ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጤና ባለሞያዎች ጋር ሆነው (ከማኅደር የተወሰደ)  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጤና ባለሞያዎች ጋር ሆነው (ከማኅደር የተወሰደ)  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ለተጠቁ አገሮች የሕክምና መገልገያ መሣሪያን አበረከቱ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕክምና የሚያገለግሉ 35 የመተንፈሻ መሣሪያዎችን ለደቡብ አሜሪካ፣ ለእስያ፣ ለአፍሪካ እና ለአውሮፓ አገሮች ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ያበረከቷቸው 35 የመተንፈሻ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች በየአገራቱ በሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች በኩል ወደ አገራቱ መድረሳቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎቹ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የመተንፈስ አቅም ለሚያጥራቸው ሕሙማን ንጹሕ አየርን በቀላሉ ለመተነፈስ የሚያስችሉ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሣሪያ እጥረት በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎች ለሞት የሚዳረጉ መሆኑ ታውቋል።

የቅዱስነታቸው የዕርዳታ ማስተባባሪያ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት እንዳመለከተው፣ ባሁኑ ጊዜ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፣ በዓለማችን ውስጥ በርካታ አገሮች ከአቅም ማነስ የተነሳ የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች እጥረት የሚታይባቸው መሆኑን አስታውቋል።   

የቅዱስነታቸው የዕርዳታ ማስተባባሪያ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት በማከልም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል ዕርዳታ የተደረገላቸው አገራት በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በእስያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበባቸው እና በማስመዝገብ ላይ የሚገኙ አገሮች መሆናቸውን አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካበረከቷቸው 35 የመተንፈሻ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች መካከል አራቱ ወደ ሃይቲ፣ ሁለቱ ወደ ዶሜኒካን ሪፓብሊክ፣ ሁለቱ ወደ ቦሊቪያ እና አራቱ ወደ ብራዚል፣ የተቀሩት ወደ አፍሪካ እና እስያ አገሮች መላካቸውን ሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ አገራት ለሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው የበሽተኞች ፈውስ ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸው በማቅረብ የእርሷን እርዳታ መለመናቸውን ገልጸዋል።

ወደ ሁለት ሚሊዮን ከግማሽ ከሚጠጉ የኮቪድ-19 ቫይረስ ተጠቂዎች መካከል 124 ሽህ ሰዎችን በሞት ካጣች ከሰሜን አሜሪካ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥርን ያስመዘቡ ዶሜኒካን ሪፓብሊክ፣ ቦሊቪያ እና ብራዚል መሆናቸውን ያስታወቀው ሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ፣ በእነዚህ አገራት ውስጥ በቫይረሱ ከተያዙት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል 55 ሺህ ሰዎች በሞት የተለዩን መሆናቸውን አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕርዳታ ካበረከቷቸው 35 የመተንፈሻ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች መካከል ሦስቱ ለደቡብ አሜሪካ አገር ኮሎምቢያ እና ሁለቱ 4,300 የቫይረሱ ተጠቂዎች ለሚገኙባት ኤኳዶር መላኩ ታውቋል። ዕርዳታዎቹ በአገራቱ በሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች አማካይነት ለአገራቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተሰጠ ሲሆን በኤኳዶር፣ ኪቶ ለሚገኝ ኤውጄኒዮ ኤስፔዮ ሆስፒታል የሚሰጥ መሆኑን በኤኳዶር የቅድስት መንበር እንደራሴ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አንድሬስ ካራስኮሳ ለሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት አስታውቀዋል። የቅዱስነታቸው እርዳታ በኮቪድ-19 ቫይረስ መዛመት የተነሳ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ለደረሰባቸው የላቲን አሜሪካ አገሮች፣ ሆንዱራስ፣ ሜክሲኮ እና ቨነዙዌላ መላኩን ሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት አስታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕርዳታ በጸሎታቸው ለሚያስታውሷት የአፍሪካ አህጉርም መድረሱን ያስታወሰው ሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ ወደ ካሜሩን እና ሞዛምቢክ አራት የመተንፈሻ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች መላካቸ ሲታወቅ፣ በእስያ አህጉር ውስጥ ለባንግላዲሽ፣ በአውሮፓ ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ለሚገኝባት ዩክሬን፣ ለእያንዳንዳቸው ሁለት የመተንፈሻ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች የተላኩላቸው መሆኑን ሐዋርያዊ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።              

27 June 2020, 19:02