ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የዕርገት በዓል ኢየሱስ በመካከላችን በቀጣይነት እንደ ሚኖር ያስታውሳል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በግንቦት 16/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ በዕለቱ በተነበበውና “ከዚያም ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ። ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡ 16-20) በማለት ኢየሱስ ታላቁን ተልእኮ ለሐዋርያቱ በሰጠበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “የዕርገት በዓል ኢየሱስ በመካከላችን በቀጣይነት እንደ ሚኖር ያስታውሳል” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ

ኩቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮቻን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ በጣሊያን እና በሌሎችም ሀገሮች የጌታ እርገት በዓል  መታሰቢያ ይከበራል። በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ማቴዎስ 28፡16-20) በገሊል የተሰበሰቡትን ሐዋርያት በመግለጽ “ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ መሄዳቸውን” (ማቴ 28፡16) ይገልጻል።  ከሙታን የተነሳው ጌታ ለመጨረሻ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር በዚህያ ተራራማ ስፍራ ይገናኛል። “ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ ሰብኳል” (ማቴ 5፡ 1-12)፣ “ኢየሱስ ለመጸለይ ወደ ተራራ እንደ ወጣ” (ማቴ. 14፡23)፣ “እዚያም በተራራ ላይ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ተቀብሎ ማስተማሩን እና በሽተኞችን ፈወሱን” (ማቴ 15፡29) ቅዱስ ወንጌል ይገልጽልናል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ በተራራው ላይ ፣ ከእንግዲህ ተአምራትን የሚያከናውን እና የሚያስተምር ጌታ ራሱ አይሆንም ፣ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ሥራውን እንዲቀጥሉ ኋላፊነት ይሰጣቸዋል፣  ደቀ መዛሙርቱ እርምጃ እንዲወስዱ እና እርሱን በዓለም ውስጥ እንዲያውጁ ኃላፊነት ሰጥቶ ይልካቸዋል።

እሱ ተልእኮውን ለሁሉም ሰዎች በመስጠት ተልእኮው እንዲስፋፋ ያደርጋል። እርሱም “ስለዚህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” (ማቴ 28፡19-20) በማለት ይልካቸዋል። ለሐዋሪያት የተሰጠው ተልእኮ ይዘቶች እነዚህ ናቸው- ማወጅ፣ ማጥመቅ፣ ማስተማር እና ጌታቸው ባሳያቸው መንገድ ላይ መጓዝ፣ ይህም ማለት ሕያው የሆነ ወንጌል መኖርን ያካትታል። ይህ የመዳን መልእክት የሚያመለክተው በመጀመሪያ የምሥክርነትን ግዴታ ነው - ያለ ምስክርነት ማወጅ አይቻልም - የዛሬዎቹ ደቀ መዛሙርት የሆንን እኛ በእምነታችን ምክንያት ተጠርተናል። እንዲህ ዓይነቱን በጣም ከባድ የሆነ ሥራ እየተጋፈጥን እና ስለ ድክመቶቻችን በማሰብ ሐዋርያት ራሳቸው ተሰምቷቸው እንደ ነበረ ዓይነት እኛም ለዚህ አገልግሎት ብቁ እንዳልሆንን ይሰማናል። እኛ ግን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ኢየሱስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ (ማቴ 28፡20) በማለት የተናገራቸውን ቃላት በማስታወስ ተስፋ መቁረጥ የለብንም።

ይህ ቃል ኪዳን በመካከላችን ኢየሱስ በማያቋርጥ መልኩ እንደሚኖር እና እንደ ሚያጽናናን ያረጋግጣል። ነገር ግን ይህ እርሱ ከእኛ ጋር መገኘቱን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? እንደ እያንዳንዱ ሰው የመንገድ ላይ ተጓዳኝ በመሆን በታሪክ ሂደት ውስጥ በጽናት እንድትራመድ ቤተክርስቲያኑን በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። በክርስቶስ እና በአባቱ የተላከው መንፈስ ቅዱስ፣ የኃጢያት ስርየት እንዲኖር የሚሰራ እና የተጸጸቱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ በማደረግ በእርሱ በመተማመን ለጸጋው ራሳቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ይጋብዛቸዋል። እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ከእኛ ጋር እንደሚቆይ በተስፋ ቃል ፣ ከሙታን የተነሳው ኢየሱስ በዓለም ውስጥ መገኘቱን እንደሚቀጥል ያሳየናል። ኢየሱስ በዓለም ውስጥ ይገኛል፣ ነገር ግን የሚገኘው በተለየ ዘይቤ ነው፣ በትንሳኤው ዘይቤ፣ ማለትም በቃሉ የሚገልጽ፣ በቅዱሳን ምስጢራት ውስጥ በመገለጽ፣ በመንፈስ ቅዱስ ቋሚ እና ውስጣዊ ተግባር የተገለጠ መገኘቱን ይቀጥላል።የእርገት በዓል እንደሚነግረን ኢየሱስ ፣ ምንም እንኳን በአባቱ ቀኝ ሆኖ በክብር ለመኖር ወደ ሰማይ የወጣ ቢሆንም አሁንም በመካከላችን እንዳለ ይገልጽልናል፣ የእኛ ኃይል፣ የእኛ ትጋት እና የእኛ ደስታ የሚምነጨው ከዚሁ ነው፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእኛ መካከል ይገኛል።

በእናትነት ጥበቃዋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጉዞዋችን ትርዳን፣ - ከእርሷ ከሙታን የተነሳው ጌታ በዓለም ውስጥ ምስክር የመሆንን ጣፋጭነት እና ድፍረትን እንማራለን።

24 May 2020, 09:17