ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የክህነት አገልግሎት እንዲኖር የፈቀደውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት የሕማማት ሳምንት እንደ ሆነ ይታወቃል። በእዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ስርዓተ አምልኮ ደንብ መሰረት እኛን ለማዳን እና ከእግዚኣብሔር ጋር እኛን ለማስታረቅ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ያቀረበው ክርስቶስ ተላልፎ መሰጠቱን፣ መንገላታቱን፣ በመስቀል ላይ እንደ ሌባ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን እና ከሙታን መነሳቱን እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተከናወኑባቸው ሦስት ዋና ዋና ቀኖች በተለየ ሁኔታ በታላቅ መነፍሳዊነት የከበራሉ። ከእነዚህ ሦስት ቀናት መካከል የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዚያ 01/2012 ዓ.ም የተከበረው የጸሎተ ሐሙስ  ቀን በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእዚህ የጸሎተ ሐሙስ ቀን ኢየሱስ መከራውን ከመቀበሉ በፊት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ራት ከመብላቱ በፊት የሐዋሪያቱን እግር ያጠበበት፣ እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የጀመረውን መንፈሳዊ ተልዕኮ እንድያስቀጥሉ በማሰብ ምስጢረ ክህነትን የመሰረተበት፣ የመጨረሻ ራት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር ከተካፈለ በኃላ “ይህንን ለእኔ መታሰቢያ አድርጉ” በማለት ምስጢረ ቅዱስ ቁርባንን የመሰረተበት፣ ብጹዕን ጳጳሳት በእየሀገረ ስብከታቸው ከካህናቶቻቸው ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ምስጢረ ክህነት የተመሰረተበትን ቀን በማስታወስ በጋራ መስዋዕተ ቅዳሴን የሚያሳርጉበት፣ ለምስጢረ ቀንዲል (ሕሙማንን ለመፈወስ የሚያገልግል ቅባ ቅዱስ)፣ ለምስጢረ ጥምቀት እና ለምስጢረ ክህነት አገልግሎት የሚውሉ ቅባ ቅዱሶች በብጽዕን ጳጳሳት የሚባረኩበት እለት ነው። ጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራውን ቀመቀበሉ በፊት ከደቀ-መዛሙርቱ ጋር በጋራ የፋሲካን ራት የተቋደሰበት እለት ነው።

ከላይ ለመጥቀስ እንደ ሞከርነው የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዝያ 01/2012 ዓ.ም. የጸሎተ ሐሙስ ምሽት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚልካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ባስረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን ይህ መስዋዕተ ቅዳሴ የተከናወነው በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከእዚህ ቀደም በሚከናወነው መልኩ በእየአመቱ እንደሚደርገው በእለቱ መከናወን የሚገባው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቅባ ቅዱሶች የሚባረኩበት ስነ ስረዓት ሌላ ጊዜ በማዛወር ጥቂት ምዕመን በተገኙበት ተከብሮ ማለፉ የተገጸ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባስረጉት መስዋዕተ ቃዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል 13፡1-15 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ የመጨረሻውን እራት ከደቀመዛሙርቱ ጋር ከመቋደሱ በፊት የደቀመዛሙርቱን እግር ማጠቡን በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ማደረጉ የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም በእለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ክህነት የመስረተበት ቀን ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባደርጉት ስብከት በአሁኑ ወቅት በኮርና ቫይረስ የተጠቁትን ሰዎች በማገልገል ላይ በነበሩበት ወቅት ሕይወታቸውን ያጡ ካህናትን በጸሎት ማስታወስ ይገባል ማለታቸው የተገለተጸ ሲሆን “የክህነት አገልግሎት እንዲኖር የፈቀደውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሚያዝያ 01/2012 ዓ.ም በጸሎተ ሐሙስ ምሽት ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ቅዱስ ቁርባን ፣ አገልግሎት እና ቅባ ቅዱስ!

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ የምናገኘው ተሞክሮ ይህ ነው፣ ጌታ በቅዱስ ቁርባኑ አማካይነት ከእኛ ጋር መቆየት ይፈልጋል።  እኛም ጌታ የሚያርፍበት ድንኳን እንሆናለን፣ እርሱን በውስጣችን እንሸከመዋለን፣ እርሱ ራሱ እደነገረን ሥጋውን ካልበላንና ደሙን ካልጠጣን ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አንችልም። የእዚህ እንጀራ እና ወይን ጠጅ ምስጢር ጌታ ከእኛ ጋር መኖሩን በውስጣችን እንደ ሚኖር ያሳያል።

አገልግሎት! ይህ ምልክት ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ ነው። አዎን ማገልገል ... ሁሉም ሰው ማገልገል ይኖርበታል። ነገር ግን ጌታ ከጴጥሮስ ጋር በተለዋወጠው ቃል (ዮሐ 13፡6-9) ወደ መንግስተ ሰማያት ለመግባት የእግዚአብሔር አገልጋይ እኛን እንዲያገለግለን ልንፈቅድለት እንደሚገባ ጌታ እንዲገነዘብ ያደርገዋል። እናም ይህን መረዳት ከባድ ነው። ጌታ አገልጋዬ እንዲሆን ካልፈቀድኩኝ፣ ጌታ እንዲያጥበኝ ካልፈቀድኩኝ፣ እርሱ እንዲረዳኝ ካልፈቀድኩኝ፣ እርሱ ይቅር እንዲለኝ ካልፈቀድኩኝ በስተቀር ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት አልችልም።

ክህነትም እንዲሁ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተሾሙት ካህናት ጀምሮ እስከ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ፣ ለሁሉም ካህናቶች ቅርብ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። ሁላችንም ካህናት ነን፡፡ ጳጳስም ቢሆን ካህን ነው። ሁላችንም የተቀባን ነን፣ የተቀባነውም በጌታ ነው። የተቀባነውም ቁርባንን ለመቀደስ እንችል ዘንድ ነው፣ ማገልገል እንችል ዘንድ ነው የተቀባነው።

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ የቅባ ቅዱስ ቡራኬ አንፈጽምም፣ ከበዓለ ሃምሳ በፊት ልናከናውነው እንችላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ያለበለዚያ ለሚቀጥለው ዓመት ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ይኖርብናል፣ ነገር ግን ካህናትን ሳናስታውስ የዛሬውን ማታ መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳለፍ አልፈልግም። ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ካህናት ፣ አገልጋዮች የሆኑ ካህናት። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ብቻ አብዛኛዎቹ በቁጥር ከስልሳ በላይ የሆኑ ካህናት በጣሊያን ውስጥ ከእዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ከሕክምና ባለሙያዎች እና ከነርሶች ጋር በመሆን በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙትን በሽተኞችን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ናቸው። ሕይወታቸውን ለአገልግሎት የሰጡ “ከጎሬቤታችን ደጅ ላይ” የሚገኙ ቅዱሳን ናቸው። ከእኔ ራቅ ብለው የሚገኙትንም አስባለሁ። ከእዚህ ራቅ ብሎ ከሚገኙ ስፍራዎች ውስጥ በማረሚያ ቤት የነብስ አባት ከሆነው ከአንድ ካህን ዛሬ ይህንን የሕማማት ሳምንት እንዴት እያሳለፈ እንደ ሚገኝ የሚገልጽ አንድ መልእክት ደርሶኝ ነበር። አንድ የቅዱስ ፍራንቸስኮስ ማሕበር ካህን ነው። ቅዱስ ወንጌልን ከሩቅ ቦታ ተነስቶ ወደ ሩቅ ስፋራ ለማደረስ የሚሄድ ካህን ነበር። ጳጳሱ እንደ ነገሩኝ ከሆነ ይህ ካህን ወደ ተልዕኮ መዳረሻ ለመሄድ ከቤቱ ሲወጣ የሚያደርገው የመጀመሪያው ነገር ቢኖር ወደ መካነ መቃብር ስፍራ በመሄድ በወቅቱ በተቀሰቀሰው ወረርሽኝ የተጠቁትን ሰዎች በማገልገል ላይ በነበሩበት ወቅት በሽታው እንዴት እንደ ሚዛመት ግንዛቤ ስላልነበራቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው የተነሳ በእዚህ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ካሕናት  መካነ መቃብር ላይ ጸሎት በማደረግ ሲሆን የእነዚህን ካህናት ስም ማንም አያውቀም፣ እነዚህ በማንም የማይታወቁ ካህናት ነበሩ። ገጠራማ በሆኑ መንደሮች ውስጥ በተራራማ ስፍራዎች ውስጥ አራት ወይም አምስ ትንንሽ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚያስተዳድሩ ካህናት  የሚገኙ ሲሆን እነርሱም ከአንዱ አጥቢያ ወደ ሌላኛው በመሄድ ያገለግላሉ፣ እነርሱ ምዕመናኖቻቸውን ያወቃሉ።  ከመካከላቸው አንዱ በየመንደሩ ውስጥ ያሉትን የእያንዳንዱን ሰው ስም እንደሚያውቅ ነግሮኛል። እርግጠኛ ነህ ወይ ብዬ ጠየኩት።  ሁሉንም ያውቃሉ። ካህናት ለሕዝቦቻቸው ቅርብ ሲሆኑ መልካም ነው።

ዛሬ በልቤ ውስጥ እና በመሰውያዊ በመንበረ ታቦት ላይ ሆኜ አስባችኋለሁ። እንዲሁም ጥሩ ስም የሌላቸውን ካህናት አስባለሁ። ይህ ብዙውን ጊዜ ዛሬ የሚከሰት ነገር ነው። መጥፎ ነገር የሠሩ ቀሳውስት መታየታቸው የሚያሳዝን ነው በማለት ሰዎች ስለ እነሱ መጥፎ ነገር ስለሚናገሩ በነፃነት መራመድ አይችሉም። አንዳንድ ካህናት ደግሞ ሰዎች ስለሚሰድቡዋቸው ካህን መሆናቸውን የሚገልጽ አልባሳት ለብሰው መውጣት እንደማይችሉ ነግረውኛል። አሁንም በእዚያ መልክ እንደ ቀጠሉ ነግረውኛል። እንደ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና ጳጳሳት ኃጢአተኞች የሆኑ ካህናት ይቅርታን መጠየቅ እና ይቅር ማለት እንዳለባቸው መዘንጋት የለባቸውም። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። በችግር ውስጥ የሚገኙ ካህናት፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁ ፣ በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ…ካህናት ማስታወስ ይኖርብናል።

ወንድሞቼ ካህናት ሆይ ዛሬ እናንተን በመንበረ ታቦት በሠዊያው ላይ ሁላችሁ ከእኔ ጋር ናችሁ። አንድ ነገር እነግራችኋለሁ ፣ እንደ ጴጥሮስ ግትር አትሁኑ። እግሮቻችሁ እንዲታጠቡ ፍቀዱለት፣ ጌታ የእናተ አገልጋይ ነውና፣ እናተንም የሌሎችን እግር እንድታጥቡ ጥናካሬን የሰጣችኋል።

በዚህ መንገድ ንፁህ በሆነው በእርሱ መታጠብ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝባችሁ እናተም በተራችሁ የእርሱን ይቅር ባይነት ለሌሎች ለማዳረስ ይቅር ባይነትን ታስተምራላችሁ። ይቅር በሉ! ይቅርታ ማደረግ የሚችል ታላቅ የሆን ልብ ያላችሁ ሰዎች ሁኑ። የምንዳኝበት መስፈርት ይህ ነውና። ሌሎችን ይቅር በምትሉበት መልኩ ነው እናተም ይቅር የምትባሉት። ይቅር ለማለት አትፍሩ። አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬ ሲኖርባችሁ ወደ ኢየሱስ ተመልከቱ። እርሱ የተሰቀለበትን መስቀል ተመልከቱ። እዚያም ለሁሉም ይቅርታ የተደረገበትን ቁምነገር ትመለከታላችሁ።  መጽናናትን ለማምጣት፣ አደጋዎችን ለመጋፈጥ ይቅር ለማለት ድፍረቱ ይኑራችሁ። በእዚህ ወቅት የሚስጢራት አሰጣጥ ስነስረዓት በተከተለ ሁኔታ ይቅርታ ማደርግ ባትችሉ እንኳን (በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ልማዳዊ በሆነ መልኩ የሚደረገው ምስጢረ ንስሐ ማደረግ ባለመቻሉ ማለት ነው) በእያላችሁበት ቦታ ሁናችሁ መጽናናትን ያገኙ ዘንድ  እርዱዋቸው፣ ሰዎች ወደ ጌታ ይመለሱ ዘንድ በሩን ክፈቱላቸው።

የክህነት አገልግሎት የሰጠንን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፣ ሁላችንም እናመሰግናለን። ካህናት ሆይ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ኢየሱስ ይወድችኋል! እሱ የሚጠይቃችሁ አንድ ነገር ቢኖር እግሮቻችሁን ልጠብ ብሎ ነው የሚጠይቃችሁ።

09 April 2020, 23:28