ፈልግ

የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ መጽሐፍ ሽፋን፣ የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ መጽሐፍ ሽፋን፣ 

የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ልደት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ መጽሐፍ መታተሙ ተገለጸ።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የልደታቸው መቶኛ ዓመት የሚያስታውስ፣ በፎቶ ግራፎች የታገዘ መጽሐፍ ታትሞ ለንባብ መብቃቱ ታውቋል። “መቶ ዓመታት በጽሑፍ እና በምስል ሲተነተኑ” የሚል ርዕሥ የተሰጠውና በቫቲካን አሳታሚ ድርጅት በታተመው መጽሐፍ መግቢያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን የሚያስታውሱ ጽሑፎች ማበርከታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ጽሑፋቸው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወንጌል ምስክርነት ከወጣትነት ዕድሜ ጀምረው ብዙ ስቃይ የተቀበሉ፣ ቤተሰባቸውን በሞት ያጡ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት አስቸጋሪ ዓመታት ያሳለፉ፣ ዓለምን በመዞር ለሰው ልጅ የነበራቸውን ታላቅ ፍቅር መግለጽ የቻሉ መሆናችውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲስ ታትሞ በወጣው መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጹት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስቃያቸውን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር አቅርበው ከወላጆቻቸው የተቀበሉት እምነት ጥንካሬን የሰጣቸው መሆኑን አስረድተው ይህን ጠንካራ እምነት ለበርካታ ወጣቶች በመመስከር እና በማስተማር የታወቁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእምነት ምስክርት የተመለከቱ ወጣት ካህናት፣ የተቀበሉትን የእምነት መንገድ በቆራጥነት የተጓዙ፣ በሕይወታቸው ተግባራዊ አድርገው ለማሳየት የበቁ መሆናቸን ገልጸዋል።

የተመረጡ ጽሑፎችን እና ምስሎችን ያካተተ መጽሐፍ ነው፣

የር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሕይወት በጽሑፍ እና በምስል የሚተነትን ይህ መጽሐፍ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ማዕረግ ከተመረጡበት፣ ከጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 16/1978 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ቤት እስከ ተመለሱበት፣ ሚያዝያ 2/2005 ዓ. ም. ድረስ ያሉትን የሐዋርያዊ አገልግሎት ጊዜ የሚያስታውስ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። መጽሐፉ በውስጡ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ካቀረቧቸው ስብከቶች፣ ንግግሮች እና አስተምህሮዎች መካከል የተመረጡትን የያዘና፣ በእንግሊዝኛ እና በፖላንድኛ ቋንቋዎች የተጻፈ መሆኑ ታውቋል።

የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤
የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በችግር መካከል በደስታ እንድንራመድ አስተምረውናል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጽሐፉ ውስጥ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በማስታወስ ባበረከቱት ጽሑፋቸው፣ አዲስ የታተመው መጽሐፍ በበርካታ ሰዎች እጅ እንደሚገባ፣ በተለይም ወደ ወጣቶች በስፋት እንደሚደርስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ “ፍርሃትን በማስወገድ በሮቻችሁን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክፍት አድርጉ” በማለት የተናገሯቸውን አበራታች ንግግሮች የያዘ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲናገሩ የተለያዩ ችግሮችን ተሸክመው ወደ መላው ዓለም የተጓዙ መሆናቸውን አስረድተው፣ እርሳቸው የተጓዙበትን መንገድ ተከትለን ስንጓዝ ብቻችን አለ መሆናችንን በማረጋገጥ የርኅራሄ እና የምህረት እናት ከሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ያለንን የጠበቀ ግንኙነት ያጠናክራል ብለዋል።

በለውጥ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን እርግጠኛ መሪ ነው፣

በቀላል ቋንቋ ለወጣቶች መልዕክትን የሚያስተላልፈው ይህ መጽሐፍ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ታላቅ የእምነት መስካሪ እና የጸሎት ሰው መሆናቸውን ከመግለጹ በተጨማሪ፣ በለውጥ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ መንገድን በማሳየት፣ በጉዞዋ እርግጠኛ እንድትሆን የሚያደርግ መጽሐፍ እንደሆነ ታውቋል። መጽሐፉ ከዚህ በተጨማሪ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነትን፣ የእግዚአብሔርን ምሕረትን፣ የመንፈስ ቅዱስ እገዛን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተክርስቲያን እናት መሆኗን የሚገልጹ ሐዋርያዊ መልዕክቶችን እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ጭብጦችን ያካተተ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል።

የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤
የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የምስራቅ አውሮፓ ቤተክርስቲያን ድምጽ ነበሩ፣

ለሰው ልጆች ታላቅ ፍቅር የነበራቸው፣ ለጋራ ውይይት ዝግጁ የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በጊዜው የሚነሱ ጦርነቶችን ለማስቆም በቆራጥነት የተነሱ፣ በስቃይ ውስጥ የሚገኙት እፎይታን እንዲያገኙ አብረው ጥረት ያደረጉ እና በኮሚንስት ሥርዓት ድምጽ ለሌላት ቤተክርስቲያን ድምጽ የሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

በወጣትነት ዕድሜ ቤተሰቦቻቸውን በሞት አጥተዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጽሐፉ ውስጥ እንደገለጹት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሕይወት ዘመናቸው የተለያዩ ስቃዮችን ያሳለፉ፣ ስቃያቸውም ከአገራቸው ከፖላንድ ሕዝብ ስቃይ ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑን ተናግረው፣ በመጀመሪያ እናታቸውን ቀጥሎም የሚወዱትን ወንድማቸውን፣ በመጨረሻም አባታቸውን በሞት ያጡ መሆኑን አስታውሰው፣ ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት በገቡበት ወቅት የተቀሩ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ፣ በርካታ ጓደኞቻቸው ሕይወታቸውን በጦርነት አደጋ ሲሰው እርሳቸው መላ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ያቀረቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወጣትነት ዕድሜአቸው ከባድ ሕመሞችን ያሳለፉ፣ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ዓመታትም፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጥረር በ1981 ዓ. ም. ከተሰነዘረባቸው የግድያ ሙከራ የተረፉ፣ ደማቸውን ለቤተክርስቲያን ሲሉ ያፈሰሱ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ የተጋሩ መሆናቸውን አስታውሰው በመጨረሻም፣ አዲስ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእግዚአብሔርን ምሕረት የመሰከሩ፣ የሕይወት ታሪካቸውን በመጠኑም ቢሆን ለሰሙት ወጣቶች ታላቅ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ መሆኑን አስረድተው፣ አዲስ የታተመው መጽሐፍ የሕይወት ታሪካቸውን በሚገባ የሚያብራራ መጽሐፍ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤
የልደታቸው መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ፤
05 May 2020, 20:48