ፈልግ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።

የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ አንድ እንዲሆኑ ያቀረበውን ጸሎት በመከተል ክርስቲያኖችን ወደ አንድነት እንዲደርሱ በመመኘት ይፋ ያደረጉት “አንድ ስለ መሆን” የተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 25ኛ ዓመት መታሰቡ ታውቋል። ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ይፋ የሆነው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የዘመናችን አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበትን ደርጃ ለማወቅ እና ጥረታቸውን በአዲስ መልክ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያግዝ ትንቢታዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “አንድ ስለ መሆን” የተሰኘ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ዛሬ በዘመናችን ክርስቲያኖች ወደ አንድነት ጎዳና ለሚያድረጉት ጉዞ ትንቢታዊ መልዕክቱን በማሰማት፣ የመከራ ጽዋን ከመቀበሉ በፊት ደቀ መዛሙርቱ አንድ እንዲሆኑ በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ዘንድ ያቀረበውን ጸሎት መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

የክርስቲያኖችን አንድነትን የተመኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣

ክርስቲያኖች በተናጠል መጓዝ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ የሚጻረር መሆኑን የተገነዘቡት እና በልባቸውም ቅሬታን የፈጠረባቸው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለክርስቲያኖች አንድነት ቅድሚያን በመስጠት ጥረት ያደረጉ መሆኑ ይታሳል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወቅቱ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እንዳስገነዘቡት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ማለት የኢየሱስ ክርስቶስን የአንድነት ዕቅድ መሻት ማለት እንደሆነ ማስረዳታቸው ይታስወሳል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከባሕል አጥባቂዎች በኩል ክስ ቀቦባቸዋል፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ከመሆኑ ሰባት ዓመት በፊት በፈረንሳይ አገር ተቃውሟቸውን ያሰሙት ሊቀ ጳጳስ ማርሴል ለፌቭረ፣ ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ ጥረት ለካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እንቅፋትን የሚፈጥር፣ እምነቷንም የሚያዛንፍ፣ በርካታ የሁለት ሺህ ዓመት የእምነት ባሕሏንም የሚቃረን ነው በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል። ሊቀ ጳጳስ ማርሴል ለፌቭረ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 1991 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ተከታዮቻቸው “አንድ ስለ መሆን” በሚለው በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በማሳደግ፣ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ የቤተክርስቲያኒቱን ባሕል በመቀየር አዲስ ባሕልን ሊያሳድግ ጥረት ያደርጋል በማለት የተነሱ መሆኑ ይታወሳል። ለዚህ የተሳሳተ ሃሳብ ምላሻቸውን የሰጡት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል እንድገለጹት፣ ባሕል ዘላቂ፣ በቀናት ወይም በዓመታት የማይገደብ፣ በትውልዶች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚመጣ፣ ከሰዎች እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ከሌሎች የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ራሱን መነጠል የማይችል መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል።

ውይይት ያልተጠበቁ ግኝቶች እንዲፈጠሩ የሚያድረግ፣ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው    

“አንድ ስለ መሆን” የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ለውይይት ቅድሚያን የሚሰጥ እና በውይይት አማካይነት በሌሎች ዘንድ ያለውን ሃብት ለማወቅ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ታውቋል። የጋራ ውይይት ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ጋር ለተደረጉ ፍሬያማ ግንኙነቶች መንገድ ከፋች፣ በሮም እና በቆንስጥንጢንያ ቤተክርስቲያናት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማስወገድ ድጋፍ የሆነ እንዲሁም ከምስራቃዊት ቤተክርስቲያን ጋር የጋራ ክርስቶሳዊ መግለጫዎች ለማውጣት ያገዘ መሆኑ ታውቋል። የጋራ ውይይት ለሕጋዊ ልዩነቶች እውቅናን በመስጠት፣ የተለያዩ ቅራኔዎችን በማስወገድ ለአንድነት ጉዞ መንገድ የጠረገ መሆኑ ታውቋል። “አንድ ስለ መሆን” የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የጋራ ውይይት ባሕል ዕድል በማመቻቸት ሁለት ተመሳሳይ መነሻ ያላቸውን አስተሳሰቦችን ለማቀራረብ ዕድል ያመቻቸ መሆኑ ታውቋል።

እውነት በተለያዩ መንገዶች ሊገለጥ ይችላል፣

የጋራ ውይይት የእምነት አቅጣጫን ለማስቀየር ወይም የቀኖናን ትርጉም ለማስቀየር አለመሆኑን ያስረዱት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እውነት በተለያዩ መንገዶች ሊገለጥ ይችላል ብለው፣ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ለመድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙት በሙሉ በግልጽ መቀመጥ አለበት ብለዋል።

ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውይይት ወደ የጋራ ፍቅር ውይይት፣

“አንድ ስለ መሆን” የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ የካቶሊክ እምነት የሚገልጽበትን መንገድ እና ዘዴ ከወንድሞች ጋር ለመነጋገር እንቅፋት እንዳልሆነ የሚያሳውቅ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሐዋርያዊ የስልጣን ደረጃ መኖሩን እና ቤተክርስቲያንም ቀጣይነት ያለውን ለውጥ እንድታደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠራች መሆኗን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አረጋግጠዋል። የጋራ ውይይት በግንባር ቀደምትነት የሚያተኩረው በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ላይ ሳይሆን የሰውን ልጅ የሚያሳትፍ በመሆኑ የፍቅር ውይይት ነው ብለው ከፍቅር አንድነት ሊገኝ እንደሚችል ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስገንዝበዋል።

የጸሎት አስፈላጊነት፣

በአብያተ ክርስቲያናት የውህደት ጎዞ ላይ የጋራ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ክርስቲያኖች በጸሎት በሚተባበሩበት ጊዜ ከሚከፋፍላቸው ይልቅ አንድ የሚያደረጋቸው መንገድ እንደሚበልጥ አስረድተዋል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተደረገው የስርዓተ አምልኮ ሥርዓት መታደስ መልካም ግንኙነት እንዲመጣ የረዳ መሆኑ ሲታወቅ፣ በአንድ ላይ ሲኮን በአንድ ልብ ወደ እግዚአብሔር አባታችን መቅረብ ቀላል እንደሚሆን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው አስረድተዋል።

ለነጻነት፣ ለፍትህ እና ለሰላም የሚደረግ የጋራ ጥረት፣

የአብያተ ክርስቲያናት የአንድነት ጉዞ ካስገኗቸው ውጤቶች መካከል፣ የሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደሚያስረዳው፣ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በኩል የተደረጉ የነጻነት፣ የፍትህ እና የሰላም ጥረቶች የሚጠቀሱ ሲሆን የክርስቲያኖች የጋራ ድምጽ ከአንድ ድምጽ ይልቅ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ አስረድቷል።

ከመፍረድ ይልቅ ምሕረት መደራረግ ያስፈልጋል፣

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እንደገለጹት የጥላቻን እና የቅራኔን መንፈስ በማስወገድ፣ ሁል ጊዜ አሉታዊ ገጽታዎችን ከመመልከት ይልቅ፣ በሌሎች ላይ ፍርድን ከመስጠት ይልቅ ምሕረትን መደራረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ እንቅፋቶችን አልፈን የልዩነት ግድግዳን ማፍረስ እንድንችል የእግዚአብሔርን እገዛ መጠየቅ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።          

ወደ አንድነት የምትጓዝ ቤተክርስቲያን፣

“አንድ ስለ መሆን” የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ የቤተክርስቲያንን የሁለት ሺህ ዓመት ታሪካዊ ጉዞን በአጭሩ የሚገልጽ፣ ቤተክርስቲያን ለተጓዘችባቸው መንገድ ብርሃን በመሆን ያገለገለ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑ ተመልክቷል። ቤተክርስቲያን ከመጀመሪያው አንስቶ የሐዋርያትን ፈልግ በመከተል፣ በእግዚአብሔር ቃል በመመራት እና መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠው ድጋፍ ለመመራት ከፍተኛ እገዛን ያደረገ ቃለ ምዕዳን መሆኑ ታውቋል። ቅዱስ ሲፕሪያኖስ “ወንድሞች ታርቀው ወደ መንበረ ታቦት መቅረብን መማር አለባቸው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የጥለኞችን መስዋእት አይቀበልምና፤ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ይዘን የምንቀርበው ታላቁ መባ ሰላም፣ ወንድማዊ እርቅ እና በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም የተመሠረተ አንድነት ነው።” ማለቱን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስታውሰው፣ “አንድ ስለ መሆን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ክርስቲያኖችን በሙሉ ወደ አንድነት የሚደርሱበትን የአንድነት ጸጋ ከእግዚአብሔር እንድንለምን አደራ ማለታቸው ይታወሳል።  

26 May 2020, 16:25