ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለግንቦት ወር ያዘጋጁትን የጸሎት ሃሳብ ይፋ አደረጉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለግንቦት ወር እንዲሆን ብለው በላኩት የጸሎት ሃሳብ ዲያቆናት ቤተክርስቲያንን በማገልገል የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 5/2020 ዓ. ም. ለመላው ምዕመናን በላኩት የቪዲዮ መልዕክት ለዲያቆናት ጸሎት እንድናደርግ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በግንቦት ወር መልዕክታቸው፣ ተሐድሶ ላይ በሚገኝ ዓለማችን ዲያቆናት ቤተክርስቲያንን በማገልገል እና በመጠበቅ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በትጋት ማበርከት እንዲችሉ በጸሎታችን እንድናግዛቸው አደራ ብለው ዲያቆናት ለመላዋ ቤተክርስቲያን አበራታች ምልክቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ምእመናን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚያቀርቡባቸው ሦስት የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ማዕረጎች መኖራቸው ሲታወቅ እነርሱም የጵጵስና፣ የክህነት እና የድቁና ማዕረጎች መሆናቸው ይታወቃል። ከእነዚህ የቤተክርስቲያን ማዕረጎች መካከል ዲያቆናት የኢየሱስ ክርስቶስን የአገልግሎት ተልዕኮ እና ጸጋ በልዩ ሁኔታ የሚካፈሉ መሆናቸው ታውቋል። የክህነት ምስጢር ለዲያቆናት የማይሻር የአገልግሎት ጸጋን በማልበስ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማስተባበር፣ የእርሱን የአገልግሎት ተልዕኮ እንዲጋሩ የሚያደርጋቸው መሆኑ ይታወቃል። ዲያቆናት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል የተቀቡ፣ አገልጋይ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌዎች መሆናቸው ይታወቃል። በእርግጥም በግሪክ ቋንቋ “ዲያኮኒያ” የሚለው ቃል ትርጉሙ፥ አገልግሎት ማለት ሲሆን ይህ ማለት ዲያቆናት የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝበ ክርስቲያን በማሰማት፣ ሥርዓተ አምልኮ ሥነ ሥርዓቶችን በማገዝ እና በማኅበረሰብ መካከል የተቸገሩትን እና እጅግ የደሄዩትን መርዳት ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑ ይታወቃል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት “ዲያቆናት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ የሚታይባቸውን ድሆች ለማገልገል እና ለመርዳት ራሳቸውን ዝግጁ ያደረጉ ናቸው” ማለታቸው ታውቋል።  

ካህናት የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ እንዲያገለግሉት የድቁና ማዕረግ ጭምር የተሰጣቸው መሆኑን ብዙ ሰው አያስተውለውም ያለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፣ ቋሚ ዲያቆናት የጋብቻን ሕይወት እየኖሩ፣ የተጠሩበትን የቤተክርስቲያን አገልግሎት በማበርከት ላይ መሆናቸው ብዙ ጎልቶ ባይታይም፣ ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በቁጥር 46 ሺህ ዲያቆናት መኖራቸው ታውቋል።  

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ ባቀረቡት አስተያየት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረበት ጊዜ፣ እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆኑን እንደገለጸላቸው አስረድተው ይህንንም በትህትና ራሱን ዝቅ በማድረግ፣ በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናውን በተግባር ማሳየቱን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ የደረሰበት አገልጋይ መሆኑንም በትንቢተ ኢሳ. 52:13-53 እና በቁጥር 12 ላይ ተጽፎ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የአገልግሎት ሕይወት፣ በተለይም በድህነት ሕይወት የሚገኙትን እና ለችግር የተጋለጡትን መርዳት መሆኑን ያስረዱት ክቡር አባ ፍሬደሪክ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴ. በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በ20:17-28 “የሰው ልጅም ለማገልገል እና ብዙዎችን ለማዳን፣ ሕይወቱንም አሳልፎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ተብሎ የተጻፈውን አስታውሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ ሁላችንም ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ራሳችንን ለአገልግሎት ማዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል። በማከልም የኢየሱስ ክርስቶስ የአገልጋይነት ምሳሌ የሆነው የዲቁና ሕይወትም ይህን ያስገነዝበናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዲያቆናት ለመላዋ ቤተክርስቲያን የብርታት ምልክቶች ናቸው ማለታቸውን ያስታወሱት ክቡር አባ ፍሬደሪክ፣ ዲያቆናት ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ከምን ጊዜም በበለጠ የሚያስፈልጉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ይፋ ባደረገው ሰነድ በቁ. 104 ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጥብቀው እንደተናገሩት “የዘመናችን ዲያቆናት፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚያበረክቱት መንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ በስነ ምሕዳር፣ በሁሉ አቀፍ የሰው ልጅ እድገት፣ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ተሰማርተው ድህነት ለማሰውገድ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ምሕረትን፣ ቸርነትን፣ አንድነትን እና የቤተክርስቲያን አገልግሎቶችን በስፋት ማዳረስ ያስፈልጋል” ማለታቸውን ክቡር አባ ፍሬደሪክ አስታውሰዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ጽ/ቤት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በመጨረሻም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ ዲያቆናት በአገልግሎታቸው ታማኞች እንዲሆኑ፣ ድሆችን እና የተጨነቁትን በማገልገል የመላዋ ቤተክርስቲያን አበራታች ምሳሌ መሆን እንዲችሉ በጸሎታችን ልናግዛቸው ይገባል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
06 May 2020, 15:48