ፈልግ

የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ፤ የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ፤  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን “የዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን” ማቋቋማቸው ተነገረ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊስም የሚጠራ ፋውንዴሽን ያቋቋሙበት ዋና ዓላማ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ አስተምህሮች፥ ባልንጀራን መውደድ፣ በትህትና ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት መመስከር፣ የጎረቤት ፍቅር እና የአንድነት መንፈስ የሚለውን ጉልህ ባሕሪያት ሳይዘነጉ በዘመናችን እና በመጭው ትውልድ መካከል ሕያው ሆነው እንዲቆዩ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። ፋውንዴሽኑን በበላይነት እንዲመሩት በማለት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መሰየማቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የካቲት 17/2020 ዓ. ም. ከሐዋርያዊ የሥራ ተባባሪዎቻቸው የቀረበላቸውን ሃሳብ በማገናዘብ ፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ አስተምህሮችን በጥልቀት በመመልከት፣ በጽሑፍ ባስቀመጧቸውን ሃሳቦች ላይ ጥናት በማድረግ እና በማሳደግ፣ ለወደፊት ትውልድ አዘጋጅቶ ለማስቀመጥ ታስቦ መሆኑ ታውቋል። መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ይዘት ያሏቸው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮች የተለያዩ ጉባኤዎችን፣ ስብሰባዎችን፣ አውደ ጥናቶችን እና ጥናታዊ ምርምሮችን ለማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ መሆናቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ የጽሑፍ ማኅደረ በጣሊያን ሆነ በውጭ አገር ሆነው በተመሳሳይ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ዘርፎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችንና ምርምሮችን በማድረግ ወደ ተመሳሳይ ግብ ለመድረስ ጥረት ለሚያደርጉ ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽዖን የሚያበረክት መሆኑ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፋውንዴሽኑን በፕሬዚደንትነት የሚመሩትን፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የመረጧቸው ሲሆን በአስተዳደራዊ ምክር ቤት ውስጥ ምክትል ፕሬዚደንት እንዲሆኑ ዶ/ር ስቴፋኒያ ፋላስካ፣ እንዲሁም ብጹዕ ካርዲናል ቤኒያሚኖ ስቴላን፣ ብጹዕ አቡነ አንድሬያ ቼሊ፣ ክቡር አባ ዳቪዴ ፊዮኮ፣ ዶ/ር ሊና ፔትሪ እና ዶ/ር አልፎንሶ ካውቴሩቾን የምክር ቤቱ አባላት አድረገው መሰየማቸው ታውቋል።

ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ከነሔሴ 26/1978 እስከ መስከረም 28/1978 ዓ. ም. ድረስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን የመሩት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ላበረከቱት የጽሑፍ ሥራቸውን እና ሐዋርያዊ አስተምህሮች ትኩረት በመስጠት ለዛሬው እና ለወደፊቱ ትውልድ አገልግሎት ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ የሚለውን ሃሳብ መሠረት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የካቲት 17/2020 ዓ. ም. የር. ሊ. ጳ. የዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን በቫቲካን ማቋቋማቸው ታውቋል።

በቀድሞ ስማቸው አልቢኖ ሉቺያኒ በመባል የሚታወቁት ር. ሊ. ጳጵሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ በር. ሊ. ጵጵስና ሐዋርያዊ የአስተዳደር ስልጣን መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለአጨር ጊዜ የመሯት ቢሆንም በእምነት ላይ የተመሠረተ እና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቅርብ በመሆን ለማኅበራዊ ሕይወት ከፍተኛ ቅድሚያን የሰጡ መሆናቸው ታውቋል። በዚህ የተቀደሰ ሐዋርያዊ ዓላማቸው፣ ባልንጀራን በመውደድ፣ በትህትና በመሞላት፣ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት በመመስከር፣ የጎረቤት ፍቅር እና የአንድነት መንፈስ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሆኑ ታውቋል። ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መርህ በመከተል በአጭር የር. ሊ. ጵጵስና ጊዜ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ወንጌል በመመራት ተልዕኮዋን በፍሬያማነት እንዲትወጣ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር ፣ ቤተክርስቲያን አገልግሎቷን በድህነት ሕይወት እንድታበረክት፣ በክርስቲያኖች መካከል አንድነትን ለማሳደግ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የጋራ ውይይቶች እንዲኖሩ በማድረግ፣ ፍትህ እና ሰላም ለማንገሥ፣ የምንገኝበትን ዘመን ያገናዘቡ ዓለም አቀፍ ውይይቶችን ለማድረግ በጽናት እና በቆራጥነት የተነሱ መሆናቸውን፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም የቤተክርስቲያን የድህነት ሕይወት አገልግሎት አስመልክተው ያቀረቧቸውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት በተለይም ለድሆች ባላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ የዕርዳታ እና የአንድነት አገልግሎት በቤተክርስቲያን ለመጀመር ያላቸውን ሃሳብ ለጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መግለጻቸውን አስታውሰዋል።    

በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ ሰላም እንዲወርድ በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 10/1978 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመና ጋር ባደረሱት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ለሰላም በሚደረገው ጸሎት እንዲተባበሩ ማሳስባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቫቲካን ውስጥ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችን አግኝተው ንግግር ባደረጉላቸው ጊዜ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አቋም፣ እምነቷን መሠረት ያደረገ መሆኑን ማብራራታቸውን አስታውሰዋል። በስመተ ርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት ዓለም አቀፍ ልኡካን ባደረጉት ንግግር “ልባችን ለመላው የዓለም ሕዝብ ክፍት ነው” ማለታቸውንም ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰው “መላዋ ቤተክርስቲያን ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሄ ይሆናሉ ብላ የምታስባቸውን ሃሳቦች ለማበርከት ዝግጁ ናት” ማለታቸውንም አስታውሰዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ለዓለም አቀፉ ልኡካን ማኅበረሰብ “ሁሉ አቀፍ የቸርነት አገልግሎት የመላዋ ቤተክርስቲያን ተልዕኮ ነው” ማለታቸውን ያስታወሱት ንጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም “ቤተክርስቲያን ትሁት የቅዱስ ወንጌል መልዕክተኛ በመሆኗ፣ በመላው ዓለም ለሚገኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ፍትህን፣ ወንድማማችነትን፣ አንድነትን እና ለዓለም በሙሉ የተስፋ መልዕክትን ለማብሰር ተጠርታለች” ማለታቸውን አስታውሰዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ “ደስታ እና ተስፋ” በማለት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረት በማድረግ፣ ቤተክርስቲያን በርካታ መልካም ፍሬዎችን ያፈራችባቸውን ሐዋርያዊ ግንኙነት ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ተግባራዊ ያደረጉ መሆኑን አስታውሰዋል።

“የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ አስተምህሮዎች ለመላዋ ቤተክርስቲያን ትልቅ እገዛ ማድረጉን ይቀጥላል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ በአጭር ሐዋርያዊ የአገልግሎት ጊዜ ለቤተክርስቲያን ያበረከቱቸው አስተምህሮዎች፣ በችግር እና በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ የቅርብ አለኝታ በመሆን፣ ቤተክርስቲያን ምን ጊዜም የቸርነት አገልግሎቶቿን ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ያረጋግጣል ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊን ለቅድስና የሚያበቃቸው ተግባራት ምርምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና፣ መንፈሳዊ አስተምህሮዎቻቸው በዘመናችን እና ለመጭው ትውልድ ከፍተኛ እገዛን የሚሰጥ መሆኑንም ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ገልጸዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
29 April 2020, 14:51