ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጴንጤቆስጤ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባከበሩበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጴንጤቆስጤ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባከበሩበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔር ለሚያቀርብልን ጥሪ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተለዩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በግንቦት 23/2012 ዓ.ም የበዓለ አምሳ ወይም የጴንጤቆስጤ በዓል ተክብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜም ዓለምአቀፍ የተልእኮ ቀን እለተ ሰንበት ተክብሮ ማለፉ ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚህ ዓለማቀፍ የተልእኮ ቀን የሚሆን መልእክት አስተላልፈዋል፣ ቅዱስነታቸው የተልዕኮ ቀን መልእክት አሁን በዓለም ላይ በመከሰት ላይ ካለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኛ ጋር በማዛመድ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እ.አ.አ ለ2020 ዓ.ም ለዓለምአቀፍ የተልዕኮ ቀን ሰንበት ያስተላለፉት መልእክት በእለቱ ከተከበረው በዓለ ሃምሳ ወይም ጴንጤቆስጤ በዓል ጋር በተያያዘ መልኩ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን እ.አ.አ ለ2020 ዓ.ም ዓለምአቀፍ የተልዕኮ ሰንበት መልእክት ጭብጥ የተወሰደው እና የተመረጠው “ እነሆኝ እኔን ላከኝ” (ኢሳያስ 6፡ 8) የሚለው መሪ ቃል እንደ ሆነ ተገልጿል።

አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ ለተልዕኮ የተደረገ ጥሪ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ ባለፈው ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም የተከበረውን መደበኛ ያልሆነ መልኩ የተከበረውን ልዩ ዓለም አቀፍ የተልዕኮ ቀን ላይ በተደርገው ፀሎት ላይ የተናገሯቸውን ቃላት በማስታወስ ነበር። አሁን ባለው ዓለም አቀፉ ቀውስ ምክንያት ግራ በተጋባንበት እና ፍራቻ ውስጥ ባለንበት ወቅት እንኳን ሳይቀር ጌታ “ማንን እልካለሁ?” በማለት ጥይቄ ማቅረብ መቀጠሉን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። እያጋጠመን ባለው ህመም እና ሞት ውስጥ ደካሞች መሆናችንን እንድናስብ የሚያደርግ ክስተት ቢሆንም እኳን እንዲሁም “ለሕይወት ያለንን ጥልቅ ፍላጎት እና ከክፉም ነፃ ለመውጣት” ያለንን ፍላጎት የሚያሳይ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል ብለዋል። የተልዕኮ ጥሪ የሚመነጨው ደግሞ “በአገልግሎት እና ምልጃ” አማካይነት “ለእግዚአብሔርና ለባልንጀሮቻችን የፍቅር አገልግሎት እራሳችንን እንድናተጋ ” ከሚቀርብልን ጥሪ ነው ብለዋል።

ሚስዮናውያን ሚሲዮናዊ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞት ተልእኮውን ሙሉ በሙሉ እንዳጠናቀቀ ሁሉ እኛም “ለሌሎች ራሳችንን ስንሰጥ በትክክል ራሳችንን እናገኘዋለን” በማለት በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ተልእኳችን፣ ጥሪያችን፣ ለመላክ ፈቃደኛ መሆናችን በራሱ እንደ “አብ ሚስዮናዊ” መሆን ማለት ነው ብለዋል። “የግል ጥሪያችን” የተመሠረተው “በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን” ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያን እንደ ሚስዮናዊ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደገለፁት በተለይም “የኢየሱስን ተልዕኮ በታሪክ ውስጥ የቀጠለችው” ቤተክርስቲያን ናት ያሉ ሲሆን ስለዚህ ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ የቤተክርስቲያን አባላት ሁሉ በቤተክርስቲያን ስም ይላካሉ ብለዋል። በወንጌል ምስክርነታችን እና እወጃችን እግዚአብሔር “ፍቅሩን መግለጡን” ይቀጥላል በማለት በመልእክታቸው የተናገሩት ቅዱስነታቸው እሱ “ልብን ፣ አእምሮን ፣ አካላትን ፣ ማህበረሰቦችን እና ባህሎችን በሁሉም ቦታ እና ሰዓት ለመንካት እና ለመቀየር የሚያስችል” ኃይል አለው ብለዋል።

ለግንኙነት ምላሽ መስጠት

“ተልዕኮው የእግዚአብሔር ጥሪ ነፃ እና ንቁ ምላሽ ነው” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተልእኮ የሚደርገውን ጥሪ የሚታወቅ የሚሆነው “በቤተክርስቲያኑ ውስጥ አሁን ካለው ከኢየሱስ ጋር የግል የፍቅር ግንኙነት ሲኖረን” ብቻ ነው ብለዋል። ያ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን መኖር እና በተግባር በሕይወታችን ውስጥ ለመቀበል ያለንን ዝግጁነት በማውሳት ጥያቄ ያነሳል ያሉት ቅዱስነታቸው ያ ጥሪ በዕለት ተዕለት ክስተቶች ውስጥ በጋብቻ ለተሳሰሩ ጥንዶች፣ በገዳም ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች እና በተቀቡ አገልጋዮች የሚደረግ ጥሪ ነው ብለዋል።  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ሌላው ጥያቄ “ስለ እምነታችን ለመመሥከር በማንኛውም ጊዜ ወይም ቦታ ለመላክ” ፈቃደኞች ከሆንን ከአብ ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመሥረት ይኖርብናል፣ ማርያም “ሁልጊዜ በአምላክ ፈቃድ ለመካፈል ዝግጁ” እንደሆንች እኛም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

ተልዕኮ ለህይወት መልስ ይሰጣል

የቤተክርስቲያኗ ተልእኮ በአሁኑ ወቅት ተግዳሮት የሚገጥመው “በዚህ ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ወቅት እግዚአብሔር የሚናገረውን መረዳት” መሆኑን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመልእክታቸው አክለው ገልጸዋል። ሰዎች ብቻቸውን ሲሞቱ ወይም እንደተገለሉ ሆኖ ሲሰማቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የመተዳደሪያ ሕልውና የሆነው ሥራቸውን ሲያጡ፣ ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ መሄድ ወይም በቤት ውስጥ መቆየት አስፈላጊነት ሲናገሩ፣ “ማህበራዊ ግንኙነቶችን እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን እንድንገመግም ይገብዘናል” ብለዋል። ይህ ሁኔታ ከሌሎች ጋር የመገናኘት አስፈላጊነት ያለንን ግንዛቤ ሊጨምር ይችላል በማለት አክለው በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው የሌሎችን ፍላጎቶች እንድንረዳ እግዚአብሔር ጸሎት ልባችንን እንዲነካ አጋጣሚውን ይከፍትልናል ብለዋል። በቤተክርስቲያኗ ሥርዓተ አምልኮ መከፋለ ወይም ለመሳተፍ ያልቻልን ሰዎች ካለን አሁን “እሁድ እሁድ መስዋዕተ ቅዳሴ ማስቀደስ የማይችሉ የብዙ ክርስቲያናዊ ማህበረሰቦችን ተሞክሮ እንረዳለን” ብለዋል።

ማንን እልካለሁ?

በነቢዩ ኢሳያስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጥያቄ “ለእኛ አንድ ጊዜ ተገለጸልን፣ እናም “እነሆኝ እኔን ላከኝ!” (ኢሳያስ 6: 8) በማለት በልግስና መንፈስ የተሞላ አሳማኝ ምላሽ ከእኛ ይጠብቃል ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመልእክታቸው መደምደሚያ ላይ የዓለም የተልዕኮ ቀን እሁድ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በኢየሱስ ተልእኮ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ለማደረግ በጸሎት ፣ በማሰላሰል እና በቁሳዊ ነገሮች በመርዳት የምናረጋግጥበት ቀን ይሆናል ብለዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች እና አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ፍላጎቶች ሁሉ እንዲሟሉ ለማድረግ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም የተሰበሰበው ገቢ በመንፈሳዊ ተልዕኮ ተግባር ላይ የተመሳማሩትን ማህበራት የሚያከናውኑዋቸውን መንፈሳዊ ተግባር ይደግፋል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸውን አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
31 May 2020, 14:41