ፈልግ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በፓኪስታን፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በፓኪስታን፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በችግር ለሚገኝ የዓለማችን ሕዝብ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሚያዝያ 4/2012 ዓ. ም. ለሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራዊ ድርጅቶች በጻፉት መልዕክት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለወደቀው የዓለም ሕዝቦች መሠረታዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው ወረርሽኙ ባስከተለው ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት የዓለማችን ሕዝብ ዕለታዊ ሕይወቱን እንኳን መምራት እያቃተው መሆኑን ገልጸው፣ መብታቸው ያልተጠበቀላቸው ሠራተኞች እና ሥራ የሌላቸው ዕለታዊ ኑሮአቸውን መምራት የሚያስችል መሠረታዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 12/2015 ዓ. ም. ወደ ላቲን አሜሪካ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በቦሊቪያ ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መሪዎች ጋር፣ በኋላም በቫቲካን ውስጥ ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 4/2012 ዓ. ም. በጻፉት መልዕክታቸው የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ተስፋፍቶ የሰውን ልጅ እያሰቃየ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ ከእነዚህ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጎን በመቆም ልዩ ትኩረትን ሰጥተው የሚያስቧቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የብዙዎችን ሕይወት እና ጤና አደጋ ላይ መጣሉን ያስታወሰው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከሥራ ገበታቸው እንዲፈናቀሉ ከማድረጉ በተጨማሪ የዓለምን ኤኮኖሚ አደጋ ላይ መጣሉን አስታውሷል። በማከልም የዓለማችንን የኤኮኖሚ ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኙ፣ በቁጥር በርካታ ከሆኑ የሰራተኛ ማሕበራት እና ሕዝባዊ እንስቃሴ ጎን በመሆን ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል።

"ዓለማችን በከፍተኛ ስጋት እና መከራ ውስጥ በሚገኝበት በእነዚህ ቀናት" በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅግ አደገኛ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቋቋም በስውር እየተፋለሙት ከሚገኙ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት ጎን በመቆም፣ ማንም ቢሆን ብቻውን ሊወጣው የማይችለው ችግር መሆኑን በመገንዘብ አንድነታችንን እና ተስፋችንን መግለጽ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እነዚህ ሕዝባዊ ተቋማት እና ማኅበራት በማከናወን ላይ ለሚገኙት መልካም ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የሕዝብን ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ላይ የሚገኙት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተገቢ እውቅናን አያገኙም ያሉት ቅዱስነታቸው ማኅበራቱ መልካም ተግባሮቻቸውን ማከናወን እና ድምጻቸውን ማሰማት ማቋረጥ የለባቸውም ብለው “ችግርን የመቋቋም ችሎታችሁ ይረዳኛል ፣ ይፈትነኛል እንዲሁም ብዙ ያስተምረኛል” ብለዋል።

የበርካታ ሰዎች ስቃይ ትኩረትን ስቧል፣

በመቶዎች ለሚቆጠሩ ልጆቻቸው በቂ የዕለት እንጀራን የሚያዘጋጁ ሴቶች ስቃይ፣ ማንም የማያውቃቸው እና በአሁኑ ሰዓት የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ሕሙማን እና አዛውንት፣ ለፍጥርታት የሚገባውን እንክብካቤ እና ጥበቃን እያደረጉ የግብርና ሥራቸውን የሚያከናውኑ፣ ያመረቱትን ምርት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የላደረጉ ገበሬዎችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የሰማዩ አባት እግዚአብሔር ከላይ በመመልከት በምድር ለምታከናውኑት መልካም ተግባራት ዋጋን በመስጠት የሚረዳቸው መሆኑን አስረድተዋል። አሁን የምንገኝበት ጊዜ በመኖሪያ ቤት እጦት ለሚሰቃዩት ድሃ ቤተሰብ አስቸጋሪ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእነዚህም መካከል ስደተኞ፣ ሰብዕዊ መብታቸውን ያጡ እና ከጎጂ ሱሶች በማገገም ላይ የሚገኙትን አስታውሰዋል።

ለሕዝብ፣ ለሕይወት እና ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያ ይስወጥ፣

ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በድጋሚ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሕብረተሰብን ከችግር ለማላቀቅ፣ በማሕበረሰቡ ላይ የሚደሰውን ስቃይ ለመቀነስ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት ለውጥ የሚያገኙበት ወቅት ነው በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ተስፋ ባደረጉት መልዕክታቸው የመንግሥትም ሆነ የገበያ ሥርዓትን የሚከተሉ ተቋማት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን እና ሌሎች ችግሮችንም ሕዝቡን በማሳወቅ ብቻ መፍትሄን ማግኘት እንደማይችል ገልጸው፣ ከምን ጊዜም በላይ ለሰው ልጅ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሕዝብ ቅድሚያን በመስጠት፣ በመካከላቸው ያለውን ሕብረት ማጠናከር እና እንክብካቤን ማድረግ እና በመካከላቸው የተፈጠረ ቁስል ካለ መጠገን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ምድራችን የምታቀርበውን ጥቅም እንዳይጋሩ የተደረጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የእነዚህ ሰዎች ጉዳት ሁለት ነው ብለው አንደኛው ከሕብረተሰቡ በሚነሳ አደጋ እና ሁለተኛው ጊዜያዊ ደስታ የሚፈጥረው የስነ ምግባር ውድቀት ነው ብለዋል። የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ፣ የልዋጭ ዕቃ ሰብሳቢዎች፣ የባሕላዊ በዓላት አስተባባሪዎች፣ በአነስተኛ የግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩት ፣ የግንባታ ሠራተኞች እና ለሰዎች የተለያዩ እንክብካቤን በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩት፣ በአጠቃላይ በዝቅተኛ የኤኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙት እና አስተማማኝ የገቢ መጠን የሌላቸው እና ወረሽኙን ለመከላከል ሲባል በቤት ውስጥ ተዘግተው እንዲቀመጡ የተደረጉት በሙሉ ችግሩ የሚበተርታባቸው መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን በምንገኝበት የችግር ወቅት ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል በማለት በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲያበቃ ሊከሰት የሚችለውን የኑሮ ሁኔታን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ገና ከጅምሩ አንዳንድ አሉታዊ ገጽታዎች መታየት ጀምረዋል ብለው፣ ይህም ሁሉ አቀፍ ሰብዓዊ እድገትን መሠረት ያደረጉ ጥረቶች የሥራ ዕድል፣ የመኖሪያ ቤት እና የእርሻ መሬት አቅርቦት የሚያስፈልግ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት፣ በቀላሉ ሊታለል የሚችል ሕሊናችን ለሰብዓዊ እና ሥነ-ምሕዳራዊ ለውጦች ቅድሚያን በመስጠት፣ የተፍጥሮ ሃብትን ለጋራ ጥቅም ከማድረግ ይልቅ ለግል ጥቅም ብቻ ለማድረግ ከማሰብ ለሰው ልጅ ሕይወት እና ክብር ቅድሚያን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሁን የምንገኝበት የስልጣኔ ደረጃ በውድድር የገበያ ሥርዓት ላይ፣ በግል ጥቅም ማስከበር ላይ ፣ መጠንን ባለፈ የፍጆታ ምርት አቅርቦት ላይ እና ተመጣጣኝ ባልሆነ የሃብት ክፍፍል ላይ ትክክለኛ ጥናት በማድረግ ተሃድሶን እንዲያደርግ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመጨረሻም ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት ጥረታቸውን በማሳደግ፣ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት ስሜት እርስ በእርስ መተጋገዝ እንዳለባቸው አሳስበው፣ በጸሎታቸው እያስታወሷቸው ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን የላኩላቸው መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።

                             

15 April 2020, 20:50