ፈልግ

“በልዩነት መካከል የሚገኝ አንድነት” “በልዩነት መካከል የሚገኝ አንድነት”  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እውነተኛ ማኅበራዊ ግንኙነት አንድነትን የሚያሳድግ መሆን አለበት ብለዋል።

በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ስር የሚገኝ አሳታሚ ድርጅት “በልዩነት መካከል የሚገኝ አንድነት” የሚል አርዕስት ያለው አዲስ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ታውቋል። መጽሐፉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእግዚአብሔር አምሳል በተፈጠሩት ሰዎች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነትን በሚመለከቱ የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ያቀረቧቸውን አስተምህሮችን እና ንግግሮችን እና ከዚህ በፊት ያልታተሙ ርዕሠ ጉዳዮን ያካተተ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። በመጽሐፉ መቅድም ላይ የዓለም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሕብረት መሪ የሆኑት፣ የካተርቨሪውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ አጭር መልዕክት የታከለበት መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

“በልዩነት መካከል የሚገኝ አንድነት” በሚል አርዕስት የታተመው አዲሱ መጽሐፍ ከዚህ በፊት ታትመው ለንባብ የበቁ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮች ቀጣይ መልዕክቶችን፣ አስተምህሮችን እና በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙት በስፋት የተመለከተ መሆኑ ታውቋል። የዓለም አንግሊካን ቤተክርስቲያን ሕብረት መሪ እና የካተርቨሪውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ባቀረቡት መልዕክታቸው “በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሜ የሆኑት ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር ወደሚጠራን የፍቅር እና የምሕረት መንገድ እንድንመለስ ግብዣቸውን አቅርበዋል ብለው፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያዘጋጀው የፍቅር እና የምሕረት መንገድ በመካከላችን ወንድማማችነትን እንድናሳድግ የሚጋብዝ ነው ብለው፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮዎች ብዙ ነገሮችን በጋራ መማር ይቻላል ብለዋል።

ኢየሱስን መመልከት ያስፈልጋል፣

“በልዩነት መካከል አንድነት” በሚል አስርዕስት የታተመው መጽሐፍ ክርስትያን ማኅበረሰብ በአንድነት ወደ ኢየሱስ በመቅረብ የእርሱን የምህረት ፊቱን መመልከት እንደሚያስፈልግ፣ ሐዋርያው ማርቆስ በጻፈው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ሐብታሙ ሰው ወደ ኢየሱስ ዘንድ ቀርቦ “ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመውረስ ማን ማድረግ ይኖርብኛል”? በሚለው ጥያቄ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። ይህን የወንጌል ክፍል በመጥቀስ አስተንትኖአቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “የዘለዓለማዊ ሕይወት ለመውረስ ማን ማድረግ ይኖርብኛል”? በማለት ጥያቄን ያቀረበውን ሃብታም በምሕረት ዓይኖቹ ተመልክቶት ፍቅሩን የገለጸለት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ በፊት ትኩረቱን የጣለው በጥያቄው ሳይሆን በሰውየው ማንነት እንደሆን አስረድተው፣ ይህም ለእውነተኛ ሰብዓዊ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፣ ይህ ብቻም ሳይሆን ከዓለማችን እና ከተለያዩ ሕዝቦች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ባልንጀራችንን ማን እንደሆነ ማሰብ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር ሰብዓዊ ግንኙነት ፍሬያማ ሊሆን አይችልም ብለው፣ ልባችንን ለባልንጀራ በመክፈት፣ በመካከላችን እና በሌሎች ሰዎች መካከል ያለውን የአንድነት ትርጉም ማወቅ እንችላለን ብለዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት መልዕክት መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን በሰዎች መካከል አንድነትን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

ልብን ለሌሎች ክፍት ማድረግ፣

ልብን ለሌሎች ክፍት በማድረግ የሚደረግ ማኅበራዊ ግንኙነት ለተለያዩ አደጋዎች የሚያጋልጥ ቢሆንም የራሳችንን ማንነት ለማወቅ እና የሌላውን ወገን አቋም በማወቅ ከልብ እንድናዳምጥ ይረዳል ብለዋል። የሁለት ወገን ውጤታማ ውይይት የራስን ማንነት እንድናውቅ ከማገዙ በተጨማሪ የሌሎችንም ማንነት እና ነጻነት ለማወቅ እንደሚያግዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። ቅዱስ ጆን ሄንሪ ኒውማን፣ ሰዎች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ንግግር፣ አስፈላጊ ቢሆንም እውነትን በመናገር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ልብን ክፍት አድርጎ በመቅረብ የወሰናል ማለታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም ማኅበራዊ ግንኙነት የሚወሰነው ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማድረግ ፈቃደኛ በሚሆኑት ሰዎች የሚወሰን ቢሆንም፣ ይህ መልካም ፈቃድ በድፍረት በመታገዝ ለውጥን ለማምጣት የተዘጋጀ መሆን አለበት ብለዋል።

የነጻነት ጥቅም፣

ሐዋርያው ማርቆስ በጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ላይ የተጻፈውን የሃብታሙን ሰው ታሪክ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሃብታሙ ወጣት ብዙ ሃብት ስለነበረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ቤቱ በሐዘን መመልሱን አስታውሰው ያዘነውም የሃብት ተግዥ በመሆን፣ ነጻ መሆን ስላልቻለ ነው ብለዋል። ነጻነት በምድራዊ ሕይወትን ውስጥ የምናደርገዋን ግንኙነት ሰብዓዊነትን እንዲላበስ ያደርገዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ያለ ሙሉ ነጻነት እውነት የለም ብለው፣ ያለ ነጻነት የሚደረግ ግንኙነት ልበ ወለድ እና ግብዝነት ያለበት ግንኙነት ይሆናል ብለዋል።

የሃብታሙ ወጣት የመዳን ዕድሉ ሙሉ በሙሉ አላለቀም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “ታዲያ ማነው ሊድን የሚችለው”? ብለው በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ፣ ለሰው ልጅ የማይቻል ለእግዚአብሔር ይቻለዋል ማለቱን አስታውሰው ይህም እግዚአብሔር በጸሎታችን አማካይነት ከእኛ ጋር እንዲሆን ዕድል መስጠት ያስፈልጋል ብለው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዓይኑ የሚመለከታቸው ከእርሱ ጋር የሚነጋገሩትን ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተንተኖአቸውን ሲያጠቃልሉ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲገኝ በጸሎት ጠይቀው፣ ከሌሎች ጋር ሕብረትን ስንፈጥር፣ ግንኙነትንም ስንጀምር፣ እስከ መጨረሻው ራሱን በለጋስነት እና በፍቅር አሳልፎ እንደሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

25 May 2020, 18:09