ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ፣  

የትንሳኤው እምነት ሁሉንም ነገር ወደ መልካምነት ሊለውጠው ይችላል ተባለ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ሚያዝያ 3/2012 ዓ. ም. የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ በተደረገው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ ዋዜማ ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ የብርሃነ ትንሳኤውን በዓል የምናከብረው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለማችን ጨለማ ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ነው ብለው፣ በመሆኑም እያንዳንዳችን ቤተሰባዊ ሃላፊነት ሊሰማን ይገባል ብለዋል።      

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ቅዳሜ ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ጥቂት ምዕመናን በተገኙበት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጣሊያን በታየበት የመጀመሪያ ሳምንት፣ የአገሩ ሕዝብ በየመኖሪያ ቤቱ መስኮት ላይ “ሁሉም መልካም ይሆናል” የሚል መልዕክት ጽፈው ማስቀመጣቸውን አስታውሰው፣ ዛሬ ግን በወረርሽኙ ምክንያት የቤተሰብ አባላትን ያጡት በሙሉ ይህን መፈክር መድገም ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በወረርሽኙ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው የተሰናበቱት እና ልጆቻቸውን መመገብ ያልቻሉት ቤተሰቦች ይህን መፈክር መድገም የማያስደስታቸው መሆኑን አስረድተዋል። 

ስብከታቸውን ባቀረቡበት በቅዳሜው ምሽት መሠረታዊ መብታችንን እንቀዳጃለን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሠረታዊ መብታችንም ተስፋን ማድረግ ነው ብለው ይህ አዲስ እና ዘለዓለማዊ ተስፋ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን አስረድተዋል። ተስፋችን የደበዘዘ፣ ከኋላችን የተሸሸገ እና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ብቻችን ሆነን ማግኘት የማንችለው ከሰማይ የወረደ ስጦታ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእርግጥም በእነዚህ ሳምንታት ውስጥ “ሁሉም መልካም ይሆናል” በማለት ልባዊ የማበረታቻ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ወደ ፊት በሰዎች መካከል ፍርሃት እና ጭንቀት እየጨመረ በመጣ ቁጥር ተስፋም ሊጠፋ ይችላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን ተስፋ ከተስፋዎች ሁሉ የሚበልጥ ነው ብለው ከእግዚአብሔር የተሰጠን ተስፋ ከመቃብር ውስጥ ሕይወት እንዲወጣ የሚያደርግ፣ ሁሉንም ነገር ወደ መልካምነት መለወጥ የሚችል ነው ብለዋል።      

የሞትን ኃይል በማሸንፍ መቃብርን ፈንቅሎ የወጣው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በስቅለተ ዓርብ ዕለት በመስቀል ላይ ከፍተኛ ስቃይ እንደደረሰበት ያስታወስነው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። “ይህን ያህል ስቃይ እና ሞት ለምን አስፈለገ” ለሚለው ጥያቄ እግዚአብሔር በቂ ምላሽን ሰጥቶናል ያሉት ቅዱስነታቸው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይን እና ሞትን እንዲቀምስ በማድረግ፣ ስቃይን እና ሞትን የምንቀበለው ብቻችን እንዳልሆነ አረጋግጦልናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሮም ከተማ እና ለመላው ዓለም ባስተላለፉት የብርሃን ትንሳኤው መልዕክታቸው፣ “የእኔ ተስፋ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል” ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የሂሳብ ስሌትን የሚያቃልል አስማታዊ ቀመር ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ፍቅር በጥላቻ ላይ ድልን የተቀዳጀበት፣ በስቃይ እና በሞት መካከል በመጓዝ ክፉን ወደ መልካም የሚቀይር እና የእግዚአብሔር ሃያል ክንዱ የተገለጠበት ነው ብለዋል።            

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የብርሃነ ትንሳኤው መልዕክት ይፋ የሆነው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መላው ዓለም በስቃይ ውስጥ በሚገኝበት ወቅት በመሆኑ ማንንም ሳይለይ ሁሉም ሰው ሃላፊነትን እንዲውስድ የሚያሳስብ መልዕክት መሆኑ ታውቋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምስት ዳቦ እና በሁለት ዓሣ ብቻ የተራበውን በርካታ ሕዝብ እንዳጠገባቸው ሁሉ እኛም ያለንን ጥቂት ነገር ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር መካፈል እንዳለብን የሚያሳስብ መልዕክት መሆኑ ታውቋል።  አሁን የምንገኝበት የስቃይ እና የፍራቻ ጊዜ ስግብግብነትን አስወግደን በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳንፈጥር የደረሰብንን መከራ በጋራ የምንወጣበት ጊዜ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል። በመልዕክታቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የበለጠ ጠንካሮች እንድንሆን አድርጎናል ያሉት ቅዱስነታቸው ፣ በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች ጩኸት በዝምታ መመልከት እንደሌለብን፣ የጦር መሣሪያ ምርት እንዲቆም፣ ዛሬ የሚያስፈልገን ጠብመንጃ ሳይሆን ዳቦ መሆኑን አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር አያይዘው የንጹሐንን ሕይወት ለሞት የሚዳርግ የጽንስ ማስወረድ ተግባር እንዲቆም፣ ለዕለታዊ ኑሮ የሚያስፈልጋቸውን የሚለምኑት ሰዎች እጅ ባዶ እንዳይመለስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።       

ይህን አስመልክተው ለአውሮፓ አገሮች ባቀረቡት ጥሪ፣ መላው የሰው ልጅ በጨለማ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት ቤተሰባዊ ስሜትን በማሳደግ ኃይላቸውን በማስተባበር ፣ እርስ በእርስ መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ብለዋል። የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ሊጋፈጡት የሚገባ የዘመናችን ከባድ ሸክም አለባቸው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህን ክብደት መሸከም የሚችሉት ብቻውን ሳይሆን ከሌሎች የዓለም መንግሥታት ጋር በጋራ መሆኑን አስረድተው አንድነትን እና መደጋገፍን በተግባር በመግለጽ ከችግሩ የሚወጣበትን  የመፍትሄ መንገድን በጋራ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህ ካልሆነ ግን የሚጠብቀን አማራጭ በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነት እና በግል ጥቅም ፍለጋ ውስጥ በመግባት፣ በሰላማዊ ሕይወት ላይ አደጋን በመደቀን የመጭው ትውልድ ዕድገት እንዲደናቀፍ ማድረግ ይሆናል ብለዋል። 

13 April 2020, 20:08