ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ከኢየሱስ ጋር ሁሉንም ፈታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ እንችላለን” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 18/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴ ካሳረጉ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት ከሚደገሙ ጸሎቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና በተለይም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሳበት የትንሳኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ድረስ የሚደገመውን “የሰማይ ንግስት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ እርሱ እንደ ተናገረው ከሙታን ተነስቷል” የሚለውን ጸሎት በስፍራው ከተገኙ ምዕመናን ጋር በመቀባበል ከደገሙ በኋላ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል (24፡13-35) ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱ በኢየሱስ ሞት ምክንያት አዝነው ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ በነበሩበት ወቅት ኢየሱስ አብሮዋቸው መጓዙን፣ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የእግዚአብሔርን መንገድ እንጂ የራሳችንን መንገድ አንምረጥ፣ ከኢየሱስ ጋር ሁሉንም ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎችን መጋፈጥ እንችላለን” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለተ ሰንበት የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል በፋሲካ ቀን የነበረውን ሁኔታ የሚገልጽ ሲሆን ስለ ሁለቱ ዝነኛ የኤማሁስ ደቀመዛሙርት ታሪክ ይናገራል (ሉቃ 24 13-35)። በመንገድ ላይ የሚጀመር እና በመንገድ ላይ የሚያበቃ ታሪክ ነው። በእርግጥ  ስለኢየሱስ ታሪክ በማሰብ እያዘኑ የነበሩ፣ ኢየሩሳሌምን ትተው አሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደ ሚገኘው ቤታቸው  ወደ ኤማሁስ በእግራቸው የሚጓዙ የሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጉዞ እንመለከታለን። ይህ በአንድ መልካም ቀን ላይ ከላይ ወደ ታች የሚደረግ ጉዞ ነው። ከእዚያን በኋላ ደግሞ አሁንም ዐሥራ አንድ ኪሎሜትሮች ያህል ወደ ኋላ የመመለሻ ጉዞው አለ - ይህ ጉዞ የሚከናወነው ደግሞ በሌሊት ሲሆን ሙሉ ቀን ከላይ ወደ ታች ሲያደርጉት የነበረው ጉዞ አሁን ደግሞ ከታች ወደ ላይ ወደ ከፍታ የሚደርግ ጉዞ ነው። ሁለት ጉዞዎች - በቀን የተደረገ አንድ ቀላል የሆነ ጉዞ እና ሌላኛው ደግሞ በምሽት የተደረገ ጉዞ ነው። ነገር ግን የመጀመሪያው በሐዘን ውስጥ የተደረገ ጉዞ ሲሆን  ሁለተኛው ደግሞ በደስታ የተከናወነ ጉዞ ነበር። በመጀመሪያው ጉዞ ከጎናቸው ሆኖ አብሯቸው የሚጓዝ ጌታ ነበር፣ እነሱ ግን አላወቁትም ነበር፤ በሁለተኛው ጎዞ ግን ጌታን አላዩትም፣ ነገር ግን ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይጓዝ እንደ ነበረ ሆኖ ይሰማቸው ነበር። በመጀመሪያው ጉዞ ተስፋ ቆርጠው ነበር፣ እናም ተስፋ ቢስ ነበሩ፤ በሁለተኛው ጉዞ ውስጥ ግን ጌታ ከሙታን መነሳቱን የሚገልጽ መልካም ዜና ለሌሎች ለማብሰር ይጣደፋሉ።

የመጀመሪያዎቹ ደቀመዛሙርት የተጓዙበት ሁለት የተለያዩ መንገዶች ለእኛ በዛሬ ዘመን ለምንገኘው የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በሕይወታችን ውስጥ ሁለት ተቃራኒ አቅጣጫዎች እንዳሉ ይነግሩናል፤ እነደነዚያ ሁለት የኤማሁስ ደቀመዛሙርት በሕይወታችን ውስጥ በገጠሙን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሽባ ሆነን አዝነን ወደ ፊት የምንጓዝበት አንድ መንገድ እንዳለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳችንን እና ችግሮቻችንን ሳይሆን ነገር ግን እኛን የሚጎበኘንን ኢየሱስን እና የእርሱን ጉብኝት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን ወንድሞች፣ የእርሱን እንክብካቤ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ማለት ነው፣ የማይያስቀድሙ ሰዎች መንገድ አለ። እዚህ ላይ የሚመጣው ለውጥ ይህ ነው- በራሳችን ዛቢያ ዙሪያ መሽከርከር እናቁም፣ ተስፋ የቆረጥንባቸው ያለፉ ጊዜያት፣ ያልተሟሉ ሀሳቦች፣ በሕይወታችን ውስጥ ተከስተው የነበሩ ብዙ መጥፎ ነገሮች ዙሪያ መሽከርከር እናቁም። ብዙን ጊዜ በራሳችን ዛቢያ ዙሪያ እንሽከረከራለን፣ እንሽከረከራለን፣ እንሽከረከራለን። ነገር ግን እነዚያን ነገሮች ትተን የህይወትን ታላቅነት እና እውነታ በመመልከት ወደ ፊት መጓዛችንን እንቀጥል፣ ኢየሱስ ሕያው ነው ፣ ኢየሱስ ይወደናል። ይህ ትልቁ እውነታ ነው። ለሌሎች የሆነ ነገር ማድረግ እንችላለን። እሱ የሚያምር እውነታ ፣ አዎንታዊ ፣ አንጸባራቂ፣ ቆንጆ የሆነ ነገር ነው! በጉዞ ላይ የተከናወነ አንድ ሽግግር አለ፣ ስለራሴ እና ስለእኔ እውነታ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ወደ አምላኬ እውነተኛ ሐሳብ የተደረገ ሽግግር ነው። ከራሴ ወደ እርሱ የተደርገ ሽግግር። ይህ ምን ማለት ነው? ነፃ ያወጣን እርሱ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ቢሰማኝ ኖሮ ፣ እኔ የፈለኩት ዓይነት ሕይወት ቢኖረኝ ኖሮ ፣ ይህ እና ያ ቢሆረኝ ኖሮ… ወዘተ እያልን እናጉረመርማለን። ይህ “ቢሆን ኖሮ” የሚለው ቃል አይረዳንም፣ ፍሬያማ አያደርገንም፣ እኛን ወይም ሌሎችን አይረዳም። ቢሆን ኖሮ የሚለው ቃል እኛን ከሁለቱ ደቀመዛሙርት ጋር ያመሳስለናል። እነሱ ግን አዎን ወደ ሚለው ቃል ይሸጋገራሉ፣ “አዎን ጌታ ሕያው ነው ፣ እርሱ ከእኛ ጋር ይጓዛል።  ነገ ሳይሆን ዛሬ አዎ ልንል የሚገባ ሲሆን እርሱን ለማወጅ ወደ መንገዱ እንድንመለስ ይረዳናል”። "አዎ ፣ ሰዎችን ደስተኛ ለማድረግ ፣ ሰዎችን የተሻሉ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ብዙ ሰዎችን ለመርዳት ይህንን ማድረግ እችላለሁ። አዎን አዎን ፣ እችላለሁ”። ከአሉታዊ ወደ አዎንታዊ፣ ከማጉረምረም ወደ ደስታ እና ሰላም መሻገር፣ ምክንያቱም የምናጉረመርም ከሆነ ደስተኛ ልንሆን አንችልም፣ የገረጣን እንሆናለን፣ ግራጫማ የሆነ የሐዘን አየር ውስጥ እንገባለን። እናም ያ በጥሩ ሁኔታ እንድናድግ እንኳን አይረዳንም። ከራሳችን ወደ እርሱ፣ አቤቱታ ከማቅረብ በአገልግሎት ወደ ሚገኝ ደስታ መሻገር።

እኔ ከሚለው መንፈስ እግዚአብሔር ወደ ሚለው መንፈስ የተደርገው ሽግግር በደቀመዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ እንዴት ነበር የተከናወነው? ኢየሱስን በመገናኘት ነበር የተከናወነው - ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች በቅድሚያ ልባቸውን ለእሱ ይከፍቱለታል፤ በዚያን ወቅት ከቅዱሳት መጽሐፍት እየጠቀሰ ሲያብራራ ይሰማሉ፤ በእዚህ ምክንያት ወደ ቤታቸው ይጋብዙታል። በቤታችን ውስጥ ልናከናውናቸው የሚገባን እና ልናከናውናቸው የምንችላቸው ሦስት እርምጃዎች አሉ - በመጀመሪያ ልባችሁን ለኢየሱስ ክፈቱ፣ ሸክሞቻችሁን፣ ድክመቶቻችሁን፣ በህይወት ውስጥ የገጠማችሁን ተስፋ መቁረጥ፣ “እንዲህ ቢሆን ኖሮ” የሚሉትን አስተሳሰቦች በሙሉ ለእርሱ በአደራ እንስጥ፣ ከእዚያን በኋላ ደግሞ ሁለተኛው እርምጃ ኢየሱስን ማዳመጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስን አንስተን ዛሬ በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 24 ውስጥ የተጠቀሰውን የወንጌል ክፍል ያንብቡ፤ በሦስተኛ ደረጃ እነዛ የኤማሁስ ደቀመዛሙርት የተጠቀሙበትን ተመሳሳይ ቃላት በመጠቀም “ኢየሱስ ሆይ ከእኛ ጋር ቆይ” (ሉቃስ 24፡29) የሚሉትን ቃላት ተጠቅመን ወደ ኢየሱስ መጸለይ ያስፈልጋል። ጌታዬ ሆይ ከእኔ ጋር ቆይ። ጌታ ሆይ ትክክለኛውን መንገድ እንድናገኝ እንድትረዳን ስለምንፈልግህ ከሁላችን ጋር ቆይ። አንተ በሌለህበት ስፍራ ጨለማ አለ።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ በህይወት ውስጥ ሁል ጊዜ በጉዞ ላይ ነን። ዓላማ አድርገን የምንጓዝበትን ነገር እንሆናለን። እናም የእግዚአብሔርን መንገድ እንጂ የራሳችንን መንገድ አንምረጥ። ቢሆን ኖሮ የሚለውን ሳይሆን አዎን የሚለውን መንገድ እንምረጥ፣ ምንም ያልተጠበቀ ነገር እንደሌለ፣ ተራራ የሚሆንብን ነገር እንደሌለ፣ ኢየሱስን መጋፈጥ የሚችል ጨለማ እንደሌለ እንረዳለን። በጉዞ ላይ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቃሉን በመቀበል መላ ሕይወቷን “እነሆኝ” በማለት ለአምላክ የሰጠቺው እርሷ፣ የአምላክን መንገድ ታሳየን።

26 April 2020, 09:29