ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቻይና ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ጸሎት አደረጉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት  16/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ሕንጻ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ በእለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በተለይም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳበት የትንሳኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግስት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ እርሱ እንደ ተናገረው ከሙታን ተነስቷል” የሚለውን ጸሎት እኩለ ቀን ላይ ከደገሙ በኋላ እንደ ተለመደው ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልዕክት በቻይና ውስጥ ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ጸሎት ማድረግ እንደ ሚገባ ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና

ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን ሲቀጥሉ “ዛሬ በተለይም በልዩ ክብር በቻይና በመከበር ላይ የሚገኘው  የክርስቲያኖች ረዳት እና የቻይና ጠባቂ የሆነችው በሻንጋይ በሚገኘው የሻሻም የመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ውስጥ አመታዊ በዓል እየተከበረ በመሆኑ በጸሎት መንፈስ ከቻይና ክርስቲያኖች ጋር ልንሆን ይገባል” ማለታቸው ተገልጿል።

በእምነት እና በወንድማማችነት መንፈስ ሕብረት እንዲፈጥሩ፣ ደስተኛ የሆኑ የቅዱስ ወንጌል መስካሪዎች እና የበጎ አድራጎት እና በወንድማማችነት መንፈስ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ተግባራትን እንዲያከናውኑ፣ ጥሩ ዜጎች መሆናቸውን እንዲቀጥሉ በእዚያ ታላቅ ሀገር ውስጥ ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያን አባቶችን እና ምዕመናንን ሰማያዊቷ እናታችን እንድትመራቸው እና በጥበቃዋ ሥር እንድታደርጋቸው ለማርያም በአደራ እንሰጣቸዋለን ብለዋል።

“በቻይና የሚትገኙ ውድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የሆናችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ እናንተንም ባካተተ መልኩ የተዋቀረችው ዓለማቀፋዊት የሆነችው ቤተክርስቲያን ተስፋዎቻችሁን እንደምትጋራ እና በህይወት ፈተናዎች ውስጥ በምትገቡበት ወቅት ሁሉ ድጋፋችን እንደ ማይለያችሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ የማዳን ኃይል ያለውን  የእግዚአብሔር ኃይል የሆነው የቅዱስ ወንጌል ብርሃን እና ውበት ፣ በውስጣችሁ እንዲያንጸባርቅ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተገኙ ዘንድ በጸሎቴ ከእናንተ ጋር ነኝ ብለዋል። ለእናንተ ለሁላችሁም የእኔን ታላቅ እና እውነተኛ ፍቅር በድጋሚ በመግለጽ ፣ ልዩ ሐዋርያዊ ቡራኬን እየሰጠዋችሁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁልጊዜ ትጠብቃችሁ ዘንድ ጸሎቴ ነው ብለዋል።

በእየአመቱ በግንቦት 16 ቀን በካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ የክርስቲያኖች ረዳት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አመታዊ በዓል በዓለማቀፍ ደረጃ እንደ ሚከበር ይታወቃል። ይህ የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አመታዊ በዓል በቻይና በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በከፍተኛ አክብሮት እና መንፈሳዊነት እንደ ሚከበር የሚታወቅ ሲሆን በቻይና በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ “የክርስትያኖች ረዳት በሆነችው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የተገነባ ቤተመቅደስ በቻይና እንደ ሚገኝ ይታወቃል። ይህ ቤተመቅደስ “የሻሻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ሲሆን በእየአመቱ በግንቦት 16 ቀን የሚከበር አመታዊ በዓል ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባለፈው አመት በቻይና በሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የእምቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “በቻይና የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን በየቀኑ በብዙ ፈተናዎች እና መከራዎች ቢደርሱባቸውም ነገር ግን በእመነታቸው እስካሁን ድረስ ጸንተው ለሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን  ሁሉ ያለኝን ልዩ ቅርበትና ፍቅር እንድገልጽ ግድ ይለኛል። በቻይና የምትገኙ ውድ ወንድሞቼ ሰማያዊ እናታችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለማቀፋዊቷን ቤተክርስቲያን ከግምት ባስገባ መልኩ የበጎነት እና የወንድማማችነት ፍቅር መስካሪዎች ትሆኑ ዘንድ እንድትረዳችሁ እጸልያለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በወቅቱ በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት “በቻይና የምትገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ምዕመናን ምንም እንኳን ጌታን በአገራችሁ ለመመስከር ከፍተኛ የሆነ ችግር እና ተግዳሮት እያገጠማችሁ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን በጌታ እርዳታ ክርስቶስን መመስከር ትቀጥሉ ዘንድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን ለእናንተ ጸሎት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን “የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርዳታዋን በፍጹም አታቋርጥም፣ በእናትነት ፍቅሯ እናንተን መደገፉና ትቀጥላለች” በማለት አክለው መግለጻቸው ይታወሳል።

24 May 2020, 10:21