ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸሎት ሲያደርሱ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ጸሎት ሲያደርሱ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “በመከራ ጊዜ ጸሎታችንን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቅርብ”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረብዕ ሚያዝያ 28/2012 ዓ. ም. የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ በዚህ የመከራ ወቅት ምዕመናን በሙሉ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ዓርብ ሚያዝያ 30/2012 ዓ. ም. የአርጀንቲና ባልደረባ የሆነች፣ የሉያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ዕለት መሆኑን አስታውሰው፣ በተመሳሳይ ዕለት በጣሊያን አገርም ወደ ፖምፔይ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት የሚቀርብበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል።

የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል፣
የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል፣

የቫቲካን ዜና

ዓርብ ሚያዝያ 30/2012 ዓ. ም. የአርጀንቲና ባልደረባ የሆነች የሉያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት መሆኑን ለስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አስታውሰው፣ መላው ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በሚገኝበት በዚህ ወቅት ጸሎታችንን ተቀብላ ወደ ልጇ ዘንድ በማቅረብ የምህረት እና የፈውስ ጸጋን እንድታስገኝልን ጸሎታችንን እናቅርብ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአርጄንቲና ዋና ከተማ ቦይነስ አይረስ በቅርብ ርቀት ወደ ሚገኝ የሉያና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ተደጋጋሚ መንፈሳዊ ጉዞን በማድረግ ጸሎት ያደረጉበት ቅዱስ ሥፍራ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በቅርቡ ለሉያናው ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ሼይኒግ በጻፉት መልዕክት፣ በሚያዝያ 30 ቀን በሚከበረው የሉያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ከመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመሆን ጸሎታቸውን ለማቅረብ የሚፈልጉ ቢሆንም የሚገኙበት ጊዜ ለዚህ አመቺ አለመሆኑን ገልጸው፣ በመንፈስ አብሮአቸው በመሆን በጸሎት የሚተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም “እርሷ እንድትመለከተኝ በጸሎቴ እማጸናታለሁ” ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 28/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ወቅት ለጣሊያንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዓርብ ሚያዝያ 30/2012 ዓ. ም. በደቡብ ጣሊያን በሚገኝ የፖምፔይ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ጸሎት የሚቀርብበት ዕለት መሆኑን አስታውሰው፣ ምዕመናን በመንፈስ በመተባበር ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል። “ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምናቀርበው የመማጸኛ ጸሎት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን እና ለመላው ዓለም ሰላሙን እና ምሕረቱን እንዲሰጠን እንጠይቅ” ብለዋል።

በዓመት ሁለት ጊዜ፣ ሚያዝያ 30 እና በጥቅምት ወር የመጀመሪያ እሑድ በጣሊያን ውስጥ ፖምፔይ በሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ፣ ለመላው ዓለም ምዕመናን የጋራ ጸሎት የሚቀርቡባቸው ቀናት መሆኑ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መጋቢት 21/2015 ዓ. ም. በጣሊያን፣ የፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስን ሲጎበኙ 5ኛው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸው ታውቋል።

07 May 2020, 18:39