ፈልግ

ለጨቅላ ሕጻናት በቂ እንክብካቤን ስለማድረግ፤  ለጨቅላ ሕጻናት በቂ እንክብካቤን ስለማድረግ፤  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሰብዓዊ ክብር የሚያስጠብቅ ባሕል እንዲዘረጋ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ ስነ ሕይወት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለእንግሊዝ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በላኩት መልዕክታቸው፣ የመላውን ሰብዓዊ ፍጥረት ክብር የሚያስጠብቅ ባሕል እንዲዘረጋ ማሳሰባቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው ባሁኑ ጊዜ ለሰብዓዊ ክብር እና ለመልካም እሴቶች መዳበር በትጋት እየሠሩ ያሉትን በጸሎት ማገዝ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። አክለውም የሰዎች ጤና በመቃወሱ ምክንያት የብዙዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን አስታውሰው፣ በመሆኑም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊውን ትኩረት፣ በተለይም በማኅበረሰቡ መካከል ተረስተው ለቀሩት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሕይወት ጥበቃን በማድረግ፣ የሰውን ሕይወት ክብር የሚያስጠብቅ ባሕል እንዲያድግ አሳስበዋል።

የቫቲካን ዜና፤

“ሕይወት ይሻላል” በሚለው የ2012 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የስነ ሕይወት ቀን መሪ ቃል በመመራት ዕለቱን በማክበር ላይ የሚገኙት የእንግሊዝ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ከስኮት ላንድ እና ከአይር ላንድ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመተባበር፣ የሰው ልጆች ሕይወት በሁሉም የሕይወት ደረጃዎች ከፍተኛ ዋጋ እና ትርጉም ያለው መሆኑን ለሕዝቦቻቸው በማስረዳት ላይ መሆናቸው ታውቋል። የየአካባቢው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ይህን ቀን በጋራ ለማክበር የወሰኑት እሑድ ግንቦት 23/2012 ዓ. ም. ቢሆንም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው እንቅፋት የተነሳ በተለያዩ ቀናት ለማክበር መወሰናቸው ታውቋል። 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለሰው ሕይወት እንክብካቤ ለሚያድረጉት በሙል እንጸልይላቸው፣

ዘንድሮም እንደተለመደው፣ ዓለም አቀፍ የስነ ሕይወት ቀን ምክንያት በማድረግ ለእንግሊዝ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በላኩት መልዕክታቸው፣ “Evangelium Vitae” ወይም “ለምዕመናን የሚቀርብ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት” በማለት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን 25ኛ ዓመቱን በማስታወስ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የስነ ሕይወት መምሪያ አስተባባሪ ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግተን በላኩት መልዕክታቸው፣ ባሁኑ ጊዜ በሕመም ላይ የሚገኙትን እና ሰብዓዊ እርዳታን በመለመን ላይ ለሚገኙት ነፍሳት ዕለታዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙትን፣ በተለይም በኮሮና ወረርሽኝ ለተጠቁት የሕክምና እርዳታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙትን በጸሎት ማስታወስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ያጋጠመው የጤና መቃወስ ለስነ ሕይወት የሚሰጠውን የአክብሮት ባሕል እና ከፍተኛ የሞራል ግዴታን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋ።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት የተቀበሉት ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግቶን በእንግሊዝ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ስም ለቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መልዕክታቸው ተስፋን የሚሰጥ፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለሚያቀርቡት ሐዋርያዊ አገልግሎት ብርታትን የሚጨምር መሆኑንም አስረድተዋል። ዘንድሮ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የስነ ሕይወት ቀን መልዕክት የሚያተኩረው ለጨቅላ ሕጻናት እና ለነፍሰ ጡር እናቶች መደረግ ስለሚገባ እንክብካቤ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጆን፣ በማህፀን ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ አዲስ ሕይወት እውነተኛ አስገራሚ ስጦታ መሆኑን ከልብ መገንዘብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ብጹዕ አቡነ ጆን ሼሪንግቶን በመጨረሻም የጨቅላ ሕጻናት እና የነፍሰ ጡር እናቶች ደህንነት በመንከባከብ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ለሚገኙት የጤና ባለሞያዎች በሙሉ፣ ከእንግሊዝ እና ዌልስ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተላከላቸውን ምስጋና አቅርበውላቸዋል።   

28 May 2020, 18:21