ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የመቁጠሪያ ጸሎት ሲደግሙ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የመቁጠሪያ ጸሎት ሲደግሙ። 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ የመቁጠሪያ ጸሎት በመጸለይ ለማርያም ያለንን መንፍሳዊ ቅርበት እናሳድግ አሉ!

በዓለማቀፋዊቷ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት የግንቦት ወር “የማርያም ወር” ተብሎ እደሚጠራ ይታወቃል። ይህ የግንቦት ወር በወር ደረጃ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “የማሪያም ወር” በመባል የሚታወቅ ወር ሲሆን የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበረስብ ክፍሎች ዘንድ  በመጪው ቅዳሜ እ.አ.አ ግንቦት 30/2020 ዓ.ም በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 12፡30 ላይ ቫቲካንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የሚጠሩ ቤተመቅደሶች በተጠቀሰው ሰዓት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሚሳተፉበት የመቁጠሪያ ጸሎት እንደ ሚደረግ ተገልጿል። በዚህ የመቁጠሪያ ጽሎት ላይ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እያሸበረ እና በፍጥነት እየተቀጣጠለ የሚገኙውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይወገድ ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት የምንማጸንበት የጽሎት ቀን እንዲሆን በቫቲካን መወሰኑ ይታወሳል።

የቫቲካን ዜና

ይህ የግንቦት ወር በወር ደረጃ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “የማሪያም ወር” በመባል የሚታወቅ እንደ ሆነ ቀድም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በዚህ የግንቦት ወር ውስጥ የክርስቶስ፣ የቤተክርስቲያን፣ የምዕመናን እናት ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለየት ባለ መልኩ ጸሎት የሚደርግበት፣ አማልጅነቷን የምንማጸንበት፣ በተለይም ደግሞ በውስጣችን፣ በቤተሰባችን፣ በማኅበረሳባችን፣ በአገራችን እና በአጠቃላይ በዓለም ውስጥ የጥል እና የክርክር ግድግዳ ተደርምሶ በምትኩ የሰላም እና የብልጽግና መንፈስ ይወርድ ዘንድ በእርሷ አማካይነት ወደ ልጇ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመማጸኛ ጸሎት እንድታቀርብልን እርሷን በተለየ ሁኔታ በመቁጠሪያ ጸሎት አማልጅነቷን የምንማጸንበት ወር ነው የግንቦት ወር።

በዚህ የማርያም ወር በመባል በሚታወቀው የግንቦት ወር ውስጥ ለሰላም፣ ለእርቅ፣ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንችል ዘንድ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን እያጋጠማት ካለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያበቃ ዘንድ ለየት ባለ መልኩ ጸሎት የምናደርግበት ወር ሲሆን ምንም እንኳን ጸሎት አንድ ክርስቲያን ከውልደቱ እስከ ሕልፈቱ ድረስ በእየለቱ ሊያደርገው የሚገባው መንፈሳዊ ተግባር መሆኑ እና ጸሎት ማብቂያ የሌለው መንፈሳዊ ምግባችን መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን በእዚህ የግንቦት ወር የማሪያም ወር ተብሎ በመጠራቱ የተነሳ ለየት ባለ መልኩ የመቁጠሪያ ጸሎት የሚደርግበት ወር በመሆኑ የግንቦት ወርን ለየት ያደርገዋል።

በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 1፡39-56 ላይ እንደ ተጠቀሰው ማርያም “በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”በማለት ኤልሳቤጥ ማሪያምን በታላቅ ደስታ በቤቷ የተቀበልችበት በዓል ነው።

እነዚህ ሁለት ሴቶች ማለትም ማሪያም እና ኤልሳቤጥ በዝምድና የተሳሰሩ ቢሆኑም ነገር ግን በእድሜ፣ በባሕሪይ፣ በአከባቢያዊ ሁኔታ የተለያየ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ሴቶች ማሪያም እና ኤልሳቤጥ የየራሳቸው የሆነ የግል ምስጢር ደብቀው የያዙ ሴቶች ነበሩ። የማሪያምን ጉዳይ በምንመለከትበት ወቅት ማሪያም የዩሴፍ እጮኛ የነበረች ሴት እንደ ነበረች የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን መልኣኩ ገብርኤል ከእግዚኣብሔር ተልእኮ የምስራቹን ቃል ካበሰራት በኃላ በሰው ሳይሆን “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አርግዛ” በመገኘቷ ይህ ሁኔታ ደግሞ በወቅቱ በነበረው የማኅበርሰብ ክፍል አንድ ከትዳር ውጭ ያረገዘች ሴት በድንጋይ ተወግራ ትሙት የሚል ሕግ በመኖሩ የተነስ ተጨንቃ ነበር፣ እግዚኣብሔር በመንፈስ ቅድስ አማካይነት በእርሷ ማደሩን በወቅቱ እርሷ ይህንን ጉዳይ ለሌሎች ማስረዳት የከበዳት ጉዳይ ነበር፣ በእዚህም ምክንያት ሁሉንም ነገር በልቧ እያሰላሰልች ይዛው ቆይታ ነበር።

ኤልሳቤጥም በበኩሉዋ “አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ በማለት ምስቱ ኤልሳቤጥ በእስተ እርጅና ወንድ ልጅ እንደ ምትወልድ ባበሰረው መሰረቱ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ታረግዛለች” (ሉቃስ 1፡8-)። ነገር ግን ኤልሳቤጥ በእስተርጅና እድሜዋ በገፋበት ወቅት ማርገዟ ከፍተኛ የሆነ ምስጢር ሆኖባት ነበር።

ስለዚህ እነዚህ ሁለት ሴቶች የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር በውስጣቸው ደብቀው የያዙት አንድ ምስጢር መኖሩ፣ ሁለቱም አንድ ወንድ ልጅ እንደ ሚወልዱ እየተጠባበቁ መሆናቸው እና ሁለቱንም ያበሰረው ደግሞ መልኣኩ ገብርኤል መሆኑ ያመሳስላቸዋል።

በዚህ አጋጣሚ ይህንን ማሪያም ኤልሳቤጥን ለመጎብኘት የሄደችበት ቀን በምንዘክርበት በዛሬው ቀን  “ልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” (ሉቃስ 1:41-43) በማለት ገና በማሕጸኑዋ ውስጥ ያለውን ሕጻኑን ኢየሱስን እንዳመስገነች ሁሉ፣ እኛም ማሪያም ልባችንን፣ ቤተሰባችንን፣ ሀገራችንን እና እንዲሁም ዓለማችንን እንድትጎበኝ እና በደስታ እና በሰላም፣ በመንፈስ የተሞላን ሆነን እንኖር ዘንድ እንድተረዳን በሕይወታችን ውስጥ ልንጋብዛት ያስፈልጋል ለማለት እንወዳለን።

26 May 2020, 12:24