ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ወደ እውነተኛ ደስታ የሚወስደውን መንገድ ኢየሱስ እንዲያሳየን እንጠይቀው” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሚያዝያ 21/2012 ዓ.ም  በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ቤት ውስጥ ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ ያደረጉት ሳምንታዊ አስተምህሮ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መተላለፉ ተገልጹዋል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ በተጠቀሰው እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ አድርጎት በነበረው ስብከት ላይ  ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእዚህ የተራራው ላይ ስብከት ውስጥ በስምንተኛው ክፍል ላይ በተጠቀሰው “ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ፤ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳደዋቸዋልና” (ማቴ 5፡10 12) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “አቋማችንን አጠናክረን የኢየሱስ ክርስቶስን መንገድ በመምረጥ የመንግሥተ ሰማይ ሕይወት ታላቅ ደስታ ፣ እውነተኛ ደስታ የምናገኝበት መንገድ ላይ መድረስ እንችል ዘንድ እንዲረዳን ኢየሱስን እንጠይቀው” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን አስተምህሮ እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

ከእዚህ ቀደም በተራራው ላይ ኢየሱስ ባደርገው ስብከት ላይ የጀመርነውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዛሬ እንደመድማለን። ቀደም ሲል እንደ ሰማነው “በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ” በማለት ለፍትህ ሲሉ የተሰደዱ ሰዎች በመጨረሻው ቀን የሚሰጣቸው ካሳ ደስታ እንደ ሆነ ይገልጻል።

ይህ የተራራው ላይ ስብከት ስምንተኛው ክፍል ከእዚህ ቀደም ከነበሩት የብጽዕና መንገዶች የሚያስገኙትን ተመሳሳይ ደስታ ይገልጻል፣ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና፣ በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና በማለት ይናገራል፤ ስለዚህ ከእዚህ ቀደም እንደ ተገለጸው ሁሉም በመጨረሻው ሰዓት ላይ አንድ ወጥ የሆነ መንገድ ላይ እንደ ሚደርሱ እንገነዘባለን።

“በመንፈስ ድኾች የሆኑ፣ የሚያዝኑ፣ የዋሆች፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ፣ ምሕረት የሚያደርጉ፣  ልባቸው ንጹሕ የሆነ፣ ሰላምን የሚያወርዱ፥ እነዚህን ተግባራት የሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ምክንያት ስደት የሚደርስባቸው ሲሆን ነገር ግን ይህ ስደት በመጨረሻ ለደስታ እና ለከፍተኛ ሽልማት እጮዎች እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው እንደ ሆነ ይገልጻል። በተራራው ላይ ኢየሱስ ያደርገው ስብከት አለማዊ ከሆነ ሕይወት ወደ ሰማይ ቤት እግዚአብሔር ወዳለበት ሕይወት የሚያሻግረን መንገድ ሲሆን በሥጋ ከሚመራው ሕይወት - ማለትም ራስ ወዳድ ከሆነ ሕይወት በመንፈስ ወደ ሚመራ ሕይወት የሚደረግ የፋሲካ ጉዞ ነው።

ዓለም ከነጣዖታቱ፣ ከነማባበያው እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮችን ሁሉ ተጠቅሞ የእዚህን ዓይነት ደስታ የሚያጎናጽፍ ይጽድቅ ሕይወት ሊያጎናጽፈን አይችሉም። ብዙን ጊዜ የሰው ልጆች የሥራ ውጤት የሆኑ “የኃጢአት አደረጃጀቶች” እውነት የሆኑ ነገሮች ባዕድ ስለሚሆኑበት የእውነት እና የመንፈስ የሆኑትን ነገሮች ዓለም ስለማያያቸው እና ስለማያውቃቸው ሊቀበላቸው አይችልም (ዮሐ 14 17)፣ ድህነትን ወይም ገርነትን ወይም ንፅህናን ብቻ ሳይሆን የሚያገሉት፣ ነገር ግን ቅዱስ ወንጌል እንደ  ሚነግረን ሕይወታችንን ሳይቀር ችግር ውስጥ በመክተት እንደ ባዕድ ነገር በመቁጠር የብጹዕናን ሕይወት እስከ መቅጠፍ ሊደርሱ ይችላሉ። ስለእዚህ ዓለም እንዲህ ያስባል - “እነዚህ ምናባዊያን ወይም አክራሪ ናቸው…ወዘተ” በማለት ያስባሉ።

ዓለም በገንዘብ ላይ መሰረቱን ያደረገ ሕይወት ስለሚኖር ሕይወቱን ስጦታ አድርጎ በስጦታ መልክ ለማቅረብ የሚፈልግ ሰው ስግብግብ በሆነ ስርዓት  ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ስሜታቸውን ይረብሻል። ይህ “ብስጭት” የሚለው ቃል ቁልፍ የሆነ ቃል ነው ፣ ምክንያቱም ለብዙ ሰዎች የሚሰጥ ብቸኛው የክርስትና ምስክርነትን የሚከተል ስለሆነ አለማዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን ያበሳጫቸዋል። እነሱ ይህንን እንደ ተግሣጽ አድርገው ይመለከቱታል። ቅድስና ሲገለጥ እና የእግዚአብሔር ልጆች ሕይወት ሲገለጥ ፣ በዚያ ውበት ቦታ በተቃራኒው ለሚኖሩ ሰዎች የማይመች ነገር አለ ማለት ነው፣ ወይም ያንን ብርሃን ላለመቀበል እምቢ ለማለት እና ልቡን ለማደናቀፍ ፣ ተቃውሞ እና ቁጣ መገንፈል ይጀምራል። በሰማዕታት ስደት እና በጠላትነት መንፈስ መታየት እስከ ንዴት ደረጃ ድረስ እንደ ሚያደርስ መመልከት በጣም የሚያጓጓ ነገር ነው፣ ትኩረትን ይስባል ። ባለፈው ምዕተ-ዓመት በአውሮፓ አምባገነናዊ አገዛዞች ምክንያት የደረሰውን ስደት ማየት ብቻ በቂ ነው። በክርስቲያኖች ላይ ክርስቲያናዊ የሆነ ምስክርነት እና በክርስቲያኖች ጀግንነት ላይ ተመስርተን እንዴት እያደግን መሆናችንን መመልከት በራሱ መልካም ነው።

ነገር ግን ይህ ነገር የሚያሳየው የስደት ድራማ በዓለም ላይ ስኬት መጎናጸፉን፣ ድል መንሳቱን እና ነጻ የሚያወጣ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በክርስቶስ ምክንያት ዓለም ያሳደዳቸው ሰዎች የሚደሰቱት ለምንድነው? ከዓለም ሁሉ የበለጠ የላቀ ዋጋ ያለው ነገር ስለሚያገኙ ደስ ይላቸዋል። “በእውነቱ "ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅሟል?" (ማርቆስ 8፡36) ። ምንም አይጠቅመውም!

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስደት የሚሰቃዩ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ማስታወሱ በጣም የሚያሳምም፣ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። እናም መከራቸው በተቻለ ፍጥነት እንዲቆም ተስፋ እናደርጋለን። ብዙ አሉ - የዛሬው ዘመን ሰማዕታት ከመጀመሪያዎቹ መቶ ዓመታት በፊት ከነበሩት ሰማዕታት በቁጥር እጅግ በጣም ከፍ ያሉ ናቸው። ለእነዚህ ወንድሞች እና እህቶች ቅርብ መሆናችንን እንገልፃለን፣ አንድ አካል ነን፣ እነዚህ ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካል የሆነችው የቤተክርስትያን አባላት ናቸው።

ነገር ግን ይህንን የተራራው ላይ ስብከት በተጎጂነት መንፈስ ውስጥ ገብተን ከማንበብ መቆጠብ አለብን። በእርግጥ ሰዎች ተንቀናል፣ ተሰደናል ሲሉ ሁል ጊዜ የክርስትያን ስደት መነሻ ጋር ማያያዝ አይኖርብንም። በእዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ኢየሱስ ክርስቲያኖች “የምድር ጨው” እንደሆኑና “ጣዕም ማጣት” ከሚያስከትለው አደጋ እንዲጠነቀቁ በማሳሰብ ካልሆነ ግን “ጣዕሙን ቢያጣ ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጪ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም” (ማቴዎስ 5፡13) በማለት ያስጠነቅቃል። ስለእዚህ የክርስቶስን እና የቅዱስ ወንጌልን ጣዕም ስናጣ በእዚህ ምክንያት የሚደርስብን ንቀት አለ።

በተራራው ላይ የተሰበከውን ስብከት በትሕትና መንፈስ መቀበል የሚገባን ሲሆን ይህ ካልሆነ እና በራሳችን መንገድ የምንመለከተው ከሆነ ወደ ክርስቶስ ሳይሆን ወደ ዓለም መንገድ እንድናመራ ሊያደርገን ስለሚችል መጠንቀቅ ይኖርብናል። የቅዱስ ሐዋርያው  ጳውሎስን ጉዞ ማስታወስ ጠቃሚ ነው - ጻድቅ ነኝ ብሎ አስቦ ነበር፣ ነገር ግን  ሁኔታው የሚያሳየው አሳዳጅ እንደ ነበረ ነው፣ አሳዳጅ መሆኑን ባወቀ ጊዜ የደረሰበትን የስቃይ መከራ፣ በደስታ እና በፍቅር ተጋፈጠ (ቆላሲያስ 1.24).

መገለል እና ስደት ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ከሰጠን ፣ እኛ የተሰቀለውን ክርስቶስን እድንመስል እና ከእርሱ ሕማማት ጋር እንድንቆራኝ የሚያደርጉን የአዲሱ ሕይወት መገለጫዎች ናቸው። ይህ ሕይወት ለእኛ ሰዎች እና ለደህንነታችን ሲል “በሰዎች የተናቀው እና የተጠላው” ከክርስቶስ ሕይወት ጋር አንድ ነው። መንፈሱን መቀበል በልባችን ውስጥ እጅግ ብዙ ፍቅር እንዲኖረን ስለሚረዳን በአለም ማታለያዎች ሳንታለል እና ሳንመካ፣ ማባበያውን ሳንቀበል የዓለምን ሕይወት ልንቀይር እንችላለን። ከዓለም መንፈስ ጋር መጣጣም አደጋ አለው። ክርስትያን ሁል ጊዜ ከዓለም መንፈስ ጋር ስምምነት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ይፈተናል። ስለእዚህ አቋማችንን አጠናክረን የኢየሱስ ክርስቶስን መንገድ በመምረጥ የመንግሥተ ሰማይ ሕይወት ታላቅ ደስታ ፣ እውነተኛ ደስታ የምናገኝበት መንገድ ላይ መድረስ እንችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ሁላችንንም ይርዳን።

29 April 2020, 20:04