ፈልግ

በፖርቱጋ፣ ፋጢማ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ቅዱስ ምስል በኡደት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ በፖርቱጋ፣ ፋጢማ የእመቤታችን ድንግል ማሪያም ቅዱስ ምስል በኡደት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሰላም እንዲነግሥ፣ ወረርሽኙም እንዲቆም የማርያምን እርዳታ እንጠይቅ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ ሰላም እንዲወርድ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም የእመቤታችን ቅድስት ማርያም እርዳታን በጸሎት እንጠይቅ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ እንደገለጹት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1917 ዓ. ም. በፖርቱጋል አገር፣ ፋጢማ በምትባል መንደር ውስጥ ብጽዕት ድንግል ማርያም ለሦስቱ እረኞች የታየችበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል። ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ አውጉስቶ ዶስ ሳንቶስ የተመራው የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት እና የፋጢማ እመቤታችን ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ካርሎስ ካቤቺናስ መልዕክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ በቪዲዮ ምስል አማካይነት ለምዕመናን በቀጥታ የተሰራጨ መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በፖርቱጋል፣ ፋጢማ በምትባል መንደር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሦስት እረኞቹ የታየችው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1917 ዓ. ም. መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው በማከልም ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራ የማያቋርጥ ፍቅር ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

ለወጥ የሚገኝበት መንገድ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 5/2012 ዓ.ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ ለፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች ሰላምታቸውን ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ እና ቤተክርስቲያንም እንደምትመክረን በያዝነው የግንቦት ወር ምዕመናን በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት በመድገም ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በእመቤታችን ጥበቃ ሥር ከሆንን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት የምንከተል ከሆነ የሚደርስብንን ስቃይ እና መከራ በትዕግስ መሻገር እንችላለን ብለው፣ ዘወትር ከእመቤታችን ጋር በጸሎት የምንተባበር ከሆነ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመድረስ በምናደርገው የለውጥ ጉዞ ቅድስት ማርያም ታግዘናለች ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና የፋጢማው ቅድስት ማርያም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ግልጸት በማስታወስ ለፖላንድ ምዕመናን ባቀረቡበት የሰላምታ መልዕክታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመላው ዓለም ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1981 ዓ. ም. የተቃጣባቸውን የግድያ ሙከራ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃ ለመትረፍ እንደቻሉ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ወደ እግዚአብሔር አብ በምናቀርበው ጸሎት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በዓለማችን ሰላም እንዲወርድ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም፣ የንስሐ እና የመለወጥ መንፈስ እንጠይቅ ብለዋል።

የብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ አጉስቶ ሰላምታ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ለመላው ዓለም ምዕመናን ልባዊ ሰላምታቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል። በተመሳሳይ መልኩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ በሚል ስጋት በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. የተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት በቪዲዮ ምስል በኩል ለምዕመናን የተሰራጨ መሆኑ ታውቋል። በፖርቱጋል በዕለቱ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው እና በልበ ኢየሱስ እና በልበ ማርያም ስም የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ንግደት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሰረዙ ታውቋል። ትናንት ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን የቀረበውን ዓለም አቀፍ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት የሊዬሪያ-ፋጢማ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ አጉስቶ ዶስ ሳንቶስ ማርቶ ሲሆኑ፣ መስዋዕተ ቅዳሴው በሚካሄድበት ሰዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ሐዋርያዊ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ አጉስቶ ዶስ ሳንቶስ ማርቶ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ላልቻሉት የጣሊያን ምዕመናን በሙሉ በቫቲካን ሬዲዮ በኩል ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።  

የፋጢማ እመቤታችን ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን መልዕክት፣

የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ካርሎስ ካቤቺናስ በቪዲዮ ምስል አማካይነት ለመላው ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ በግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በፋጢማ እመቤታችን መቅደስ በተካሄደው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የመላው ዓለም ምዕመና በመንፈስ መተባበራቸውን ገልጸው፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1917 ዓ. ም. አካባቢው በወረርሽኝ መጠቃቱን አስታውሰዋል። “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ፋጢማ የተስፋ መልዕክትን ይዛ መጥታለች” ያሉት ክቡር አባ ካርሎስ፣ ያን ጊዜም ቢሆን ዓለማችን በከባድ ችግር የወደቀ መሆኑን አስታውሰዋል። የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የተስፋ መልዕክት ለመላው የዓለም ሕዝብ ነው ብለው፣ ዘንድሮ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበው ጸሎትም በፋጢማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ ተመልሰን ለመምጣት ብርታትን እና ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ተስፋ በመታገዝ ሁላችን በድጋሚ ተገናኝተን አብረን እምነታችንን ለማክበር እንሰበሰባለን በማለት ክቡር አባ ካርሎስ ምኞታቸውን ገልጸዋል።    

14 May 2020, 19:18