ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነውን መጽናናት ከሌሎች ጋር መጋራት ያስፈልጋል አሉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የጎርጎሮርሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክስቲያን ግንቦት 23/2012 ዓ. ም. የተከበረውን የበዓለ ሃምሳ ‘ጴንጤቆስጤ’ መታሰቢያን ዕለት ምክንያት በማድረግ፣ “መንግሥትህ ይምጣ” በሚል አርዕስት መልዕክት አስተላልፈዋል። የቅዱስነታቸውን መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት አሰናድተን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥

የቫቲካን ዜና፤

"ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

ከሊቀ ጳጳሳ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በመሆን የልቤን ሃሳብ በደስታ ላካፍላችሁ እወዳለሁ። ይህም በበዓለ ሃምሳ ዕለት የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል የወረደበት፣ የጴንጠቆስጤ ዕለት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በመካከላችን በመገኘት፣ ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ተስፋን፣ ሰላምን እና ደስታን ወደ እኛ አምጥቷል። መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ዓለም ሕይወትን አግኝቷል። ለወራት ያህል ወደ መላው ዓለም በመዛመት ብዙዎችን ለሞት ከዳረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዴት ይለያል? የእግዚአብሔር ሕይወት የሆነው ፍቅር  በልባችን እንዲፈስ ዛሬ ከምን ጊዜም በላይ መንፈስ ቅዱስን መለመን ያስፈልጋል። ለወደ ፊት ሕይወታችን መልካም ዕድልን ከፈለግን፣ ልባችን ጥሩ ነገርን ለማስተናገድ የተዘጋጀ መሆን አለበት።   

መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች እርስ በእርስ ይገናኙ ነበር። በእነዚህ ወራት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን በመጠበቅ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ራሳችንን መከላከል የምንችልባቸውን ሌሎች መመሪያዎችንም ስናከብር ቆይተናል። በሌላ ወገንም በፍርሃት ውስጥ የወደቁት እና ለሕይወታቸው ደህንነት እርግጠኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ችለናል። በችግር እና በሐዘን ውስጥ ወድቀው መጽናናትን የሚፈልጉ ስንቶች ናቸው! ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ በተናገረ ጊዜ፣ ጰራቅሊጦስ የሚለውን ቃል እንዴት እንደተጠቀመ አስባለሁ። ጰራቅሊጦስ ማለት አጽናኝ ማለት ነው። ብዙዎቻችሁ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ መጽናናትን በማግኘት፣ በሌሎች መወደዳችሁን የሚያረጋግጥ ውስጣዊ ሰላምን ውስጣዊ ብርታትን ማግኘት ተለማምዳችኋል። ብቻችን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን መንፈስ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ወዳጆቼ! ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነውን መጽናናት እና የእግዚአብሔርን አለኝታ ከሌሎች ጋር መጋራት ያስፈልጋል።

ይህን እንዴት ማከናወን እንችላለን? ለራሳችን የምንመኛቸውን መልካም ነገሮች በሙሉ እናስታውስ፤ መጽናናትን፣ ብርታትን፣ የሰዎችን እንክብካቤ እና ጸሎት፣ ችግራችንን እና ሐዘናችንን የሚካፈሉትን እናስብ። ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው (ማቴ. 7፡12)። ሌሎች እንዲያዳምጡን የምንፈልግ ከሆነ በቅድሚያ እናድምጣቸው። ከሌሎች ዘንድ ብርታትን የምንፈልግ ከሆነ አስቀድመን እናበረታታቸው። ሰዎች እንክብካቤ እንዲያደርጉልን የምንፈልግ ከሆነ፣ ከማኅበረሰቡ ተገልለው ብቻቸው የቀሩትን እንንከባከባቸው። የነገን ተስፋ የምንፈልግ ከሆነ፣ የዛሬን ተስፋ እንስጣቸው። ዛሬ ዓለማችን ተስፋን በጣም ተርቦ ይገኛል። ምን ያህል የሕመም ስቃይ በዙሪያች አለ፣ ምን ያህል ልበ ባዶነት በዙሪያችን አለ? ብርታትን ማግኘት ያልቻሉ ስንት ሕመሞች በዙሪያችን አሉ? በመሆኑም ከመንፈስ ቅዱስ የተገኘውን መጽናናት ለሌሎች የምናዳርስ እንሁን። ወደ ፊት ስንጓዝ እግዚአብሔር አዲስ መንገድ እንዲከፍትልን የተስፋ ብርሃናችንን እናብራ።

በሕብረት ሆነን ለምንጓዘው መንገድ አጋዥ የሚሆን አንድ ሃሳብ ከእናንተ ጋር መጋራት እወዳለሁ። ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር ለሰብዓዊ ቤተሰብ ምሕረትን የመመስከር ፍላጎቴ ከፍተኛ ነው። የአንድነትን ስጦታ ከመንፈስ ቅዱስ እንለምን። የወዳጅነትን መንፈስ ወደ ሌሎች ዘንድ ማድረስ የምንችለው እንደ ወንድም እና እንደ እህት ስንኖር ብቻ ነው። የተለየ መንገድ እየተጓዝን ሌሎችን አንድ ሁኑ ማለት አንችልም። በመሆኑም እርስ በእርስ በጸሎት በመተጋገዝ፣ ለሌሎች ሰዎች ያለንን ሃላፊነት በተግባር እንግለጽ።

መንፈስ ቅዱስ ጥበብንና መልካም ምክርን ይሰጣል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የሰው ልጅ ነፍስን እና የሥራ ክብርን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ፣ ውስብስብ እና ከባድ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ሃላፊነት ለተጣለባቸው በሙሉ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንለምን። የጤና አገልግሎትን እና የሥራ ዕድልን ለማሳደግ፣ የኑሮ አለመመጣጠንን እና ድህነትን ለማስወገድ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት የነበረውን እና በራስ ወዳድነት ላይ ከተመሠረቱ የብልጽግና መንገዶች በመመለስ፣ በድህነት ምክንያት ወደ ኋላ የቀሩትን የሚያሳትፍ መልካም የሆነ ሰብዓዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ብዙዎች ይህን በተግባር እያዋሉ ሲሆን፣ እኛም አካሄዳችንን ለውጠን መልካም ተግባራችንን እንድናከናውን እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ‘በበዓለ ሃምሳ ቀን ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በድፍረት እንዲህ አላቸው፥ ንስሓ ግቡ፤ ተለወጡ፣ ከተሳሳተ የሕይወት መንገዳችሁም ተመለሱ’።  (የሐዋ. 2፡38) እኛም ማድረግ ያለብን ይህ ነው። ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ጎረቤቶቻችን በመመለስ፣ የድሆችን እና የምድራችንን ጩሄት ችላ ሳንል ማድመጥ ይኖርብናል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን የርሃብ፣ የጦርነት፣ የንቀት እና የግድ የለሽነት ወረርሽኞችን ለመከላከል መተባበር ይኖርብናል። ሩቅ መሄድ የምንችለው አብረን የምንጓዝ ከሆነ ብቻ ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እናንተ ሕይወት የሚገኝበት የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና አብሳሪዎች እና የተስፋ ምልክቶች በመሆናችሁ ልባዊ ምስጋናዬን እያቀርብኩላችሁ፣ እግዚአብሔር እንዲባርካችሁ ጸሎቴን አቀርባለሁ። እናንተም በበኩላችሁ የእርሱን ቡራኬ እንድትልምኑልኝ እጠይቃችኋለሁ። አመሰግናለሁ"።   

31 May 2020, 10:27