ፈልግ

ቅዱስነታቸው በመለኮታዊ ምሕረት ክብረ በዓል ዕለት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲያሳርጉ፣ ቅዱስነታቸው በመለኮታዊ ምሕረት ክብረ በዓል ዕለት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲያሳርጉ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “እንደ ቶማስ እኛም ትንሳኤያችንን እናረጋግጥ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሚያዝያ 11/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የመለኮታዊ ምሕረት ክብረ በዓል ከቫቲካን ከተማ ውጭ በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ በመንፈስ ቅዱስ ቁምስና ተገኝተው ማክበራቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት መካከል ባቀረቡት ስብከት እንደገለጹት እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ተቀብለን ለሌሎች እንድናሳይ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣርጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ሚያዝያ 4/2012 ዓ. ም. የተከበረውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሳኤ በዓል ካለፈ ከሳምንት በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የሚታወስበት ዕለት መሆኑን አስታውቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛመት በሚል ስጋት ምዕመናን ባልተገኙበት ቤተክርስቲያን ውስጥ መከናወኑ ታውቋል።

የሐዋርያው ትንሳኤ፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ ከአንድ ሳምንት በኋላም ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን “አይዞአችሁ! ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” በማለት ያጽናናቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

በአዲስ መልክ መጀመር፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ነገር በአዲስ መልክ መጀመሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ትንሳኤ የተከናወነው በእምነት እና በምሕረት መሆኑን አብራርተው በዚህ አኳኋን እግዚአብሔር ከውድቀታችን ሊያነሳን ዘወትር የሚፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል። እግዚአብሔር ይህን በማድረጉ፣ ሁል ጊዜ የሚወድቀው ልጁን ለማንሳት የተዘጋጀውን አባት ይመስላል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የእግዚአብሔር እጅ ከውድቀታችን የሚያነሳን የምሕረት እጅ መሆኑን አስረድተዋል። ዘወትር እንደምንወድቅ እግዚአብሔር ያውቃል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በምንወድቅበት ጊዜም በእጆቹ ያነሳናል ብለው እኛም ማየት ያለብን ውድቀታችንን ሳይሆን ከውድቀታችን ሊያነሳን የፈለገው ኢየሱስን ነው ብለዋል። ውድቀታችንን ወደ እርሱ በማቅረብ ምሕረቱን እንድንቀምስ ኢየሱስ ይፈልጋል ብለዋል።

የቅዱስ ቶማስ ትንሳኤ፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስብከቱን ከማቅረብ ይልቅ ቁስሎቹን ባሳያቸው ጊዜ እጅግ ተጸጽተው ሁሉም ትተውት መሄዳቸውን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በዕለቱ በቦታው ያልነበረው ቶማስ፣ የኢየሱስን ትንሳኤ ያመነው ቁስሉን በእጁ በመንካት ከማመኑ በተጨማሪ ወሰን የሌለውን ፍቅሩንም ለማወቅ መቻሉን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የቶማስ ጎስቋላ ስብዕና በኢየሱስ ክርስቶስ ቁስል ውስጥ በገባ ጊዜ ከሞት ለመነሳት መብቃቱን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተው፣ እግዚአብሔርን የግላችን ስናደርገው ሕይወታችንን መቀበል እንጀምራለን ብለዋል።

ውድ ዕቃዎች ነን፣

የእግዚአብሔር ወድ ዕቃዎች መሆናችንን እንድንገነዘብ ሐዋርያው ቶማስ ያግዘና ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ዕቃ ከሆንን የእርሱ የምሕረት ብርሃን በእኛ ላይ አርፎ ወደ ዓለም ሁሉ ሊያበራ ይችላል ብለዋል። ቅዱስነታችው ከዚህ ጋር በመማያያዝ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ቶማስን እንደጠበቀ ሁሉ በላያችን የበራው ብርሃን ወደ ሌሎችም እንዲደርስ በመጠበቅ ዓለማችን ከኮሮና ቫይረስ እንዲፈወስ ያግዛል ብለዋል።

ከሁሉ የሚከፋው ቀውስ ስግብግብነት ነው፣

“ራስ ወዳድነት እና ግድ የለሽነት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያስከትለው ቀውስ የከፋ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሚከፋውም የራስን ምቾት ብቻ በሚከተል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው ብለዋል። ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች መማር ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እነርሱ ምሕረትን በመቀበል በምሕርት የኖሩ ናቸው ብለው፣ ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ከሌላቸው ጋር የተካፈሉ በመሆናቸው ይህም እውነተኛ ክርስቲያናዊ ምስክርነት ነው ብለዋል።

የወደ ፊት ዕድላችን፣

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ያስከተለው ቀውስ ክንዳችንን ለማስተባበር ዕድል ሰጥቶናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደርጉ እያንዳንዱን ግለ ሰብ የሚያካትት መሆን አለበት ብለው፣ ይህ ካልሆነ ግን የወደፊት ዕድላችን ለሁላችንም የጨለመ ይሆናል ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ማራኪ ፍቅር የቶማስን ልብ አነሳስቷል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እኛም የኢየሱስን ምሕረት ተቀብለን ለሌሎች ማሳየት ይናርብናል ብለው፣ ዓለም የሚድነው እና የሚያድገው የእግዚአብሔርን ምሕረትን ተቀብሎ ለሌሎች በተግባር ሲገልጽ ነው ብለዋል።

20 April 2020, 19:40