሬው ምንባብ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ሚመጣ የሚያመለክተውን ቅዱስ ወንጌል ለመጀመርያ ጊዜ ለመስበክ እየተዘጋጁ ለሚገኙ ሐዋርያት የሚያዘጋጃቸው የሚስዮናዊ ንግግር አካል ነው። ኢየሱስ “አትፍሩ” በማለት ያለማቋረጥ አጥብቆ መክሯቸዋል ፣ እናም ኢየሱስ የሚያጋጥሟቸውን ሦስት ተጨባጭ ሁኔታዎችን ገልጾላቸዋል።

በመጀመርያ እና ከሁሉም ይበልጥ ጣፋጭ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ የተላኩ ሰዎችን ነፍስ በከንቱ ለማጥፋት ወይም ዝም ለማሰኘት እና ለማጥፋት የሚፈልጉ ሰዎች የጠላትነት መንፈስ ይገኛል። በዚህን ጊዜ ​​ኢየሱስ እርሱ በአደራ የሰጣቸውን የደህንነት መልእክት እንዲያስተላልፉ ኢየሱስ ያበረታታቸዋል። ለጊዜው ይህንን መልዕክቱን በተወሰነ መልኩ በደቀመዛሙርቱ አነስተኛ ቡድን ውስጥ አስተላልፏል። እነሱ ግን ቅዱስ ወንጌሉን “በብርሃን” ተሞልተው ማለትም በግልጽ ሊሰብኩ የገባል፣ እናም ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው “ሰገነት” ላይ ሁነው (በይፋ) ማወጅ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

የክርስቶስ መልእክተኞች የሚያጋጥሟቸው ሁለተኛው ችግር ደግሞ በእነሱ ላይ የሚደርሰው አካላዊ ስጋት ነው፣ ማለትም በግለሰብ ደረጃ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ለስደት ሊጋላጡ ይችሉ ይሆናል፣ እስከ መገደል ድረስ ሊደርሱ ይችሉ ይሆናል። የኢየሱስ ትንቢት በየዘመናቱ ተፈፅሟል፣ ይህ አሳዛኝ እውነታ ነው፣ ነገር ግን የምሥክሮቹን ታማኝነት ያሳያል። በዛሬው ጊዜ እንኳን ሳይቀር በዓለም ሁሉ ውስጥ ምን ያህል ክርስቲያኖች እየተሰደዱ ይገኛሉ! ለወንጌል ፍቅር ሲሉ ይሰቃያሉ፣ የዘመናችን ሰማዕታት ናቸው። ከጥንት ጊዜያት ከነበሩት ሰማዕታት በቁጥር የሚበልጡ ሰማዕታት በአሁኑ ወቅት እንደ ሚገኙ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፣ እጅግ በጣም ብዙ ሰማዕታት አሉ፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ለሰማዕትነት የተዳረጉ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ኢየሱስ ትናንት እና ዛሬ ስደት የሚደርስባቸውን እነዚህን ደቀመዛሙርት “ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ” (ማቴ 10፡28) በማለት ይመክራቸዋል። የወንጌላዊያንን ኃይል በእብሪት እና በኃይል ለማጥፋት የሚፈልጉትን መፍራት አያስፈልግም። በእርግጥ በነፍስ ላይ ምንም ማድረግ አይችሉም ፣ ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን አንድነት ማጥፋት አይችሉም፣ ማንም ይህንን ከደቀመዛሙርቱ ሊወስድ አይችልም ፣ ምክንያቱም ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። አንድ ደቀመዝሙር ሊኖረው የሚገባው ብቸኛ ፍርሃት መለኮታዊ ስጦታን ማጣት፣ ከእግዚአብሔር ያለውን ቅርበት እና የእግዚአብሔር ወዳጅነት ማጣት ፣ በወንጌል መሠረት መኖርን ማቆም ፣ በዚህም የኃጢአት ውጤት ውስጥ መዘፈቅ፣ አንድ ደቀመዝሙር ሊፈራው የሚገባው ጉዳዮች እነዚህ ናቸው።

የኢየሱስ ሐዋርያት ሊያጋጥማቸው የሚችለው ሦስተኛው የመከራ ዓይነት ፣ እግዚአብሔር ራሱ እነርሱን እንደራቃቸው፣ ከእነርሱ እጅግ በጣም ርቆ የሚገኝ እና በዝምታ የሚመለከታቸው እነደ ሆነ ሁኖ የሚሰማቸው ስሜት ነው። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ እንዳይፈሩ አጥብቆ አሳስቧቸዋል ፣ ምክንያቱም እነዚህ እና ሌሎች አደጋዎች ቢያጋጥማቸውም እንኳን የደቀመዛሙርቱ ሕይወት በሚወደን እና በሚንከባከበን በእግዚአብሔር እጅ ላይ ጸንቶ ይኖራል። እነሱ እንደ ሦስቱ ፈተናዎች ናቸው- ቅዱስ ወንጌልን እንዲያው ላይ ላዩን ብቻ መስብከ የመጀመርያው ፈተና ሲሆን፣ ሁለተኛው ስደት ሦስተኛ እግዚአብሔር ትቶናል ረስቶናል የሚል ስሜት ናቸው። ኢየሱስ እንኳ ሳይቀር በአትክልቱ ስፍራ በነበረበት ወቅት እና በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ይህ ፈተና ገጥሞታል “አባት ሆይ ፣ ለምን ተውከኝ?” በማለት ተናግሮ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የዚህ ዓይነት መንፈሳዊ ድርቀት ሊሰማው ይችላል። እሱን መፍራት የለብንም። በፊቱ እጅግ የተከብረን ስለሆንን አብ ይንከባከበናል። አስፈላጊ የሆነው ነገር ግልጽነት ፣ የምስክርነት ድፍረቱ፣ የእምነት ምስክርነታችን ነው፣- “ኢየሱስን በሌሎች ፊት በማየት” እና መልካም ማድረግ መቀጠል ይኖርብናል።

በመከራ እና በአደጋ ጊዜ በእግዚአብሔር የመተማመን ምሳሌ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ማርያም በጭንቅ ጊዜያት እጅ እንዳንሰጥ፣ ይልቁንም ሁልጊዜ እራሳችንን ለእርሱ እና ለችሮታው በመታመን፣ ከክፉ ይልቅ የእግዚአብሔር ጸጋ ሁል ጊዜ የበለጠ ኃያል ስለሆነ በእርሱ በመተማመን መኖር የምንችልበትን ጸጋ እድትሰጠን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

21 June 2020, 18:03