ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእግዚአሔር ድምፅ ወቅታዊ በሆነ መልኩ ይናገራል መልካም እንድናደርግ ይጋብዘናል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም  በዕለቱ በተነበበውና “ውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።  የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም።ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” (ዮሐንስ 10፡ 1 10) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን “የእግዚአብሔር ድምፅ ወቅታዊ በሆነ መልኩ ይናገራል፣ እናም መልካም እንድናደርግ አሁን ይጋብዘናል” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በምናከብረው አራተኛው የፋሲካ ሳምንት እሑድ ኢየሱስ መልካም እረኛ መሆኑ የሚታሰብበት እለት ነው። የእለቱ ቅዱስ ወንጌል “በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል” (ዮሐንስ 10፡3) በማለት ይናገራል። ጌታ በየስማችን ይጠራናል፣ እርሱ የሚጠራን ደግሞ ስለሚወደን ነው። ሆኖም ልንከተላቸው የማይገባን ሌሎች ድምጾች እንዳሉ በመግለጽ ባዕድ የሆኑ ድምጾች፣ የሌቦች እና በበጎቹ ላይ አደጋ ሊያደርሱ የሚፈልጉትን ድምጾች እንዳንከተል ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል።

እነዚህ የተለያዩ ድምጾች በውስጣችን ያስተጋባሉ። ለሕሊና በደግነት የሚናገር የእግዚአብሔር ድምፅ አለ ፣ ወደ ክፋት እንድናመራ የሚያደርገን ፈታኝ ድምፅም አለ። የመልካሙን እረኛ ድምፅ ከሌባው ድምፅ እንዴት መለየት እንችላለን? የሚያበረታታውን የእግዚአብሄርን ድምጽ ክፉ እና መጥፎ ነገር ከሚመክረው ድምጽ እንዴት መለየት እንችላለን? እነዚህን ሁለት ድምጾች መለየት የሚያስችለንን የማስተዋል ችሎታ መማር እንችላለን፤ ሁለቱም ድምጾች በእውነቱ ሁለት የተለያዩ ቋንቋዎች ናቸው፣ ልባችንን የሚያኳኩበት ሁለት ተቃራኒ የሆኑ መንገዶች አሏቸው። እነሱ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገራሉ። አንዱን ቋንቋ ከሌላው እንዴት እንደምንለይ ስለምናውቅ በእዚህም የተነሳ የእግዚአብሔርን ድምፅ እና የክፉውን ድምፅ መለየት እንችላለን። የእግዚአብሔር ድምፅ በጭራሽ አያስገድድም - እግዚአብሔር ሐሳብ ያቀርብልናል እንጂ ሐሳቡን በግድ በእኛ ላይ አይጭንም፣ እራሱን ለእኛ ቅርብ ያደርጋል፣ እርሱ አያስገድድም። ይልቁን መጥፎው የሆነው ድምጽ ያታልለናል ፣ ያሽከረክረናል፣ ያስገድደናል፤ የሚያነቃቁ ህልሞችን ያነሳሳል፣ ስሜታዊ የሆኑ ነገሮችን ያስተላልፋል። በመጀመሪያ ደረጃ ጭፍን በሆነ ሐስተሳሰብ ተሞልተን ሁሉንም ነገሮች ማከናወን የምንችል ሰዎች እንደ ሆንን ሆኖ እንዲሰማን እና እንድናምን ያደርገናል ፣ ከዚያ በኋላ ባዶ እንደ ሆንን ሆኖ እንዲሰማን በማድረግ ብቻችንን ጥሎ ከሄደ በኋላ “ምንም ዋጋ የለህም” በማለት ይከስናል። በሌላ በኩል ደግሞ  የእግዚአብሔር ድምፅ በብዙ ትዕግሥት ያርመናል ፣ ሁል ጊዜ ያበረታታናል ፣ ያጽናናላንም፣ ሁል ጊዜም ተስፋችንን ያለመልማል። የእግዚአብሔር ድምፅ አድማሳዊ ገጽታ አለው፣ በተቃራኒው ደግሞ ክፉ የሆነ ድምጽ ወደ ግድግዳ ይወስደናል፣ ወደ ጥግ እንድናመራ ያደርገናል።

ሌላም ልዩነት አላቸው። የጠላት ድምፅ አሁን ያለንን ትኩረታችንን የሚከፋፍል እና ለወደፊቱ ወይም ላለፉ ነገሮች እንድንጨነቅ፣ እንድንፈራ እና ሐዘን ውስጥ እንድንገባ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንድናተኩር ይፈልጋል።  ጠላት አሁናዊ ወይም ወቅታዊ የሆኑ ነገሮችን አይፈልግም፣ - - መራራ የነበሩ ጊዜያትን፣ ስህተት የሰራንባቸውን ወቅቶች፣ የጎዳናቸውን ሰዎች ... ወዘተ ብዙ መጥፎ ትዝታዎች በውስጣችን እንዲቀሰቀሱ ያደርጋል። በምትኩ የእግዚአብሔር ድምጽ ወቅታዊ የሆኑ ነገሮችን ይናገራል፣ “አሁን ጥሩ ማድረግ ትችላላችሁ ፣ አሁን ፍቅርን መለማመድ ትችላላችሁ ፣ አሁን ልባችሁን እስረኛ አድርገው የያዙትን ፀፀቶች እና ቁጭቶች መተው ትችላላችሁ” በማለት ያበረታታናል። እኛን ይቀሰቅሰናል ፣ ወደፊት እንድናመራ ያደርገናል፣ የሚናገረው አሁን እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ነው።

እንደገና-ሁለቱ ድምጾች በእኛ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋሉ። ከእግዚአብሔር የሚመጣው ድምጽ “ለእኔ መልካም የሆነው ነገር ምንድነው?” የሚል ድምጽ ይሆናል።  ይልቁንም የፈታኙ ድምጽ ግን “እኔ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” የሚል ጥያቄ በውስጣችን እንዲነሳ ያደርጋል። ለእኔ የሚያስፈልገኝ ምንድነው? የሚሉ ጥያቀዎችን ክፉ የሆነው ድምጽ ሁልጊዜ በራሳችን ዙሪያ ላይ፣ በራሳችን ፍላጎቶች ላይ፣ ሁሉንም ነገር በፍጥነት ማከናውን እንደ ሚገባን ይመክረናል። እንደ አንዳንድ ብልጣብልጥ ሕጻናት ልጆች ሁሉም ነገር አሁን እንዲደረግለት ይፈልጋል። የእግዚአብሔር ድምፅ ግን በዝቅተኛ ዋጋ ደስታን እንድናገኝ በጭራሽ አያደርግም፣  እውነተኛውን ሰላም ለማግኘት ከፈለግን እኔ ከሚለው መንፈስ ባሻገር እንድንሄድ ይጋብዘናል። አስታውሱ ክፋት በጭራሽ ሰላም አይሰጥም ፣ አስቀድሞ ቂምን ያስባል እና ከእዚያም በኋላ ምሬትን ያስከትላል።  ይህ የክፋት ዘዴ ነው።

በመጨረሻም የእግዚአብሔር እና የፈታኙ የዲያቢሎስ ድምጽ በተለያዩ “ሁኔታዎች” ውስጥ ሁነው ይናገራሉ፣ - ጠላት ጨለማን ፣ ውሸትን ፣ ሐሜትን ይወዳል። ጌታ የፀሐይ ብርሃንን ፣ እውነትን ፣ ቅንነትን እና  ግልፅነትን ይወዳል። ጠላት “ራስህን በራስህ ቆልፈህ ዝግ ሁን፣ ስለዚህ ማንም ሊረዳህና ሊያዳምጥህ አይችልም ፣ ማንንም አትመን!” ይለናል። በተቃራኒው መልካሙ ድምጽ ራሳችንን ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች በግልፅነት እና በራስ መተማመን እንድንከፍተው ይጋብዘናል። ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ በዚህ ጊዜ ብዙ ሀሳቦች እና ጭንቀቶች ውስጥ እንደ ገባን ይታወቃል። ወደ ልባችን በመምጣት ላይ ለሚገኙትን ድምጾች በትኩረት እንከታተላቸው።  ከየት እንደመጡ እንጠይቅ። የራስ ወዳድነት ከሚንጸባረቅባቸው ስፍራዎች የሚያወጣንና ወደ እውነተኛ በነፃነት የተሞላ የግጦሽ ስፍራ የሚወስደንን የመልካሙን እረኛ ድምጽ ለመለየት እና ለመከተል ጸጋን እንጠይቅ። የመልካም ምክር እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትመራን እና አብራን እንድትጓዝ ማሰተዋልን እንድታሰጠን አማላጅነቷን እንማጸን።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 May 2020, 18:57