ፈልግ

ጋዜጣን በመሸጥ ከሚተዳደሩ ሰዎች መካከል፣ ጋዜጣን በመሸጥ ከሚተዳደሩ ሰዎች መካከል፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመንገድ ዳር ጋዜጣ አዘዋዋሪዎች ምስጋናቸውን አቀረቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የብዙዎችን ሕይወት ችግር ውስጥ በጣለበት ባሁኑ ወቅት፣ በየመንገዱ ተስፋን የሚሰጡ ጋዜጦች የሚያሰራጩ በጎ ፈቃደኞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ መጠለያ አልባ የሆኑ ሰዎች እና ስደተኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከጋዜጦች መካከል በአንዱ ላይ ታትሞ በወጣው መልዕክት  በኩል ቅዱስነታቸው እንደገለጹት፣ በዓለማችን ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች መጠን ማወቅ የምንችለው ድሆችን ስንመልከት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የተለያዩ ስሞችን ይዘው በየመንገድ ዳር የሚሸጡ ከመቶ ባላይ ጋዜጦች በገጾቻቸው ይዘው የሚወጡትን መልዕክቶች በማስታወስ በጻፉት መልዕክታቸው፣ እነዚህ ጋዜጦች ወረቀት ብቻ ሳይሆኑ በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ሥራን አግኝተው ስብዕናቸውን ያስከበሩበት፣ ብዙዎችም ከኢፍትሃዊ ሕይወት መውጣት የቻሉበት እንደሆነ አስረድተው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስጨነቀ በሚገኝበት ጊዜም ቢሆን የጋዜጣ ማዘዋወር ሥራቸውን እንዳያቋርጡ  በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ድህነት ከባድ ዋጋን የሚያስከፍል ሕይወት ነው፣ 

በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ ችግሮችን በመጋፈጥ ላይ እንደሚገኙ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእነዚህ ችግሮች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቁት የጎዳና ተዳዳሪዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በችግሮች በቀላሉ በመጠቃት ከፍተኛ ዋጋን ለመክፈል የሚገደዱት መጠለያ አልባ የሆኑ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች ናቸው ብለዋል። በብዙ አገሮች ጋዜጣን በመሸጥ የሚተዳደሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ መጠለያ አልባ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች፣ ሥራ የሌላቸው እና በድህነት ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች መሆናቸውን አስታውሰው፣ ትንሽ ቢሆንም ጋዜጣን በመሸጥ ራሳቸውን መርዳት ችለዋል ብለዋል።

የጎዳና ላይ ጋዜጣዎች ተሞክሮ፣

በእትማቸው አስገራሚ ታሪኮችን ይዘው የሚወጡ፣ በቁጥር ከመቶ በላይ ጋዜጦች በ25 ቋቋዎች እየታተሙ በዓለማችን በ35 አገሮች እየተሸጡ ለ20,500 የጎዳና ተዳዳሪዎች የሥራ ዕድል እንደከፈቱላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። በጣሊያን ውስጥ በአንድ እርዳታ ሰጭ ድርጅት አስተባባሪነት የሚታተም “ስካርፓ ዲ ቴኒስ” በሚባል ስም የሚታወቅ ጋዜጣ እንዳለ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ጋዜጣ ለአንድ መቶ ሰላሳ ሰዎች የሥራ ዕድል መክፈቱንም አስታውሰዋል።

ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ሆነናል፣

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ እነዚህ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች ጋዜጣን የመሸጥ ሥራን ያቋረጡ መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ሰዎች ብርታትን በመመኘት ከጎናቸው መሆናቸውን የገለጹላቸው ሲሆን ሲያከናውኑ የቆዩት የጋዜጣ መሸጥ ሥራ ተስፋ ያለበት እና ስለ ተስፋ የሚናገር እንደነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በእነዚህ ቀናት ውስጥ በዙሪያችን የሚገኙ ድሆችን ዞር ብለን ስንመለከታቸው ብርታትን አግኝተው የሚጽናኑ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለማችን ውስጥ በቁጥር በርካታ የሆኑ ችግሮች መኖራቸውን እንገነዘባለን ብለዋል።

የድህነት ማስረጃ

በየጎዳናዎቹ ለሚሸጡት ጋዜጦች ትኩርታቸውን የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሐዋርያዊ ስልጣን ከተመረጡ ወዲህ ከእነዚህ ጋዜጦች መካከል ከሦስቱ ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ሲታወስ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 27/2015 ዓ. ም. በሆላንድ አገር ከሚታተም፣ “ስትራት ኒውስ” ከተባለ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ ጋዜጣ በኩል የቀረቡት ጥያቄዎች በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን የመጀመሪያው በትውልድ አገራቸው አርጄንቲና ስለሚገኝ አንድ ሕጻን እና በቫቲካን ውስጥ የሚያሳልፉት ዕለታዊ ሕይወት ምን እንደሚመስል የተጠየቁበት መሆኑ ታውቋል። ስለ ድሆች እና ተፈናቃዮች በሚጠየቁበት ጊዜ “መልሴን ከየት ልጀምር” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ድሆችንና ተፈናቃዮችን አስመልክቶ መናገር ግዴታ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ አስቸጋሪ ሕይወት ለሚሰቃዩት ሦስት ነገሮች እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለው እነርሱም፥ ሥራ ፣ መጠለያ እና መሬት ናቸው ብለዋል። ቤተክርስቲያን እውነትን ተገን በማድረግ መመስከር ያለባት ስለ ድህነት እና መጠለያ አልባነትን ነው ብለዋል። አንድ አማኝ ስለ ድህነት ወይም ስለ መጠለያ እጦት እየተናገረ የከበረ ሕይወት የሚኖር ከሆነ ስለ ድህነት ወይም ስለ መጠለያ አልባነት በሚገባ መመስከር አይቻለውም ብለዋል።

በጣሊያን፣ ሎምባርዲያ ክፍለ ሀገር፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1994 ዓ. ም. ጀምሮ በሚላን ከተማ ከሚታተም ጋዜጣ ጋር በየካቲት ወር 2017 ዓ. ም. ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ድሆች በልመና የሚተዳደሩ ቢሆንም በመካከላቸው ሕብረት ስላለ የእርስ በእርስ መረዳዳት አስፈላጊ መሆኑን ይረዱታል ብለዋል። የሌሎችን ስቃይ በትክክል መገንዘብ ትልቅ ችሎታ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አስቸጋሪ የሆኑ ወቅቶችን ማወቅ ችሎታን ይጠይቃል ብለዋል። ብዙውን ጊዜ የሰዎች ታላቅነት እና ሃብታምነት ሊጠፋ የሚችለው የሚናገሩትን በተግባር ስለማይገልጹ ነው በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው ታላቅነትን በተግባር የማይገልጹ፣ ነገር ግን ብዙ ቃላትን ለመናገር የሚችሉ ሰዎች የድሆች ሕይወት ምን እንደሚመስል በተግባር ካልቀመሱ ታላቅ ናቸው ሊባሉ አይችሉም ብለዋል።

አእምሮ ፣ ልብ እና እጅ፣

ከተለያዩ አካባቢዎች የቀረቡ ጥያቄዎችን በማሰባሰብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት የቅዱስ ዮሐንስ ቦስኮ ቁምስና መሪ ካህን፣ ክቡር አባ ፔፔ በአርጄንቲና ውስጥ በአደንዛዥ ዕጽ ዙሪያ የሚከናወነውን በማስታወስ ላቀረቡት ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ ሰዎች በአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋርነት ወንጀል ምክንያት ሁሉን ነገር በሚያጡበት ጊዜ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር በማስረከብ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ መለመን ይጀምራሉ ብለዋል። ስለ ሦስት ነገሮች መናገር እንደሚፈልጉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው እነርሱም የአእምሮ ፣ የልብ እና የእጅ ቋንቋዎች ናቸው ካሉ በኋላ በእነዚህ ሦስቱ መካከል የጠበቀ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ አስረድተው ሰዎች የሚያስቡት የሚሰማቸውን እና የሚያደርጉትን፣ የሚሰማቸውም ስለሚያስቡትን እና ስለሚያደርጉትን ፣ የሚያደርጉትም የሚሰማቸውን እና የሚያስቡትን ነው በማለት አስረድተዋል። ይህም በምናባዊነት ዓለም ፣ በሰውነት አልባ ሕይወት ውስጥ እንደመኖር ያህል ነው ብለዋል።                 

28 April 2020, 21:03