ፈልግ

ቅዱስነታቸው በጣሊያን ከተማ ባሪ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ሲቀበሉ፤ ቅዱስነታቸው በጣሊያን ከተማ ባሪ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ሲቀበሉ፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለክርስቲያኖች አንድነት የተደረጉ በርካታ ጥረቶችን ማድነቃቸው ተገለጸ።

“አንድ ስለ መሆን” የሚለውን የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን 25ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ለሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ለክርስቲያኖች አንድነት እስካሁን የተደረጉ በርካታ ጥረቶችን አስታውሰው፣ ወደ ፊትም የበለጠ ጥረት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ ከ25 ዓመት በፊት “አንድ ስለ መሆን” በሚል ርዕስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ያበረከቱትን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን አስታውሰዋቸዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ሙሉ አንድነትን በመሻት ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የጋራ ጉዞ ከፍተኛ ጥረትን የጠየቀ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለበርካታ ዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን ለማስወገድ በተለይም ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ወዲህ የተደረጉ ብዙ ጥረቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ባለፉት አሥርተ ዓመታ ውስጥ ለተደረጉት ጥረቶች እና ለተገኙት መልካም ውጤቶች እግዚአብሔርን አመስግነዋል።   

የቤተክርስቲያን የአንድነት ጥረት ወደ ኋላ የሚታጠፍ አይደለም፣

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ቤተክርስቲያን ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን በምታደርገው ጉዞ ከመስራቿ የተቀበለችውን የአንድነት ጸሎት በሚገባ አስታውሳው እንድታቀርብ መመኘታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ “አንድ ስለ መሆን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በጻፉበት ወቅትም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለክርስቲያኖች አንድነት የምታደርገውን ጥረት ወደ ኋላ የማትለው መሆኑን አስታውሰዋል። በጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ እርገት መታሰቢያ ዕለት ይፋ የሆነው ቃለ ምዕዳን፣ በልዩነት መካከል አንድነትን የሚፈጥር የመንፈስ ቅዱስ ተግባር መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “አንድ ስለ መሆን” የተሰኘው ቃለ ምዕዳን 25ኛ ዓመት በምናከብርበት ባሁኑ ወቅት መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ለአንድነት በርትቶው እንዲሠራ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።

መንፈስ ቅዱስ ልዩነትን በማስወገድ አንድነትን ያጠናክራል፣

አንድነትን መልሶ ለመገንባት የተደረገውን ውሳኔ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ ለተመሠረቱት እንቅስቃሴዎች እውቅናን በመስጠት በልዩነት መካከል አንድነትን ለማምጣት ከመንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን የተሰጡ የጸጋ ስጦታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። “አንድ ስለ መሆን” በሚል ርዕስ ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታዩ አንዳንድ ልዩነቶችን ለመቃወም ሳይሆን የወንድማማችነትን ተልዕኮ ለማጠናከር እገዛን ያደረገ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ኅዳር 29/2014 ዓ. ም. ወደ እስታምቡል ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ካቶሊካዊ ካቴድራል ያሰሙትን ስብከት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በልዩነት መካከል ፍቅርን፣ ብዝሃነትን በማጠናከር ወደ አንድነት የሚመራው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስረድተው፣ መንፈስ ቅዱስ የሰላም መሰረት በመሆኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ ስምምነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ለክርስቲያኖች አንድነት የበለጠ ጥረት ማድረግ እንችላለን፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ በላኩት መልዕክት፣ ባለፉት አሥርተ ዓመታ ውስጥ ለተደረጉት ጥረቶች እና ለተገኙት መልካም ውጤቶች እግዚአብሔርን አመስግነዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የክርስቲያኖች አንድነት ጥረት በሙሉ ልባቸው የሚጋሩ መሆናቸውን ገልጸው እምነትን በማሳደግ እና አንዱ ለሌላው ዕውቅናን በመስጠት፣ የተፈጠረውን ቁስል ለመጠገን የተደረጉ በርካታ ጥረቶችን አስታውሰዋል።

ቅዱስ ቁርባንን በጋራ ለምካፈል የተደረጉ ጥረቶች፣

በበርካታ ሥነ መለኮታዊ እና የቸርነት ሂደቶች ላይ የጋራ ውይይቶች ተደርጎባቸው መልካም ውጤቶች መገኘታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ለጋራ ውይይቶች፣ ሐዋርያዊ እና ባሕላዊ አገልግሎቶችን በሕብረት ለማከናወን  መልካም ፍላጎቶች መታየታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።         

የክርስቲያኖች አንድነት ማጠናከሪያ መጽሔት ስርጭት፣

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምስጋናቸውን በድጋሚ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ውስጥ ተጨማሪ ሁለት የተግባር መርሃ ግብሮች የሚታከሉ መሆኑን ገልጸው፣ እነርሱም ብጹዓን ጳጳሳት በየሃገረ ስብከታቸው የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተው፣ ሁለተኛው በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን የያዘ መጽሔት ለብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ማዳረስ መሆኑን ገልጸዋል።

የክርስቲያኖች አንድነት መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው፣

የክርስቲያኖች አንድነት በቀዳሚነት የሰዎች ሥራ ውጤት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን አስረድተው፣ የክርስቲያኖች አንድነት እንደ ተዓምር የሚታይ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የአንድነት ጉዞ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል የበለጠ የቸርነት ተግባር ይገለጥ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የላኩትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ ለክርስቲያኖች አንደነት የሚደረገውን ጥረት መንፈስ ቅዱስ እንዲመራው ጸሎታቸውን አቅርበው፣ መላው ዓለም እምነትን እንዲያገኝ በኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል የበለጠ የቸርነት ተግባር እንዲገለጥ፣ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርብ የውዳሴ ጸሎትም እንዲጨምር በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።        

26 May 2020, 17:44