ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ያስተላለፉት መልእክት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ያስተላለፉት መልእክት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን በማገልገል ላይ ለሚገኙ ሰዎች ልንጸልይላቸው ይገባል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 06/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤን ባለሙያ ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረጋቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ካገባደዱ በኋላ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት ለምዕመናን ባስተላለፉት መልእክት ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በአሁኑ ወቅት በስፋት በሚስተዋለው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዝግ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በእዚህም ምክንያት “የብዙሃን የመገናኛ መስመሮችን ተጠቅሜ ሰላምታዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።

“ይብለጥም ወይም ይነስም በእዚህ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተገለን በቤታችን እንድንቀመጥ ተገደናል” በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በዚህ ወረርሽኝ ሁኔታ ውስጥ  ሁሉንም የቤተክርስቲያኗ አባላት የሚያቀራርበውን ህብረት እንደገና እንድናውቀው እና በጥልቀት በጸሎት መንፈስ እንድንፈጽም ተጋብዘናል ብለዋል። ከክርስቶስ ጋር አንድ በምንሆንበት ጊዜ በጭራሽ ብቻችንን አይደለንም ፣ ነገር ግን የእርሱ ራሱ አንድ አካል እንሆናለን በማለት በሳምንታዊ መልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው በእሁኑ ወቅት እየተከሰተ በሚገኘው የኮርና ቫይረስ ምክንያት ወደ ቤተክርስቲያን ሂደን ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የማንችለበት ወቅት ላይ በመሆናችን በጸሎት በመተጋት መንፈሳዊ ሕብረታችንን ማጠናከር የገባናል ብለዋው፣ በተለይም ደግሞ ለብቻቸው ለሚኖሩ ሰዎች ልንጸልይላቸው የገባል ብለዋል። ለታመሙ ሁሉ እና የታመሙ ሰዎችን ለሚንከባከቡ ሁሉ ጸሎቴ ከእነርሱ ጋር ነው በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እንዲሁም ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት ለማይችሉ ሰዎች እና ድሆችን እና ቤት አልባ የሆኑ ሰዎችን ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመትጋት ላይ ለሚገኙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና የበጎ ተግባር ተሳታፊ ሰዎችን ላመሰግን እፈልጋለሁ፣ ለእነርሱም ልንጸልይላቸው የገባል ብለዋል።

በዚህ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዳችንን ለመርዳት የተቻላችሁን ሁሉ እያደረጋችሁ ለምትገኙ ሰዎች ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ይባርካችሁ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትጠብቃችሁ፣ “እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትረሱ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ሳምንታዊውን መልእካታቸውን አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
15 March 2020, 11:30