ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ የሚገኝ የሕጻናት ሆስፒታል በጎበኙበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ የሚገኝ የሕጻናት ሆስፒታል በጎበኙበት ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ "ነርሶች የሕሙማንን ስቃይ የሚጋሩ፣ ተስፋንም የሚሰጡ ናቸው" አሉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ግንቦት 4/2012 ዓ. ም. ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የሕክምና አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት ነርሶች እና ዋላጆች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ክቡራት እና ክቡራን፣ ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እናቀርብላችኋለን፥ 

የቫቲካን ዜና፤

“የተከበራችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣

በተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የነርሶች እና የአውላጆች ቀን እንዲከበር በማለት በይፋ ያጸደቀውን ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን በማክበር ላይ እንገኛለን። በዚሁ ጊዜ ፣ ዘመናዊ የነርስ ሞያን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀውን የፍሎረስ ናይቲናጋል ልደት ሁለት መቶኛ ዓመትንም እናስታውሳለን።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መዛመት ምክንያት ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የጤና መቃወስ በተከሰተበት አስጨናቂ ጊዜ የነርሶች እና የአዋላጆች ሚና ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን በድጋሚ ለመገንዘብ በቅተናል። የአዋላጆችን፣ በተለይም የነርሶችን ጥንካሬ እና የሚከፍሉትን መስዋዕትነት፣ ሞያቸው የሚጠይቀውን የአገልግሎት ብቃት፣ የሕይወት መስዋዕትነት፣ ሃላፊነት፣ ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር፣ ለግል ሕይወታቸው ሳይሳሱ፣ ራሳቸውን ለሞት አደጋ አሳልፈው በመስጠት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለተጠቁት የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ላይ መሆናቸውን በየቀኑ እንመሰክራለን። ለሕሙማን በሚሰጡት በዚህ ታማኝ አገልግሎታቸው ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በጸሎቴም አስታውሳቸዋለሁ። እነዚህን ታማኝ አገልጋዮች እና በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡትን በሙሉ እግዚአብሔር በስም ያውቃቸዋል።  ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይ ብርሃን ያብራላቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይስጣቸው።

ነርሶች በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚናን ተጫውተዋል። ከሕሙማን ጋር ባላቸው ዕለታዊ ግንኙነት ሕመም በሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ስቃይ ተመልክተዋል። ነርሶች እና አዋላጆች ለሰዎች ሕይወት ክብርን በመስጠት፣ ስቃያቸውንም በመመልከት የተላከላቸውን ጥሪ አሜን ብለው የተቀበሉ ወንዶች እና ሴቶች ናቸው። ለሕሙማን አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎትን ከመስጠት፣ ሕይወትን ከአደጋ ከመከላከል እና ከመጠበቅ በተጨማሪ ብርታትን፣ ተስፋን እና እርግጠኝነትን ይሰጣሉ።

ውድ ነርሶች! ግብረ ገባዊ ሃላፊነት የሞያዊ አገልግሎታችሁ መለያ ምልክት ነው። በመሆኑም በቴክኒካዊ የሳይንሳዊ እውቀት ዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጠው ሳይሆን ከሰው ልጆች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊያድግ እና ሊለመልም ያስፈልጋል። በእያንዳንዱ የሕይወት ደረጃ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ሳታቋርጡ የማድመጥ፣ ፍላጎታችውንም ከልብ የመረዳት ችሎታ አላችሁ። በተለያዩ ገጠመኞች መካከል የሕክምና ሂደቶችን አክብሮ መገኘት ብቻውን በቂ አይደለም። ነገር ግን ለሕሙማን ትኩረት በመስጠት የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ከነርሶች በተጨማሪ እናንት አዋላጆች፣ ለሰው ልጅ ወሳኝ በሆኑት ጊዜያት፥ በልደት እና በሞት፣ በሕመም እና በጤና ጊዜ ቅርብ በመሆን አስፈላጊውን እርዳታ ታደርጋላችሁ። ወደ ሞት በሚቃረቡበት ጊዜ የሚያሳዩትን ጨንቀት በመጋራት፣ በመጨረሻዎቹ የሕይወት ደቂቃዎች መጽናናትን እና እፎይታን ትሰጣላችሁ። ይህን በማድረጋችሁ በአጠገባቸው እንደሚገኙ ቅዱሳን ትቆጠራላችሁ። ወደ ሰዎች ዘንድ በመሄድ፣ የተለያዩ ሕመሞችን የሚፈውስ፣ በትህትና ራሱን ዝቅ በማድረግ የደቀ መዛሙርትን እግር ያጠበ የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ ይዛ የምትጓዝ ቤተክርስቲያንን ትመስላላችሁ። ለሰው ልጆች በሙሉ ለምታቀርቡት አገልግሎታችሁ አመሰግናችኋለሁ።

በበርካታ አገሮች የነበረውን የጤና አገልግሎት ደካማነት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግልጽ አድርጎታል። ስለዚህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥታት መሪዎች በጤናው ዘርፍ ትኩረት በማድረግ፣ ለጋራ ጥቅም ቅድሚያን በመስጠት ገንዘብ እንዲያፈሱበት፣ የጤና አገልግሎት ሥርዓቱንም እንዲያሻሽሉ፣ የእያንዳንዱ ሰው ክብር ተጠብቆ በቂ የጤና እንክብካቤን ማግኘት እንዲችል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የጤና ባለሞያ እንዲያዘጋጁ በትህትና እጠይቃለሁ። ለሕሙማን የሚሰጥ እንክብካቤን በተመለከተ ነርሶች ለሚጫወቱት ሚና፣ ለአስቸኳይ የሕክምና አቅርቦት፣ ለበሽታ መከላከል ተግባር፣ ለጤና ዘርፍ እድገት፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በትምህርት ቤት ለሚሰጡት ውጤታማ አገልግሎት እውቅናን መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው።

ነርሶች እና አዋላጆች በማኅበረሰብ ውስጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያበረክቱትን የጤና አገልግሎት ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ ከተፈለገ ለመብታቸው መከበር በቂ ዋጋን መስጠት ያስፈልጋል። የጤና ባለሞያዎችን ማዘጋጀት የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል እና ጠቅላላውን የጤና አገልግሎት ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው። የጤና ባለ ሞያቸውን በሳይንሳዊ፣ ሰብዓዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ዕውቀቶች በማሳደግ፣ በሥራው ዓለምም መብታቸው ስለ መጠበቁ ሙሉ ዋስትናን መስጠት ያስፈልጋል። 

ይህን በተመለከተ የጤና ባለሞያዎች ማኅበራት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። የስልጠና ዕድልን ከማመቻቸት በተጨማሪ እያንዳንዱን የጤና ባለሞያ የማኅበሩ አባልነት እንዲሰማው በማድረግ በሥራ ዙሪያ የሚደርስባቸውን ሥነ ምግባራዊ ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ችግሮችን እንዲቋቋሙ ያግዛሉ።

ለነፈሰ ጡር ሴቶች በወሊድ ጊዜ ድጋፍን ለሚያደርጉ አዋላጆች ልዩ መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ሥራችሁ ለሕይወት እና ለእናትነት ከሚሰጥ አገልግሎት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው በመሆኑ እጅግ የከበረ ሞያ ነው። በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ፣ ዕብራውያን ሴቶችን የሚረዱ ፣ ጺፓራ እና ፉሐ የተባሉ ሁለት ብርቱ አዋላጆች በኦሪት ዘጸዓት 1:15-21 ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። ዛሬም የሰማዩ አባት አገልግሎታችሁን በመመልከት ምስጋናውን ያቀርብላችኋል።

ውድ ነርሶች እና ውድ አዋላጆች ሆይ! ይህ ዓመታዊ በዓል ለማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት እድገት ሲባል የሥራችሁን ታላቅነት አጉልቶ የሚያሳይ ይሁን። በጸሎቴም የማስታውሳችሁ መሆኔን እያረጋገጥኩላችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁ፣ እንክብካቤን ለምታደርጉላችሁ እና ለእናንተም በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬዬን እልክላችኋለሁ”።        

12 May 2020, 18:01