ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በሕማማት ሳምንት በመስቀሉ ምስጢር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 30/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር ረቡዕ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም፣ የእዚህ ወረርሽኝ መስፋፋት ለመዋጋት ይቻል ዘንድ ሰዎች በእየቤታቸው መቆየት አለባቸው የሚለውን የጤና ባለሙያዎች ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ያስተላለፉት ሳምንታዊ አስተምህሮ እንደነበረ ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 30/2012 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በአሁኑ ወቅት የጎጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የፋሲካ በዓል ከመከበሩ በፊት በሚገኘው የሕማማት ሳምንት ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስለሚፈጸመው ስቃይ፣ መከራ እና ሞት ላይ ባተኮረው መልኩ ቅዱሳት መጽሐፍት በሚገልጹት ጭብጥ ዙሪያ ላይ ያተኮረ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእዚህ በያዝነው የሕማማት ሳምንት በየቤታችን የሚገኘውን የኢየሱስ መስቀል መመልከት እና መጽሐፍ ቅዱስ መክፈት መዘንጋት የለብንም ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 30/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በአሁኑ ወቅት ዓለምን በጣም እያሰቃየ ሰለሚገኘው ወረርሽኝ በምንሰማበት እና በፍርሀት ውስጥ በምንገኝበት በእነዚህ ሳምንታት ውስጥ  ለራሳችን ከምናቀረባቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል “እኛ በእዚህ ጭቀት ውስጥ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት እግዚአብሔር ምን እየሰራ ይገኛል? ሁሉም ነገር ውጥንቅጡ ሲወጣ እግዚአብሔር የት አለ? ችግሮቻችን ለምንድነው በፍጥነት የማይፈቱት? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት እግዚአብሔርን ልንጠይቀው እንችል ይሆናል። እነዚህ ስለ እግዚአብሔር የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ናቸው ፡፡

በእነዚህ የሕማማት ሳምንት ቀናት ውስጥ (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንደ በመጋቢት 27/2012 ዓ.ም የተጀመረውን የሕማማት ሳምንት የመለክታል) ኢየሱስ ስቃዩን ለመቀበል ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን የሚገልጹ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱትን ታሪኮች በማንበብ ላይ የምንገኝ ሲሆን እነዚህ ታሪኮች ሁኔታውን እንዲንመለከት ይረዱናል። በእውነቱ በእነዚያ ታሪኮች ውስጥም እንኳን ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ሰዎቹ ወደ እየሩሳሌም ይሄድ የነበረውን ኢየሱስን በድል አድራጊነት መንፈስ በታላቅ ደስታ ከተቀበሉት በኋላ ሕዝቡ  “እኛ ግን በመጨረሻ ሰዓት እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን አልነበረምን?” (ሉቃስ 24፡21) በማለት ማጉረመርም ጀመረው ነበር።  እነሱ ኃያል የሆነ እና በስይፍ ድል በማድረግ አሸናፊ የሚሆን መሲህ ጠብቀው ነበር። ነገር ግን እነርሱን የገጠማቸው መሲህ ወደ መለወጥ እና ምሕረት የሚጠራ ገር እና ትሁት ሰው ይመጣል።  ቀድም ብለው ሆሳዕና እያሉ ሲጮኹ የነበሩ ሰዎች አሁን ደግሞ “ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ” (ማቲ 27.23)። ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ግራ ተጋብተው እና ፈርተው ብቻውን ትተውት ሄዱ። እነሱ እንዲህ ብለው አሰቡ: - “የኢየሱስ ዕጣ ፈንታ ይህ ከሆነ በእውነቱ እርሱ መሲህ አይደለም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ብርቱ ነው፣ እናም እግዚአብሔር በፍጹም የማይሸነፍ ነው” በማለት ማሰብ ይጀምራሉ።

ነገር ግን ኢየሱስ መከራ የተቀበለበትን ታሪክ ማንበብ ከቀጠልን አስገራሚ እውነታ እናገኛለን። ኢየሱስ በሚሞትበት ጊዜ አንድ አማኝ ያልሆነ፣ አይሁዳዊ ሳይሆን አረማዊ የነበረ ሮማዊ መቶ አለቃ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የነበረውን ስቃይ ከተመለከተ፣ ኢየሱስ ሁሉንም ይቅር እንዳለ ካየ እና ወሰን በሌለው የፍቅር እጁ እርሱን ከዳሰሰው በኋላ “በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነበር "(ሉቃስ 15፡39) በማለት ስለእርሱ መሰከረ። ይህ ቀድም ሲል አማኝ ያልነበረ ሰው ከሌሎች ተቃራኒ በሆነ መልኩ ምስክርነትን ሰጠ። እዚያ ላይ (በመስቀሉ ላይ) በእውነት እግዚአብሔር አለ በማለት ተናገረ።

ዛሬ ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን-እውነተኛው የእግዚአብሔር ፊት ምንድነው? ብዙውን ጊዜ እርሱን የምንስልበት ሁኔታ እኛ ለመሆን በምንፈልገው እና በምንመኘው መልኩ ነው፣ ከፍተኛ የሆነ ሀይል ወይም ጉልበታችንን፣ ስኬታችን፣ ለፍትህ ያለን ስሜታችንን እና እንዲሁም ቁጣችን እንዲመስል እንፈልጋለን። ቅዱስ ወንጌል ግን እግዚአብሔር እንደዚህ እንዳልሆነ ያሳያል።  እሱ ከእኛ መስፈርት እጅግ የተለየ በመሆኑ የተነሳ በራሳችን ጥንካሬ እና ብርታት እርሱን ማወቅ አንችልም። ለዚህም ነው እርሱ ለእኛ ቅርብ የሆነው፣ እኛን ለመገናኘት የመጣ እና በፋሲካ ቀን ራሱን ለእኛ የገለጸው በእዚሁ ምክንያት ነው። ይህ ሙሉ በሙሉ የተገለጸው የት ነበር? በመስቀል ላይ! እዚያ የእግዚአብሔርን የፊት ገፅታዎች እውነተኛ ትርጉም እንማራለን።

ወንድሞችና እህቶች! መስቀሉ የእግዚአብሔር መቀመጫ ካቴድራል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ኢየሱስ የተሰቀለበትን በእየቤታችን የሚገኘው መስቀል ስር ሆነን መስቀሉን በዝምታ መመልከት ጌታችን ማን እንደ ሆነ ለይቶ ለማወቅ ይጠቅመናል፣ በማንም ሰው ላይ ጣቱን ሲቀስር አይታይም፣ እርሱን ሲሰቅሉት በነበሩት ሰዎች ላይ ሳይቀር እንኳን ምንም ዓይነት ተቃውሞ አላነሳም፣ ወይም አላሳየም፣ ለሁሉም እጆቹን ሰፋ አድርጎ ይከፍታል፣ ታላቅ ክብሩን ተጠቅሞ ከእዚያ ስፍራ ሰዎችን ማባረር አልፈለገም፣ ነገር ግን ለእኛ ሲል መዋረድ ፈለገ፣በቃላት ብቻ ሳይሆን የወደደን ነገር  ግን በጸጥታ ሕይወቱን በመስጠት እንደ ሚወደን አሳየን፣ በፍጹም አያስገድደንም ነገር ግን ነፃ ያወጣናል፣ እንደ ባዕድ አድርጎ የማይቆጥርን ነገር ግን ክፋታችንን በራሱ ላይ አድርጎ የሚሸከም፣ ኃጢአታችንን በሙሉ የራሱ በማደረግ የተሸከመ አምላክ መሆኑን እንረዳለን። እናም ይህ እኛ ራሳችንን ስለ እግዚአብሔር ካለን ጭፍን የሆነ አመለካከት ለማላቀቅ እርሱ የተሰቀለበትን መስቀል መመልከት ያስፈልጋል። ከእዚያም በመቀጠል መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንክፈት። በእነዚህ ቀናት ሁሉላችንም ገለልተኛ ሁነን ቤታችንን ዘግተን የምንገኝ ሲሆን እነዚህን ሁለት ነገሮች በእጃችን ላይ አድርገን እንመልከት፣ እነዚህ ሁለት ነገሮች ደግሞ ኢየሱስ የተሰቀለበት መስቀል እና መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው። መስቀሉን በእጃችን ላይ አድርገን አትኩረን እንመልከት፣ መትጽሐፍ ቅዱስኑም እንክፈት። ይህ ደግሞ በእዚህ ወት በቤታችን ውስጥ የምናደርገው አንድ ትልቅ የሆነ የቤት ውስጥ ሥነርዓተ አምልኮ አድርገን ለመቁጠር እንችላለን፣ ምክንያቱም በእነዚህ ቀናት ውስጥ  ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ አንችልምና፡፡ መስቀል እና መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን ላይ ዘወትር ሊገኙ ይገባል!

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ለምሳሌም ኢየሱስ በጥቂት እንጀራ እና ዓሳ አምስት ሺ ሰዎችን ከመገበ በኋላ ሰዎች ኢየሱስን ንጉሳቸው አድርገው ለማንገስ በፈለጉበት ወቅት እርሱ ከእዚያ ስፍራ ሸሽቶ እንደ ሄደ እናነባለን (ዮሐንስ 6 15)፡፡ አጋንትም የእርሱን ታላቅ ክብር እንዲገልጽላቸው በሚፈልጉበት ወቅት እርሱ ዝም ያሰኛቸዋል (ማርቆስ 1፡24-25)። ለምን? ምክንያም ኢየሱስ ሰዎች እንዳይደነጋገሩ፣ ሰዎች ትሁት ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከሆነ አምላክ ጋር በማነጻጸር በተሳሳተ መልኩ እንዳይረዱት፣ በኃይሉ በማስገደድ ድንቅ ነገር ለማደረግ የሚጥረውን ዓለማዊ የሆነ አምላክ ከእውነተኛ አምልካ ለይተው ለማወቅ ይችሉ ዘንድ ሕዝቡን ለመርዳት አስቦ ያደርገው ነገር ነው። እሱ ጣዖት አይደለም። እርሱ እንደ እያንዳንዳችን ስጋ ለብሶ ሰው የሆነ ነው፣ መለኮታዊ ጥንካሬውን በጠበቀ መልኩ ራሱን እንደ ሰው አድርጎ የሚገልጽ እግዚአብሔር ነው። ይልቁኑ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የኢየሱስ ማንነት ብቻ የተገለጸው መቼ ነው? የመቶ አለቃውም “እርሱ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” ብሎ በተናገረበት ወቅት ነበር። እዚያ በመስቀሉ ላይ ሕይወቱን በሚሰጥበት ሰዓት እንደዚያ ተብሎ የተገለጸበት ምክንያት ከእንግዲህ ወዲህ እርሱን በተሳሳተ መልኩ እንዳንረዳው እና የእግዚአብሔር ፍቅር ሁሉን ቻይ መሆኑን እና እግዚአብሔር የሚገለጸው ከእዚህ በተለየ ሌላ መንገድ እንዳልሆነ እንድናውቅ ስለተፈለገ ነው። የእርሱ ተፈጥሮ  ይህ ነው፣ እርሱ ፍቅር ነው።

እናንተ ይህንን በመቃወም “በእዚህ መልኩ በሚሞት እንዲህ ባለ ደካማ አምላክ ላይ ምን ማድረግ አለብኝ? በማለት ልታስብ ትችል ይሆናል። ነገር ግን እኔ ጠንካራ እና ኃይለኛ አምላክ እመርጣለሁ! ልትል ትችል ይሆናል።  ግን ታውቃላችሁ የዚህ ዓለም ኃይል ያልፋል፣ ፍቅር ግን እንዳለ ይቆያል። ያለንን ሕይወት የሚጠብቀው ፍቅር ብቻ ነው፣ ምክንያቱም ድክመቶቻችንን የሚያቅፍ እና የሚቀይር ስለሆነ። በሞቱ ኃጢያታችን ይቅር እንዲባልልን ፣ ፍርሃታችንን ወደ እምነት፣ ሥቃያችን ወደ ተስፋ የለወጠው በፋሲካ ቀን በተገለጸው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ፋሲካ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር በመልካም መለወጥ እንደሚችል ይነግረናል፡፡ በእርሱ ዘንድ ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን በእውነት መተማመን እንችላለን ፡፡ ይህ ቅዤት አይደለም፣ ምክንያቱም የኢየሱስ ሞት እና ትንሣኤ ቅዤት አይደለምና፣ ይህ እውነት ነው! ለዚህም ነው በ ‹ፋሲካ› ጠዋት ላይ “አትፍሩ!” ተብለን የተነገረን (ማቴዎስ 28.5)፡፡ እናም የሚያስጨንቁን ክፉ ነገርን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች በድንገት አይጠፉም፣ ነገር ግን ከሙታን በተነሳ በእርሱ አማካይነት በእነርሱ ፍራሃት ውስጥ ገብተን እንዳንጥለል የሚያስችለንን ጠንካራ መሠረት ለመገንባት ያስችለናል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ኢየሱስ ለእኛ ቅርብ መሆኑን በማሳየት ታሪክን ቀይሩዋል፣ ምንም እንኳን አሁንም በክፉ ምልክት የተያዘ ቢሆንም እርሱ የደህንነት ታሪክ በመፈጸም ቀይሮታል። በመስቀል ላይ ሕይወቱን በማቅረብ ፣ ኢየሱስ ሞትን ድል አደረገ፡፡ ከተከፈተው የመስቀሉ ልብ የእግዚአብሔር ፍቅር ወደ እያንዳንዳችን ይደርሳል፡፡ እኛ እሱ የሚሰጠንን ድህንነት በመቀበል ታሪኮቻችንን መለወጥ እንችላለን።

ወንድሞች እና እህቶች በሕማማት ሳምንት በእነዚህ ቀናት በጸሎት ለመስቀሉ እና ለመጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን እንክፈትለት።  እርሱ የተሰቀለበትን መስቀል እና መጽሐፍ ቅዱስን በፍጹም እንዳትረሱ። በቤት ውስጥ የሚደረግ ስርዓተ አምልኮ ማለት ይህ ነው። ልባችንን በሙሉ በጸሎት እንክፈት፣ ትኩረቱ በእኛ ላይ እንዲያደርግ እንፍቀድለት። እናም እኛ ብቻችንን አይደለንም ነገር ግን የተወደድን መሆናችንን እንረዳለን ፣ ምክንያቱም ጌታ አይተወንም እንዲሁም ፈጽሞ አይረሳንም። በእነዚህ ሀሳቦች ላይ ተንተርሼ መልካም የሕማማት ሳምንት እና ቅዱስ የሆነ የፋሲካ በዓል ታከብሩ ዘንድ እመኛለሁ።

08 April 2020, 17:48