ፈልግ

ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ተልዕኮ ቀን እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በቫቲካን በተከበረበት ወቅት ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ተልዕኮ ቀን እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም በቫቲካን በተከበረበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ ተልእኮ የሥልጠና ውጤት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 13/2012 ዓ.ም የመንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራት የሚያከናውኑ መንፈሳዊ ማሕበራት በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባሳተላለፉት መልዕክት  መንፈሳዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው ማህበራት - ራሳቸውን ማስተዋወቅ እና የራሳቸውን ተነሳሽነት የሚገልጹ ተግባራትን ለሕዝቡ ከማስተዋወቅ ተቆጥበው ሚስዮናዊ መሆን በነጻ የተሰጠን ስጦታ በመሆኑ የተነሳ በምስጋ መንፈስ የምናጸባርቀው ተግባር መሆኑን ተረድተው ተልእኮ የሥልጠና ውጤት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና

ቅዱስ ወንጌልን ማወጅ ማለት እኛ የምናከናውነውን “ማንኛውም የፖለቲካ ወይም ባህላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ ወይም ሀይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ሰዎች እንዲከተሉ ከማድረግ ተግባር እጅግ የተለየ ነው” በማለት በመልዕክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው መንፈሳዊ ተልእኮው የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ ሲሆን “የሥልጠና ትምህርቶችን በመስጠት ላይ ያተኮረ፣ ወይም በማስታወቂያ ሥራ ላይ የተጠመደ እና የራሳችንን ተነሳሽነት ለማሳደግ ወደ አእምሮው የሚመጡ“ የቤተ-ክርስቲያን ሥርዓቶች ” በመጠቀም የሚደረጉ ተግባራት ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደማይገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው  ገልጸዋል። መንፈሳዊ ተልዕኮ የራሳችንን ተነሳሽነት እና ራሳችንን የምናስተዋውቅበት አጋጣሚ ሳይሆን ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የተልዕኮ ዋና ተዋናይ እንዲሆን በአደራ የሰጠንን ኢየሱስን መመስከር ላይ ያተኮረ ተግባር መፈጸም ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚሁ የመንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራትን  የሚያከናውኑ መንፈሳዊ ማሕበራት በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባሳተላለፉት መልዕክት የክርስትና እምነት መሰረታዊ ተልዕኮ ምን እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ይህ መንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራትን የሚያከናውኑ ማሕበራትን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ከእዚህ ቀደም አውጥቶት በነበረው የሥራ መረዓ ግብር መሰረት በግንቦት 13/2012 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ስብሰባ በሮም እንዲካሄድ እቅድ ይዞ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በእዚህ ስብሰባ ላይ የክርስቲያኖች ተልዕኮ ዋና ዓላማ እና መሰረት ላይ ትኩረቱን በማደረግ ሊካሄድ የነበረ ስብሰባ ነበር፣  ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስብሰባ ወደ ሌላ ጊዜ መዛወሩ ተገልጿል።

የተልእኮው መሠረቶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመልዕክታቸው የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ “በጣም ቅርብ የሆነ ዘረ-መል (ባህርይ)” መሰረቱን ያደርገው “በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ እንጂ የእኛ አስተሳሰባችን እና ምኞቶቻችን ውጤት አይደለም” ብለዋል። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሆነውን  ደስታ መቀበል “ጸጋ” ነው እናም “ቅዱስ ወንጌልን ለመስበክ የሚያስችለን ብቸኛው ብርታት” የሚሰጠን ይህ ጸጋ ነው ብለዋል። ደኅንነት “የሚስዮናዊነት ተነሳሽነታችን ውጤት ፣ ወይም ቃል እንዴት ሥጋ እንደ ሆነ በማብራራት የምናደርጋቸው ንግግሮች ውጤት አይደለም” በማለት በመልዕክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ደኅንነት ሊከሰት የሚችለው ከእርሱ እኛን ከሚጠርና ጌታ ጋር ስንገናኝ ብቻ ነው፣ ስለሆነም የዚህ ውጤት እና ዳግም መገለጽ የሚሰጠን ደስታ እና ምስጋና ውጤት ነው ብለዋል። አንድ ሰው ቅዱስ ወንጌልን እየመሰከረ ነው ልንል የምንችለው ስለራሱ ሳይሆን ስለሌላው ይህንን ተልዕኮ ስለሰጠው ጌታ ሲመሰክር ብቻ ነው ብለዋል።

ልዩ ባሕሪዎች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክታቸውን ሲቀጥሉ እ.አ.አ በ2013 ዓ.ም እርሳቸው በላቲን ቋንቋ “Evangelii gaudium” በአማርኛው “በወንጌል የሚገኝ ደስታ” በሚል አርዕስት ለንባብ አብቅተው ከነበረው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ የአንድ መንፈሳዊ ተልእኮ ልዩ ገጽታዎች በመልዕክታቸው አብራርተዋል።

ሰዎችን የመሳብ ችሎታ

“በመጀመርያ የምትማርክ ወይም ሰዎችን መሳብ የምትችል ቤተክርስቲያን መሆን፣ ቤተክርስቲያኗ ማደግ የሚገባት በዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመሳብ እንጂ ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንዲቀይሩ በማድረግ አይደለም፣  እናም ኢየሱስን በደስታ የምትከተል ቤተክርስቲያን ከሆነች ሌሎችን ወደ ራሷ መሳብ ትችላለች፣ ሰዎች በዚህ ተግባሯ ይገረማሉ፣ ይሳባሉም” ብለዋል።

ምስጋና እና ቸርነት

“ቤተክርስቲያን በምስጋና መንፈስ የተሞላች እና በነጻ የተቀበለችሁን በነጻ የምትሰጥ ቸር ልትሆን ይገባታል” በማለት በመልዕክታቸው ሁለተኛውን የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ልዩ ባህሪይ የገለጹት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም “የሚስዮናዊነት ተነሳሽነት በምክንያት ላይ የተመሰረተ ወይም በስሌት ውጤት በጭራሽ ሊገኝ ስለማይችል” ወይም በዚህ ስሜት ውስጥ ግዴታ ስለሚኖር በዚህ የተነሳ ቤተክርስቲያን “የምስጋና ነፀብራቅ” ልትሆን ስለማትችል የቸርነት ተግባሯን ልትቀጥል ስለምትቸገር ነው ብለዋል። “ከዚያ በመቀጠል ትህትና አለ ፣ ምክንያቱም ደስታ እና ድኅንነት ‘የእኛ ንብረት ስላልሆኑ ነው፣ ወይም በእኛ ጥረት የሚገኙ ነገሮች ባለመሆናቸው የተነሳ ነው፣ ቅዱስ ወንጌሉ ሊታወጅ የሚገባው ያለትዕቢት በትህትና ሊሆን የገባዋል’” ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን በማብሰር ሂደት ውስጥ ልትከተላቸው ከሚገባቸው በህሪያት መካከል ነገሮችን ከማወሳሰብ ይልቅ ሕዝቡ በቀላሉ ይረዳ ዘንድ ማመቻቸት እንደ ሚገባት የገለጹ ሲሆን የተወሳሰቡ ነገሮችን ማቅረብ ሕዝቡ እጅግ በጣም ግልጽ የሆነውን ኢየሱስን ውስብስብ በሆነ መልኩ እንዲረዳው ማደረግ ተገቢ እንዳልሆነ ጨምረው ገልጸዋል።  ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ይህንን ሐሳባቸውን በይበልጥ ለማስረዳት በማሰብ ጨምረው እንደ ገለጹት  ትክክለኛ የሆነ መንፈሳዊ ተልእኮ በሕይወት ጫና ምክንያት ቀድሞውኑ የደከሙ ሰዎች ላይ “ከንቱ ሸክም” መጨመርን አያካትትም ፣ ወይም ጌታ በቀላሉ የሚሰጠንን ደስታ ለማግኘት “የተራቀቁ እና አድካሚ የሥልጠና መንገዶችን” መጠቀም አያስገድድም ብለዋል።

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ሊያካትታቸው ከሚገባው ባሕሪያት መካከል ሌሎች ሁለት ልዩ ባህሪያት ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለሕዝቡ ሕይወት ቅርብ መሆን እና ይህን ተጨባጭ በሆነ መልኩ መግለጽ እንደ ሆነ በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱንሰታቸው ምክንያቱም መንፈሳዊ ተልእኮው “ሰዎች ባሉበት ስፍራ እና ባሉበት ሁኔታ” ተደራሽ መሆን እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ “የስሜት ህዋስ እምነት ነው”  እናም ለታናናሾች እና ለድሆች ቅርብ መሆን “ለቤተክርስቲያኗ አማራጭ ሳይሆን መንፈሳዊ ግዴታ ነው” ብለዋል።

ልናዳብራቸው የሚገባን ችሎታዎች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራትን የሚያከናውኑ ማሕበራትን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ያስተላለፉትን መልእክት በቀጠሉበት ወቅት ሲገልጹ የወደፊቱን እጣ ፈንታ መንፈሳዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው ሚስዮናዊያን ማሕበራት “በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በቀጣይነት ከሚወለዱ ሰዎች እምነት ነው” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህ የተነሳ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ስሜት ቅርብ የሆነ ምስክርነት ሊሰጡ እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።

ማስወገድ የሚገባን ጉድለቶች

በመቀጠልም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራት የሚፈጽሙ ማሕበራትን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተልዕኮ መንገድ ላይ የሚንጠለጠሉ በሽታዎችን ይዘረዝራሉ። የመጀመሪያው ራስን ማስተዋወቅ ነው፣ ራስን ማስተዋወቅ በትኩረት የመከታተል እና የእራሱን ተነሳሽነት በማስታወቂያ መልክ የማቅረብ አደጋ አለ ብለዋል። ከዚያ የትዕዛዝ ጭንቀት አለ ፣ ማለትም እነዚህ አካላት ሊያገለግሉዏቸው የሚገቡትን ማህበራት  የመቆጣጠር ተግባሮችን የመጠቀም የይገባኛል ጥያቄ አለ ብለዋል።  አሁንም ቢሆን  የቅንጦት  ሂደት አለ ፣ ያም “የበላይ ተቆጣጣሪ አካል እኔ ነኝ” ብሎ የማመን ሃሳብ “የከፍተኛ ባለሞያዎች ቡድን” አባል የመሆን ፈተና እንዳለ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “የእምነቱ እርግጠኛነት አሳማኝ ንግግር ወይም የሥልጠና ዘዴዎች” ውጤት እንደ ሆነ አድረግው እንደ ሚቆጥሩ በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው “ውስጠ-ብዙ ፣ እንደገና መነቃቃት እና መተባበር ያለበት” ከሕዝቡ ያልተነጠለ ምክር ቤት እንዲሆን ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።  ሌሎች ጉድለቶች ደግሞ ማራኪ ሆኖ ለመታየት የሚደረግ ጥረት እና የሥራ ሂደቱን በሚገባ በማስኬድ ላይ ያተኮረ ምክር ቤት ሆኖ ለመታየት እንደ ሚሞክር የገለጹ ሲሆን ይህም ደግሞ ሁሉም ነገር “በዓለም ውጤታማነት ሞዴሎች ምሳሌ” ላይ ያተኮረ ስለሚሆን ነው ብለዋል።

ለጉዞ ጠቃሚ ምክሮች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “በሰዎች እውነተኛ ሕይወት ውስጥ በቀጣይነት በሀገረ ስብከት፣ በቁምስናዎች፣ የሕብረተሰብና የቡድን ማኅበረሰብ አባል በመሆን ከቤተክርስቲያኒቷ በተቆራኘ መልኩ ተግባራቸውን ማከናወን እንደ ሚገባቸው መንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራትን የሚያከናውኑ ማሕበራትን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ያሳሰቡ ሲሆን ከሕዝቡ ጋር በፀሎት መንፈስ እና ለዚህ መንፈሳዊ ተልእኮ ግብዓት የሚሆን ሐብት በማሰባሰብ ከሕዝቡ ሕይወት ጋር ቅርብ የሆነ ሕይወት ሊኖረው እንደ ሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን እንዲሁም አዲስ የመንፈሳዊ ተልእኮ መንገዶችን መክፈት እንደ ሚገባ፣ ነገር ግን “ቀላል የሆነውን ነገር ሳያወሳስቡ” ቅዱስ ወንጌልን በታላቅ ፍቅር መስበክ እንደ ሚገባ ገልጸዋል።

ልገሳ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፈራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ መንፈሳዊ ተልዕኮን ለማስፈጸም የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የሚያስችል የገንዘብ የማሰባሰብ ሂደት ሙሉ በሙሉ ትኩረት ተሰጥቶት እንደ አንደ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እጅግ በጣም ትኩረት ተሰጥቶት ሊከናወን የሚገባው ጉዳይ ሊሆን እንደ ማይገባው በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከናወነው ሐብት የማሰባሰብ ተግባር ካልተሳካ ታላላቅ ለጋሾችን በመፈለግ ችግሩን ለመሸፈን መሞከር የለበትም ብለዋል። በአመት አንዴ በጥቅምት ወር “የዓለም የተልእኮ ቀን”  ላይ ለዓለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮ የሚሆን ገንዘብ የማሰባሰብ ሂደት  “በዋነኝነት ለተጠመቁ ሰዎች ሁሉ ወደ ተግባር ተለውጠው መመለሳቸውን” ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደ ሆነ ገልጸው በዚህ ምክንያት በሁሉም ሀገሮች አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሐብት በማሰባሰብ ሁኔታ ላይ ትኩረት ማድረጉ መልካም እንደ ሆነ፤ የተሰበሰበውን ገንዘብ በመጠቀም ፣ በቤተክርስቲያንም ውስጥ “የጥገኛነት” አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ የደህነት ዓይነቶችን በማስወገድ የኅብረተሰቡን ዋና ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ድሆችን መርሳት የለብንም ያሉ ሲሆን መንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባራት የሚፈጽሙ ማሕበራትን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ በመጠየቅ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።

21 May 2020, 20:13