ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በኮሮና ቫይረስ የታመሙትን ሰዎች በጸሎቴ ማስታወስ እፈልጋለሁ” አሉ!
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው ሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓ.ም ቅዱስ የሆነው የሕማማት ሳምንት እንደ ሚጀመር ይታወቃል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ አምልኮ ደንብ መሰረት እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ መሰጠቱን፣ መንገላታቱን፣ በመስቀል ላይ እንደ ሌባ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን እና ከሙታን መነሳቱ . . . ወዘተ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተከናወኑባቸው ሦስት ዋና ዋና ቀኖች በተለየ ሁኔታ በታላቅ መንፍሳዊነት ይከበራሉ።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
በመጪው እሁድ መጋቢት 27/2012 ዓ.ም ኢየሱስ በታላቅ ክብር መከራውን ለመቀበል ወደ ኢየሩስአሌም የገባበት የሆሳዕና በዓል ከተከበረ በኋላ የሕማምት ሳምንት ይጀመራል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለእዚህ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጪው ሰኞ መጋቢት 28/2012 ዓ.ም የሚጀመረውን የሕማማት ሳምን አስመልክተው ለመላው ምዕመን ባስተላለፉት መልእክት “በኮሮና ቫይረስ የታመሙት እና በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በጸሎቴ ማስታወስ እፈልጋለሁ” ማለታቸው ተገልጹዋል።
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅርቡ የሚጀመረውን የሕማማት ሳምንት አስመልክተው በመጋቢት 25/2012 ዓ.ም ምሽት ላይ በቪዲዮ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።
የተወደዳችሁ ጓደኞቼ እንደምን አመሻችሁ!
ዛሬ ምሽት ከወትሮው በተለየ መንገድ ወደ እየቤታችሁ ለመግባት እድሉን አግኝቻለሁ። ከፈቀዱችሁልኝ ደግሞ በዚህ የችግር እና የመከራ ጊዜ ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ከእናንተ ጋር ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ። ተላላፊ የሆነውን ይህንን በሽታ ለማስወገድ ይቻል ዘንድ እናንተ እና ቤተሰቦቻችሁ ያለመዳችሁት ዓይነት ሕይወት በመኖር ላይ እንደ ምትገኙ እገምታለሁ። ወደ ውጪ መውጣት ያልቻሉ፣ ትምሕርት ቤት በመሄድ ትምሕርታቸውን መከታተል ያልቻሉ፣ እለታዊ ሕይወታቸውን መምራት ያልቻሉ፣ የሕፃናትና ወጣቶች የኑሮ ሁኔታ እያሰላሰልኩ እገኛለሁ። ሁሉንም ቤተሰቦች በተለይ ደግሞ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በእዚህ በኮሮና ቫይረስ በሽታ ተይዘው የታመሙባቸውን ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሀዘን የደረሰባቸውን ሰዎች በሙሉ በልቤ ውስጥ አስባቸዋለሁ። በእነዚህ ቀናት ውስጥ በብቸኝነት የሚኖሩ ሰዎችን እና ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ መጋፈጥ አቅቶዋቸው የሚገኙ ሰዎች ኑሮ ለእነርሱ ይበልጥ ከባድ ስለሆነ ብዙ ጊዜ አስባቸዋለሁ። ከሁሉም በላይ ለእኔ በጣም ውድ ስለሆኑት አዛውንቶች አስባለሁ።
በኮሮና ቫይረስ የታመሙት እና በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ማሳታወስ እፈልጋለሁ። የራሳቸውን ሕይወት ለአደጋ በማጋለጥ በእዚህ ወረርሽኝ የተያዙትን ሰዎች ለማከም ተጋላጭ በሆነ ሁኔታ የሕክምና አጋልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትን ወይም ለሕብረተሰቡ አስፈላጊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ዋስትና በመስጠት ላይ የሚገኙ ሰዎችን ልግስና እውቅና ልሰጥ እፈልጋለሁ። ብዙ ጀግኖች በየቀኑ እና በየሰዓቱ እየፈለቁ ነው! በተጨማሪም የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ የሚገኙትን፣ ለሥራቸው እና ለወደፊቱ ሕይወት በመጨነቅ ላይ የሚገኙትን ብዙ ሰዎች በልቤ አስባለሁ። በተጨማሪም የበሽታውን ወረርሽኝ በመፍራት ለራሳቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሳይቀር በማሰብ በጭንቀት ውስጥ የሚገኙትን የሕግ ታራሚዎች መከራ እጋራለሁ፣ ራሳቸውን ከበሽታው ወረርሽኝ መከላከል የሚይስችል የመኖሪያ ቤት የሌላቸውን ሰዎች በልቤ አስባለሁ።
ለሁሉም ሰው አስቸጋሪ ጊዜ ነው። ለብዙዎች እጅግ በጣም ከባድ የሆነ ጊዜ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን በሚገባ ይረዱታል እናም በእዚህ መልእክቴ ከሁሉም ሰዎች ጋር በሐሳብ እና በፍቅር ከእናንተ ጋር መሆኔን ለመናገር እፈልጋለሁ። የምንችለውን ያህል ጊዜውን ለመጠቀም እንሞክር -ለጋስ እንሁን፣ በአካባቢያችን የሚገኙትን ችግረኞች እንርዳ። ብቸኝነት የሚሰማቸውን ሰዎች ምናልባትም በስልክ ወይም ማህበራዊ አውታረመረቦችን ተጠቅመን እንፈልግ፤ በጣሊያን እና በዓለም ውስጥ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ። ምንም እንኳን ተገልለን በየቤታችን ውስጥ የምንኖር ቢሆንም ሀሳብ እና መንፈስ ከፍቅር ጋር በመሆን ርቆ መራመድ ይችላል። ዛሬ የምንፈልገው ይህ ነው -ፍቅር! ዛሬ የሚያስፈልገው ይህ ነው-ፍቅራችንን ለሰዎች መግለጽ።
ወሰን የሌለው የእግዚአብሔር የፍቅር መልእክት የሚገለጸው እና የቅዱስ ወንጌል መልእክት የሚጠቃለልበት ቅዱስ የሆነ የሕማማት ሳምንት ዘንድሮ በእውነቱ ባልተለመደ ሁኔታ እናከብራለን። በከተሞቻችን ዝምታ ውስጥ የፋሲካ ወንጌል ማስተጋባት ይጀምራል። ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል: - "በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ” (2 ቆሮ 5. 15)። ከሙታን በተነሳው በኢየሱስ አማካይነት ሕይወት ሞትን ድል አደረገ። ይህ የፋሲካ እመነት ተስፋችንን ያበለጽጋል። በዚህ ምሽት ላጋራችሁ የምፈልገው ይህንኑ ነው። የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማደረጉ ነው መልካም የሚሆነው፣ በመጨረሻም ከክፉ እና ከዚህ ወረርሽኝ ነፃ የምንሆንበት የተሻለን ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማደረግ ነው። ተስፋ አያሳፍረንም፣ ተስፋ ቅዤት አይደለም፣ ተስፋ ተስፋ ነው እንጂ።
አንዳችን ከሌላው ጎን በፍቅር እና በትዕግስት በመቆም በእነዚህ ቀናት ውስጥ በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀት እንችላለን። ወደ እየቤታችሁ እንድገባ ስለፈቀዳችሁልኝ አመሰግናለሁ። ለተሰቃዩ ፣ ለህፃናት እና ለአዛውንቶች የርህራሄ መገለጫ የሆኑ ተግባራትን አድርጉ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለእነርሱ ቅርብ እንደ ሆኑ እና በጸሎት አብረዋችው እንደ ሆኑ፣ ጌታ በቅርቡ ሁሉንም ከክፉ እንደሚያድን ንገሩዋቸው። ለእኔም ጸልዩልኝ። መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ። በቅርቡ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ!