ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ሕይወት ጥበቃ የማደረግ ኃላፊነት ተጥሎባታል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 16/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር ረቡዕ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤና ባለሙያዎች ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ያስተላለፉት ሳምንታዊ አስተምህሮ እንደ ነበረ ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉት አስተምህሮ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 16/2012 ዓ.ም የተከበረውን መልአኩ ገብርኤል ማርያምን ባበሰራት ወቅት የዓለም መድሕኒት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ አስቀድሞ ማብሰሩን በሚገልጸው (ሉቃስ 1፡26 38 ) የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ቤተክርስቲያን ለሰው ልጆች ሕይወት ጥበቃ የማደረግ ኃላፊነት ተጥሎባታል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 16/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ልክ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ  መበሰሩ የሚታወስበት ዓመታዊ በዓል በመጋቢት 16 በተከበረበት ወቅት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በላቲን ቋንቋ “Evangelium vitae” (በአምርኛ በግርድፉ ሲተረጎም የሕይወት ወንጌል) በሚል አርእስት የሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ ያለው በመሆኑ የተነሳ ሊጣስ የማይገባው ክብር እንዳለው የሚገልጽ አንድ ሐዋርያዊ መልእክት በወቅቱ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት አጽኖት ሰጥተው እንደ ገለጹት የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ የተበሰረበት በዓል እና “የሕይወት ወንጌል” (Evangelium vitae) በተሰኘው እርሳቸው ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት መካከል ያለው ግንኙነት ቅርብ እና ጥልቅ ነው። ዛሬ ይህንን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የሰውን ሕይወት እና የዓለም ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ከሚጥል ወረርሽኝ ሁኔታ ጋር እያነፃፀርን እንመለከታለን። ይህ ሐዋርያዊ መልእክት የሚጀምርበትን ቃል እንደ ገና በጥልቀት እንድንመለክት በሚያደርገን ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን።  ይህም “የሕይወት ወንጌል” በኢየሱስ መልእክት ልብ ውስጥ ማዕከላዊ የሆነ ስፍራ አለው። በየቀኑ ቤተ-ክርስቲያን በፍቅር የተደገፈች፣ በሁሉም እድሜ እና ባህሎች ውስጥ ላሉት ሰዎች እንደ መልካም ዜና ሆኖ በድፍረት እና በታማኝነት መታወጅ ያለበት የምስራች ቃል ነው” ይለናል።

እንደማንኛውም የወንጌል ምልእክት ይህ የመጀመሪያው የቅዱስ ወንጌል ምስክርነት መሆን አለበት። እናም የታመሙትን፣ አረጋውያንን፣ በብቸኝነት ውስጥ የሚገኙትን እና በጣም ችግረኛ የሆኑትን ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ለማገልገል የተቻላቸውን ብዙ ጥረት በዝምታ በማደርግ ምስክርነት እየሰጡ የሚገኙት ሰዎች ላመስገን እወዳለሁ። እነሱ የመልአኩን ቃል እንደተቀበለችው እና የአጎቷን ልጅ ኤልሳቤጥን በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ ለማገዝ እና ለመርዳት እንደ ሄደችው ማርያም የሕይወት ወንጌልን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ።

በእውነቱ እንድንጠብቀው እና እንድንከባከበው የተጠራነው ሕይወት ረቂቅ የሆነ ፅንሰ-ሀሳብ አይደለም፣ ነገር ግን ሁል ጊዜ ስጋ እና ደም በለበሰ በአንድ ሰው ውስጥ በቀላሉ የሚታይ ነገር ነው፣ አዲስ የተፀነሰ ልጅ ፣ ደካማ የሆነ አንድ ደሃ ሰው፣ ብቸኛ የሆነ እና ተስፋ የቆረጠ አንድ በሽተኛ ወይም በመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ አንድ በበሽታ የተጠቃ ሰው፣ አንድ ሥራ ያጣ ወይም ማግኘት ያልቻለ ሰው፣ ተቀባይነት ያጣ ወይም በማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ስደተኛ የሆነ ሰው ...ወዘተ፣ ሕይወት በእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ውስጥ ሳይቀር ይገለጻል።

እያንዳንዱ ፍጡር በሕይወት ሙሉነት ለመደሰት በእግዚአብሔር ተጠርቷል፣ እናም ለቤተክርስቲያኗ የእናትነት ሀላፊነት በአደራ የተሰጠ ሲሆን ክብሩ እና ሰብአዊው ሕይወትን ሁሉ አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባሮች የእናትነት “አንጀት”ያላትን ቤተክርስቲያን ልብን ሳይነካ የሚያልፍ ነገር አይደለም። የቤተክርስቲያኗ የህይወት ማዕከል ርዕዮተ-ዓለም አይደለም፣ እውነት እንጂ፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚመለከት ሰብዓዊ የሆነ እውነት ነው፣ ምክንያቱም እነርሱ በትክክል ክርስቲያን እና ሰው በመሆናቸው የተነሳ ነው።

እንደአለመታደል ሆኖ እኛ አሁን በምንገኝበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ  ተብሎ በሚታመንበት ወቅት ላይ እንገኛለን፣ በተቃራኒው በሰዎች ክብር እና ሕይወት ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች እየቀጠሉ ይገኛሉ፣  በእኛ ላይ አዳዲስ ስጋቶች እና አዲስ የባርነት ዓይነቶች ተጋርጠውብናል፣ እናም ሕግ ሁልጊዜ ደካማውን እና በጣም ተጋላጭ የሆነውን የሰውን ሕይወት ለመጠበቅ እየተጋ አይደለም።

ስለሆነም (በላቲን ቋንቋ “Evangelium vitae” የሕይወት ወንጌል በሚል አርእስት ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ መልእክት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ላለንበት ወቅት ጠቃሚ ነው። እኛ እሁን ከምንገኝበት ድንገተኛ ከሆነ ሁኔታ ባሻገር በመሄድ እኛም እነዚህን እሴቶች በሚገባ በመረዳት እና በደንብ በማወቅ ለመጪው  ትውልድ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ በባህል ዘርፎች እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲተገበሩ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ሊተገበር የሚገባው ደግሞ በክርስትያኖች ላይ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሰዎች በቅርበት እንዲገናኙ ጥረት በሚያደርጉ የእያንዳንዱን ሰዎች እሴት በሚገነዘቡ ሰዎች ሁሉ ላይ ሊሆን የገባል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች! እያንዳንዱ ሰብዓዊ ሕይወት ልዩ እና የማይተካ፣ በራሱ ትልቅ ክብር ያለው፣ ለእራሱ ትክክለኛ ነው ፣ እጅግ ጠቃሚ ዋጋ ያለው ነው። ይህ ዋጋ በቃል እና በድርጊቶች በታጀበ መልኩ  በድፍረት ሁል ጊዜ እንደገና መታወጅ አለበት። ይህ የታላቁ የሰው ልጅ እና የእያንዳንዱን አባላቱ ትብብር እና ዘላለማዊ ፍቅርን ይጠይቃል።

ስለዚህ ይህንን ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንድንተገብረው የጠየቁበት ሐዋርያዊ መልእክት እንደገና ለማደስ እፈልጋለሁ፣ “እያንዳንዱን ሕይወት፣ እያንዳንዱ ሰብዓዊ ሕይወት፣ ሊወደድ እና ሊከበር የገባዋል! ፍትህ፣ ልማ ፣ ነፃነት፣ ሰላምና ደስታ ሊገኙ የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
25 March 2020, 16:43