ፈልግ

"በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብቻ በማትኮር በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መርሳት የለብንም"።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስከረም 17/2012 ዓ. ም. ለ106ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ዘንድሮ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አስታውሰው፣ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩበትን አካባቢ ጥለው እንዲሸሹ የተገደዱ መሆናቸውን አስረድተዋል። በሚደርሱበት አካባቢ መልካም አቀባበል ማድረግ ፣ የሕይወት ከለላን መስጠት፣ ለተፈናቃዮች ሊሰጡ የሚገቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማሳደግ እና ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፥

የቫቲካን ዜና፤

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ በቅድስት መንበር ውስጥ ለልዩ ልዩ አገራት ዲፕሎማቶች ባስተላለፍኩት መልዕክቴ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚደርስ ስቃይ ዓለማችንን ከሚፈታትኑ ወቅታዊ ችግሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ገልጫአለሁ። በየቦታው የሚከሰቱ አመጾች እና አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከሚከሰቱ አደጋዎች ጋር ሆኖ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን እና አስቀድሞም ቢሆን በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን በማጥቃት ላይ ይገኛል። እነዚህ ችግሮች የሚከሰቱባቸው በርካታ አገሮች በተፈናቃዮች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ዝግጅት የላቸውም።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሚገኝ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ፣ ቤተክርስቲያን ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምታቀርበውን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናክራ እንድትቀጥል የሚረዳ የአገልግሎት መመሪያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 5/2020 ዓ. ም. ይፋ አድርጓል።

በመሆኑም ብዙን ጊዜ ከእይታ ተሰውሮ የቆየውን እና የመላው ዓለም ቀውስ በሆነው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እየተባባሰ የመጣውን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መከራን በማስመልከት ይህን መልዕክቴን ለማስተላለፍ ወስኛለሁ። በእርግጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ በአደገኛነቱ፣ በክብደቱ እና በጂኦግራፊያዊ ስፋትነቱ የተነሳ፣ ቀዳሚ የፖለቲካ አጀንዳ በመሆን ዓለም አቀፍ ጥረትን በሚጠይቁ በርካታ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ እንቅፋትን በመደቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ መዘናጋት የለብንም። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ፣ ለብዙ ሰዎች ስቃይ ምክንያት የሆኑ ሌሎች በርካታ ቀውሶችን ሊያስረሳን አይገባም።

በጎርጎሮሳያኑ 2020 ዓ. ም. የተከሰቱ የመከራ ወቅቶችን በመመልከት ያስተላለፍኩት መልዕክቴ፣ ምንም እንኳን በግንባር ቀደም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚመለከት ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት በማኅበረሰቡ የኑሮ ቀውስ፣ የመገለል፣ ተቀባይነትን የማጣት እና ተነጥሎ የመቅረት ዕድል ያጋጠማቸውን ሁሉ ማካተት እፈልጋለሁ።

ይህን መልዕክቴን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 1/1952 ዓ. ም. “በግዞት ያለ ቤተሰብ” በሚል ርዕሥ ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ደንብ በመጥቀስ እጀምራለሁ። ሕጻኑ ኢየሱስ ከእናቱ ማርያም እና ከዮሴፍ ጋር ወደ ግብጽ በሸሸ ጊዜ የመፈናቀል እና ጥገኛ የመሆን መከራን በመቀበል በፍርሃት እና በጥርጣሬ ኖረ። (ማቴ. 2:13-15, 19-23) ዛሬ በዘመናችንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ይህ ዕድል ያጋጥማቸዋል። የብዙሃን መገናኛዎች በየቀኑ በሚያሰራጩት ዜና ከረሃብ፣ ከጦርነት እና ከሌሎች አደጋዎች በመሸሽ፣ ለራሳችው እና ለቤተሰቦቻቸው የሕይወት ዋስትናን እና የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ይሰደዳሉ። ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ በሚገደዱ ሰዎች መካከል፣ በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ተመሳሳይ መፈናቀል የደረሰበት ኢየሱስ ክርስቶስ ይገኛል። በረሃብ፣ በውሃ ጥም፣ በእርዛት፣ በህመም፣ በስደት እና በእስራት የሚሰቃዩትን ሰዎችን በምናይበት ጊዜ የሰዎችን መከራ ለማስወገድ ከእኛ ጋር ጥረት የሚያደርገውን ኢየሱስ ክርስቶስ እንመለከታለን። (ማቴ. 25: 31-46) በስቃይ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በመመልከት ኢየሱስን ማየት የምንችል ከሆነ፣ በእነዚህ ሰዎች በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን ለመውደድ እና ለማገልገል በመቻላችን ምስጋናችንን ለእርሱ እናቀርብለታለን።

ልብሶቹ የተቀደዱ፣ እግሮቹ የቆሸሹ፣ መልኩ የተለወጠ፣ ሰውነቱ የቆሰለ፣ አንደበቱ ቋንቋችንን መናገር ቢያቅተው፣ በዓይናችን ተምልክተነው እርሱ መሆኑን ለይተን ማወቅ ባንችልም የተፈናቀሉት ሰዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንድንገናኝ መልካም አጋጣሚን ይፈጥሩልናል። ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓ. ም. ባስተላለፍኩት መልዕክቴ እንደገለጽኩ፣ የተፈናቆዮችን ችግር ለመፍታት አራት ሐዋርያዊ የዕርዳታ ተግባሮችን ለማበርከት ተጠርተናል። እነርሱም ከሚኖሩበት አካባቢ ለተፈናቀሉት መልካም አቀባበል ማድረግ ፣ የሕይወት ከለላን መስጠት፣ ለተፈናቃዮች ሊሰጡ የሚገቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማሳደግ እና ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ የሚሉ ናቸው። በእነዚህ አራት የሐዋርያዊ የእርዳታ አቅርቦት ተግባር ላይ ተጨምሪ የሚሆኑ፣ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እና ከችግሩ ምክንያት እና ውጤቱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያላቸውን ቃላት ማከል እወዳለሁ።

በሚገባ ለመረዳት አስቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል። ስለ ሌሎች ሰዎች ግንዛቤን እንዲኖረን ዕውቀት የመጀመሪያው እና በጣም አስፈላጊ ደረጃ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ በነበሩ ደቀ መዛሙርት ላይ የሆነውን በማስታወስ ይነግረናል። ይህንን በሚያወሩበት እና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሯቸው ይጓዝ ጀመር። ነገር ግን በዓይናቸው እያዩት ማን እንደሆነ ማወቅ አልቻሉም (ሉቃ. 24:15-16)። ስለ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች በምናወራበት ጊዜ ቁጥራቸውን እና ብዛታቸውን ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን። ማሰብ ያለብን ስለ ብዛታቸው ወይም ቁጥራቸው ሳይሆን ሰው መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል። በአካል የምናገኛቸው ከሆነ ስለ እነርሱ ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ታሪካቸውን ያወቅን ከሆነ ማንነታቸውንም ማወቅ እንችላለን። ለምሳሌ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋ በእኛ ላይ ያሳየውን ልምድ በመገንዘብ በተፈናቃይ ሰዎች ላይም ተመሳሳይ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችን እናውቃለን።

የተቸገሩትን ለማገልገል ከፈለግን ወደ እነርሱ መቅረብ ይኖርብናል፤ ይህ ግልጽ መስሎ ሊታይ ይችላል ፣ ግን ብዙውን ጊዜ ተቃራኒ ነው። “አንድ ሳምራዊ በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውየው መጣ። ባየውም ጊዜ ራራለት። ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይት እና የወይን ጠጅ በቁስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀመጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደርያ ቤተ ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተከባከበው” (ሉቃ. 10:33-34) ፍርሃት እና ጭፍን ፍርድ ከሰዎች እንድንርቅ እና ጉርብትናን መስርተን በፍቅር እንዳናገለግላቸው ያደርጉናል። ወደ ሌሎች ሰዎች መቅረብ፣ በእነዚህ ወራት ውስጥ ዶክተሮች እና ነርሶች እንዳስተማሩን ሁሉ ሃላፊነት መውሰድ ማለት ነው። የተቸገሩትን ለመርዳት ራስን ዝግጁ አድርጎ እና ወደ እነርሱ መቅረብ ከአገልግሎት በላይ ልዩ ትርጉም አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበ ጊዜ ከሁሉ በላይ የሆነ ምሳሌን አስተምሮናል። “ፎጣም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ሳህን ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ። (ዮሐ. 13:1-15)

ለመታረቅ ማዳመጥ አለብን፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም በመላክ ይህን አስተምሮናል። የመከራ ልመና በሰው ልጅ ጆሮ ለማዳመጥ ፈልጓል። “እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደ አንድ ልጁን ሰጠ፤ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ እንዲፈርድ አይደለም”። (ዮሐ. 3:16-17) ከሞት የሚያድን እና የሚያስታርቅ ፍቅር የሚጀምረው ከማዳመጥ ነው። በዛሬው ዓለም ብዙ መልዕክቶች ይሰራጫሉ፣ ነገር ግን በሰዎች ዘንድ የማድመጥ ዝንባሌ እየቀነሰ እና እየጠፋ ሄዷል። እውነተኛ እርቅ የሚገኘው በትህትና እና በትኩረት ማድመጥ ስንችል ብቻ ነው፡፡ ዘንድሮ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2020 ዓ. ም. አውራ ጎዳናዎቻችን ለሳምንታት ያክል በጸጥታ ተውጠዋል። ይህ አስጨናቂ ጸጥታ የሰዎችን የመከራ ጩኸት፣ የተፈናቃዮችን እና ክፉኛ የተጎዳች ምድራችንን ዋይታ እንድናደምጥ ዕድል ሰጥቶናል። ማድመጥ ከጎረቤቶቻችን ጋር እንድንታረቅ፣ ከተገለሉት ጋር፣ ከራሳችን እና ምሕረቱን ሊሰጠን ከማይሰለቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንድንታረቅ ዕድል ይሰጠናል።

ማደግ ከፈልግን ካለን ማካፈል ያስፈልጋል፤ ያለንን ከሌሎች ጋር መጋራት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ዋና ተግባር ነበር። አማኞች ሁሉ አንድ ልብ እና አንድ አሳብ ነበረኣቸው፤ ማንም ሰው ‘ይህ የእኔ ነው’ የሚለው ነገር አልነበረውም፤ በመካከላቸው ሁሉ ነገር የጋራ ነበር። (የሐዋ. 4:32) የምድራችን ሃብት በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ እንዲቀር እግዚአብሔር አልፈለገም። የእግዚአብሔር ፍላጎት ይህ አልነበረም! ማንንም ወደ ጎን ሳናደርግ፣ አብረን ለማደግ ያለንን በጋራ መካፈልን መማር አለብን። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ መሳፈራችንን እንድናስታውስ አድርጎናል። ሁላችንም ባለን ተመሳሳይ ጭንቀት እና ፍርሃት ከወረርሽኙ ብቻውን መትርፍ የሚችል ሰው አለመኖሩን እንድናውቅ አድርጎናል። እውነተኛ እድገትን ለማምጣት ከፈለግን፣ ያሉትን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ አውጥቶ ለኢየሱስ እንደ ሰጠው ልጅ ያለንን ከሌሎች ጋር  በመጋራት አብሮ ማደግ ያስፈልጋል። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድሪያስ እንዲህ አለ፥ አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ነገር ግን ይህ ለዚህ ሕዝብ ሁሉ ምን ይበቃል አለ? ነገር ግን ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ያህል አገኙ፤ የተረፈውንም ትርፍራፊ ሰብስበው በአሥራ ሁለት መሶን ሞሉ። (ዮሐ. 6:1-15)

አገልግሎትን ለማሳደግ መሳተፍ አለብን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር መገናኘቱን በሚገልጽ በዮሐ. 4:1-30 ላይ እንደተጻፈው፣ ወደ እርሷ በመቅረብ እንዳዳመጣት፣ ልቧን የሚነካ ንግግር በመናገር፣ ወደ እውነትም በመምራት፣ የሰማችውን መልካም ዜና ለሌሎች እንድታበስር አድርጓታል። “የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑ እዩ”! (ዮሐ. 4:29) አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ለማገልገል ያለን ግፊት እውነተኛ ሀብታቸውን እንዳናይ ያደርገናል። እኛ የምናገለግላቸው ሰዎች በአገልግሎት እንዲሳተፉ ማድረግ ከፈልግን የዳኑበትን የራሳቸውን መንገድ እንዲመሰክሩ ማድረግ ያስፈልጋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ላይ የጋራ ሃላፊነት መውሰድ ምኑን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ፣ እያንዳንዱ ሰው በሚያበረክተው የግል አስተዋጽዖ ብቻ ወረርሽኙ ያስከተለውን መከራ ማለፍ እንችላለን። ሰዎች የተጠሩበትን የአገልግሎት ዓይነት ለይተው እንዲያቁ የሚያስችሉ ዕድሎችን በማመቻቸት አዲስ የእንግዳ ተቀባይነት፣ የወንድማማችነት እና የአንድነት ጥሪ እንዲያውቁ ማገዝ ያስፈልጋል።

ለመገንባት መተባበር ያስፈልጋል፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ማኅበረሰብ የተናገራቸው ይህ ነው። ወንድሞቼ! በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የምነግራችሁ ይህ ነው፥ መለያየት በመካከላችሁ አይኑር፤ ሁላችሁም ተስማምታችሁ በአንድ አሳብ እና በአንድ ዓላማ ጸንታችሁ ኑሩ። (1ኛ ቆሮ. 1:10) የእግዚአብሔርን መንግሥት መገንባት ለክርስቲያኖች የተሰጠ የጋራ ተግባር በመሆኑ፣ የቅናት ፈተናን፣ ልዩነትን እና መከፋፈልን አስወግደን መተባበርን መማር ያፈልጋል። አሁን የምንገኝበትን ጊዜ ስንመለከተው፣ የብቸኝነት ጊዜ አለመሆኑን እናያለን፤ በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳንፈጥር የመጣብንን መከራ በጋራ መጋፈጥ ያስፈልጋል። የጋራ መኖሪያ ቤታችንን ከአደጋ ተከላክለን፣ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር እቅድ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ፣ ማንንም ወደ ጎን ሳናደርግ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማሳደግ ይኖርብናል።

ቅዱስ ዮሴፍ ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአደጋ ለማትረፍ ወደ ግብጽ የተሰደደበትን ምሳሌ በሚገልጽ ጸሎት መልዕክቴን ማጠቃለል እፈልጋለሁ።

እግዚአብሔር አባት ሆይ! ላንተ ውድ የሆኑትን ሕጻኑን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እናቱ ማርያምን ከአደጋ እንዲጠብቃቸው በማለት ቅዱስ ዮሴፍን አዘጋጅተህላቸዋል።

እኛም የእርሱን ጥበቃ እና እርዳታን እንድንረዳ አድርገን። የኃይለኞችን ጥላቻን እና በተፈናቃዮች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ከልብ የተረዳው ቅዱስ ዮሴፍ፣ በጦርነት እና በድህነት ምክንያት የሚኖሩበትን ቤት እና መሬት ጥለው የሚሸሹ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መጽናናትን እና ጥበቅ እንዲያደርግላቸው እንለምናለን።

ከሚኖሩበት አካባቢ ለመሸሽ የተገደዱት በሙሉ በቅዱስ ዮሴፍ አማላጅነት አማካይነት ኃይልን እንዲያገኙ፣ በሐዘን ጊዜ መጽናናትን፣ በመከራ ጊዜ ብርታትን እንዲያገኙ እርዳቸው።

የተሰደዱትን ተቀብለው ለሚያስተናግዱት በሙሉ፣ እውነተኛ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ እና ማርያምን በፍቅር እና በርህራሄ የመራቸው የጻድቅ እና ጥበበኛ አባት የዮሴፍ ልብ ስጣቸው።

የዕለት እንጀራውን በእጆቹ ሥራ ያገኘው ቅዱስ ዮሴፍ፣ ንብረታቸውን እና ሥራቸውን ያጡት በሙሉ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን እና የሚኖሩበትን ስፍራ ተመልሰው እንዲያገኙ ይርዳቸው።

ይህን ጸሎት ቅዱስ ዮሴፍ ወደ ግብጽ በማሸሽ ባዳነው በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናቀርባለን። እንደ አንተ ፈቃድ፣ ቅዱስ ዮሴፍ ባፈቀራት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ጸሎታችንን እንድትቀበለን እንለምንሃለን። አሜን።                    

16 May 2020, 19:09