ፈልግ

ሕጻኑ ካሮል ዎይቲላ ከወላጅ እናቱ ወይዘሮ ኤሚሊያ ጋር፣ ሕጻኑ ካሮል ዎይቲላ ከወላጅ እናቱ ወይዘሮ ኤሚሊያ ጋር፣ 

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና የወላጆቻቸው የእምነት ጥንካሬ።

ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ልደት መቶኛ ዓመትን እና ቤተ ሰባቸውን በዛሬው ዕለት አስባ መዋሏ ተገለጸ። መላው ቤተሰብ በእግዚአብሔር ላይ ጠንካራ እምነትን ያኖረ፣  ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ አክብሮት የነበረው እና የመስዋዕትነትን ትርጉም በመረዳት ሕይወቱን ለሌሎች ፍቅር አሳልፎ የሰጠ መሆኑ ተንግሯል።

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 27/2014 ዓ. ም. ሁለቱን የቀድሞ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳትን ማለትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ቅድስና ባወጁበት ዕለት ባሰሙት ንግግር “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያገለገሉ ታላቅ የቤተክርስቲያን መሪ ነበሩ” ማለታቸው የልደታቸውን መቶኛ ዓመት በምናከብርበት በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሥፍራ የተሰጠው መሆኑ ታውቋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ምድራዊ ሕይወት በምናስታውስበት ጊዜ የልጅነት አስተዳደጋቸው ምን እንደሚመስል እና የወላጆቻቸው የሕይወት ምስጢር ምን እንደ ነበር ለማየት ማነሳሳቱ ታውቋል። በዚህ ምክንያት ከግንቦት 3/2012 ዓ. ም. ጀምሮ በፖላንድ አገር የወላጆቻቸውን የሕይወት ታሪክ በማጥናት ለብጽዕና ደረጃ የሚያደርስ አካል በሀገረ ስብከት ደረጃ መቋቋሙ ታውቋል። የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወላጆች የሆኑት የወይዘሮ ኤሚሊያ እና የአቶ ካሮል አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ የሕይወት ምስክርነት በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መንፈሳዊ አስተዳደግ እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት መብቃት ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተ መሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 18/1920 ዓ. ም. በደቡብ ፖላንድ፣ ክራኮቪያ ከተማ አጠገብ፣ ቫዶቪች በምትባል መንደር የተወለዱት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በወላጆቻቸው በኩል የተደረገላቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ ድጋፍ በክህነት ሕይወታቸው፣ የክራኮቪያ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ እና የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው እስከ ተመረጡበት ጊዜ ድረስ ሁሉ የረዳቸው መሆኑ ታውቋል።

ወላጅ እናታቸውን በሞት ሲለዩአቸው ዘጠኝ ዓመት የነበራቸው ካሮል ወይቲላ፣ በበጋው ወራት መጀመሪያ ላይ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር 1939 ዓ. ም. የእናታቸውን ሞት በማስታውስ በጻፉት ግጥም “በነጭ መካነ መቃብርሽ ላይ ነጭ የሕይወት አበቦች ያብባሉ፤ አንቺን ሳናይሽ ብዙ ዓመታት አልፉ” ማለታቸው ይታወሳል። የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እናት ኤሚሊያ፣ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ከባድ የሕይወት ፈተናዎችን ያለፉ፣ ለልጃቸው መልካም በመጨነቅ ለዘጠኝ ዓመታት ብዙ የለፉ መሆናቸው ታውቋል።

በበርካታ ፈተና ውስጥ የሚገኘውን የሰው ልጅ ሕይወት ከአደጋ መከላከል የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አገልግሎት ወሰን ከሌለው የእናት ፍቅር ያገኙት ውስጣዊ ብርታት መሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮስውያኑ የቀን አቆጣጠር 1995 ዓ. ም. ብጽዕናቸው የታወጀላቸው፣ ቀጥሎም በ2004 ዓ. ም. ቅድስናቸው የታወጀላቸው ጃና ቤረታ ሞላ፣ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እናት የሆኑት የወይዘሮ ኤሚሊያ መልካም ምሳሌነት በማስታወስ እንደተናገሩት፣ ወይዘሮ ኤሚሊያ የልጃቸውን ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የሌሎች እናቶች ሕይወት ምሳሌ በመሆን የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉት ወይዘሮ ኤሚሊያ ካዞሮስካ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በመተባበር፣ “የብቸኛ እናት ቤት” በመባል የሚጠራ ቤት በስጦታ ማበርከታቸው ይታወሳል። “ለሰው ልጅ ሕይወት ክብርን በመስጠት ላቀረባችሁት ክቡር ስጦታ አመሰግናለሁ፤ ይህ ቤት በእናቴ ስም እንዲጠራ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በሰኔ ወር 1999 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የአካባቢውን ነዋሪ ማመስገናቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዕለቱ ባሰሙት ንግግር፣ ወደዚህ ዓለም እንድመጣ ያደረገችኝ እና በልጅነት ሕይወቴ በፍቅር ተንከባክባ ያሳደገችኝ እናቴ፣ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ወቅትም በመንፈስ ሆና የምታግዘኝ መሆኑን አምናለሁ” ማለታቸው ይታወሳል። እናታቸው ካረፉ ከሦስት ዓመት በኋላ ታላቅ ወንድማቸውን በ26 ዓመት ዕድሜው በአሰቃቂ ሁኔታ ያጡት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ለወንድማቸው ከፍተኛ አድናቆት ያነበራቸው መሆኑ ታውቋል። የሕክምና አገልግሎትን በማበርከት ላይ እያለ የሞተው ወንድማቸው፣ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ለሞት አደጋ ራሳቸውን እንዳጋለጡ በርካታ የሕክምና ባለሞያች የሚታወስ መሆኑን ታውቋል። በክራኮቪያ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1932 ዓ. ም. የሕክምና አገልግሎት ለማበርከት የወሰነው ወንድማቸው ኤድሙንድ፣ መድኃኒት ባልነበረው ጊዜ በትኩሳት የምትሰቃይ ወጣት በማከም ላይ እያለ ለሞት የተጋለጠ መሆኑ ታውቋል። ሕመሙ መድኃኒት እንደሌለው ጠንቅቆ ቢያውቅም ለራሱ ሕይወት ሳይራራ ሌሎችን ከሞት ለማዳን በማለት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። የወንድማቸው ዕረፍት ከፍተኛ ድንጋጤን ያስከተለባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ምንም እንኳን በዕድሜ ጠና ካሉ በኋላ ቢሆንም፣ ወንድማቸው የሰማዕትነት ሞት እንደ ሞተ በአዕምሮአቸው እንዲያስታውሱ ያደረጋቸው መሆኑ ታውቋል። ከእናታቸው ሞት በኋላ ታላቅ ወንድማቸው ኤድሞንድ ዘወትር እየተንከባከባቸው፣ በትምህርት እንዲበረቱ በመርዳት እና ኳስ መጫወትን ያስተማሯቸው መሆኑ ታውቋል።

እናታቸውን እና ታላቅ ወንድማቸውን በሞት ያጡት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ12 ዓመት ዕድሜአቸው፣ የፖላንድ መንግሥት ወታደር ከሆኑት ወላጅ አባታቸው ጋር የኖሩ መሆናቸው ይታወሳል። አባታቸውም እንደ ሌሎች የቤተሰብ አባላት በእምነት ጠንካራ የነበሩ፣ በሕይወታቸው የተለያዩ ችግሮች ያጋጠሟቸው ቢሆንም ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ በማሳደግ፣ በተለይም ታማኝነትን፣ የአገር ፍቅርን እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት እንዲኖረው በማስተማር ያሳደጉ ብርቱ አባት መሆናቸው ይታወሳል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጻፉት የሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው እንደገለጹት አባታቸው በወጣትነት ዕድሜያቸው ወቅት ለክርስቲያናዊ ሕይወት በኋላም ለክህነት ጥሪ መጎልበት ያበረከቱት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የወጣትነት ዕድሜአቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያሳደሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በክራኮቪያ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እያሉ የፖላንድ ጦር ከናዚ ጦር ጋር ባደረገው ጦርነት አባታቸውን በሞት ያጡ መሆናቸው ታውቋል። በ21 ዓመት ዕድሜ ወላጅ አባታቸውንም በሞት ያጡት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሕይወት ያጋጠሟቸውን ከፍተኛ ሐዘኖች ተሻግረው ሕይወታቸውን በሙሉ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠው መነሳታቸው ይታወሳል። ይህን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለቅድስና የበቁት በወላጆቻቸው ብርታት እና በእምነት ጥንካሬው መሆኑን አስታውሰው፣ የወንጌልን መልካም ዜናን ለመመስከር ወደ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ የቤተሰባቸውን የሕይወት ማዳን ተልዕኮን ፣ ለሌሎች ሲሉ ሕይወታቸውን በድፍረት አሳልፎ መስጠትን የተማሩ እና ልባቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክፍት ያደረጉ ሐዋርያዊ አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

18 May 2020, 15:13