ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚአብሔር ሁሌም ከወደቅንበት ሥፍራ የሚያነሳን አባት ነው” አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም የዳግማዊ ትንሣኤ በዓል ተክብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ይህ የዳግማዊ ትንሣኤ ሰንበት “የመለኮታዊ ምሕረት” ሰንበት በመባል ይጠራል። ይህንን የዳግማዊ ትንሣኤ ሰንበት “የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት” እንዲሆን ያወጁት ከእዚህ ቀደም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ እንደ ነበሩ የሚታወስ ሲሆን ይህንን ሰንበት “የመለኮታዊ ምሕረት ሰንበት” በማለት የሰየሙት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ተሰቃይቶ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ከሙታን መነሳቱ እኛን ከእግዚአብሔር ጋር ለማሳትረቅ የከፈለው ዋጋ በመሆኑ፣ በተጨማሪም “እኔ ይቅር እንዳልኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ይቅር ተባባሉ” ብሎ እኛም እርስ በእርሳችን ይቅር መባባል እንዳለብን በዳግማዊ ትንሣኤ ሰንበት ለሐዋርያቱ በድጋሚ በተገለጸበት ወቅት ማሰሰቡን በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ “መለኮታዊ ምሕረት” በመባል የሚታወቀው የዳግማዊ ትንሣኤ ሰንበት በሚያዝያ 11/2012 ዓ.ም በቫቲካን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት “እግዚአብሔር ሁሌም ከወደቅንበት ሥፍራ የሚያነሳን አባት ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳር ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን የጀመሩት የትንሣኤ በዓል (የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የትንሣኤ በዓል ያመለክታል) ካሳለፈን አንድ ሣምንት መሙላቱን በመግለጽ ሲሆን ምንም እንኳን ደቀ መዛሙርቱ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ቢያዩም በፍርሃት ያሳለፉት ሳምንት እንደ ነበረ ገልጸው (ዮሐ 20፡ 26) ብቸኛው የኢየሱስን ትንሣኤ ያለተመለከተው እና ጣቶቼን በቁስሎቹ ውስጥ አስገብቼ ካላየው በስተቀር አላምንም ያለው ቶማስ ብቻ ከሙታን የተነሳውን ጌታ እስከ እዛ ሰዓት ድረስ አለመመልከቱን ገልጸዋል።

“በዚህ ፍርሃት እና አለመታመን ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ኢየሱስ ምን አደረገ?” በማለት ጥያቄ በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከእዚህ ቀደም በተገለጸላቸው መንገድ በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው (ዮሐ 20፡ 19, 26) የሚለውን ቅዱስነታቸው በስብከታቸው አስታውሰዋል።

“ነገር ግን ሁሌም በአዲስ መልክ እንደገና ይጀምራል፣ የደቀ መዛሙርቱ ትንሣኤ የሚጀምረው ከዚህ ታማኝ ከሆነ ምሕረት እና ትዕግስት ነው፣ እግዚአብሄር ልጆቹ ከወደቁበት ስፋራ ለማንሳት እጆቹን መዘርጋት በጭራሽ እንደ ማይታክት አሳይቶናል” በማለት ስብከታቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛ እርሱን እንደ አንድ ባላባት ሳይሆን ነገር ግን እሱ ሁሌ ከወደቅንበት ሊያነሳን እንደ ሚፈልግ አንድ አባት አድርገን ስለእርሱ በእዚህ መልክ እንድናስብ ይፈልጋል ብለዋል።

ደረጃ በመውጣት ላይ ያለ አንድ ልጅ በሚወድቅበት ወቅት ሁሌም ቢሆን አባቱ ከጎኑ ሆኖ በተደጋጋሚ እንደ ሚያነሳው ሁሉ እግዚአብሔር አባታችንም እኛ ከወደቅንበት ስፍራ በተደጋጋሚ እንደሚያነሳን የገለጹት ቅዱስነታቸው የእኛ እግዚአብሔር የሚወቅሰን ወቃሽ የሆነ አባት ሳይሆን ነገር ግን ከጎናችን ሁኖ ከወደቅንበት ስፍራ የሚያነሳን አባት ነው፣ ያለእርሱ ምሕረት በወደቅንበት ሥፍራ ላይ እንደ ምንቀር እግዚአብሔር ያውቃል፣ ተመልሰን ለመራመድ ደግሞ በእግራችን መቆም እንዳለብንም ይረዳል ብለዋል።

“’ነገር ግን መውደቄን በጭራሽ አላቋረጥኩም’ በማለት ይህንን ሐሳብ ልትቃወም ትችል ይሆናል፣ ጌታ ይህንን በሚገባ ያውቃል እናም አንተን ሁል ጊዜ ከፍ ከፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እርሱ ስለውድቀታችን በተደጋጋሚ እንድናስብ አይፈልግም፣ ነገር ግን በወድቀታችን እና በመከራችን ወቅት አባት ወደ ሆነው ወደ እርሱ እንድንመለከት ይፈልጋል ብለዋል።

ከዛሬ ሃያ አመት በፊት በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ዛሬ እያከበርን እንደ ምንገኘው በዳግማዊ ትንሣኤ በዓል ቀን የተከበረው “የመለኮታዊ ምሕረት” እለተ ሰንበት በተከበረበት ወቅት ቅድስት ፉስቲና ዘኢየሱስ “እኔ ፍቅርና ምሕረት ነኝ ፣ ከእኔ በላይ የሆነ መከራ የለም” ብሎ ኢየሱስ እንደነገራት መናገሯን ያስታወሱ ሲሆን  በመሆኑም ውድቀቶቻንን እና ደክመቶቻችንን በሙሉ ለእግዚአብሔር ልናቀርባቸው ይገባል ብለዋል።

“ወደ ደቀ መዛሙርቱ እንመለስ። በሕማማቱ ወቅት ጌታን ብቻውን ትተውት ስለነበረ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እነሱን መልሶ ባገኛቸው ወቅት በጣም ረጅም የሆነ ስብከት አላደረገም ነበር። ውስጣቸው በጣም ቆስሎ ለነበረው ለእነርሱ አካላዊ የሆነ ቁስሉን አሳያቸው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “በእነዚያ ቁስሎች ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ፍቅር በእጁ የነካው ቶማስ ፣ ምህረትን በተቀበለ ጊዜ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት የላቀ ሆነ፣ በትንሣኤ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔርን ወሰን የሌለው ፍቅር ተቀበለ” ብለው ቀለል ባለ መልኩ ነገር ግን ይበልጥ ውብ በሆነ መልኩ “ጌታዬ እና አምላኬ!” በማለት ቶማስ ምስክርነት እንደ ሰጠ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች አሁን በምንገኝበት የፈተና ወቅት እኛም እንደ ቶማስ በፍርሃቶቻን እና በጥርጣሬዎቻችን ውስጥ በመግባት ደካሞች እንደ ሆንን ተረድተናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከአቅማችን በላይ የሆነ ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ውበት በእኛ ውስጥ የሚመለከተውን ጌታ እንፈልጋለን በልዋል። በእርሱ አጋዢነት ድክመቶቻችንን ለይተን ለማወቅ እንችላለን ያሉት ቅዱስነታቸው በተመሳሳይ ጊዜም የእርሱ የተወደድን እና ክቡር የሆንን ልጆቹ መሆናችንን ለመረዳት እንችላለን፣ በፊቱ ግልጽ ሆነን በምንቀርብበት ወቅት የእርሱ ብርሃን፣ የምሕረት ብርሃን በእኛ ውስጥ በማለፍ በእኛም በኩል በዓለም ውስጥ ሊያበራ ይችላል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

19 April 2020, 09:54