ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የእኛ ክርስትና ምሕረት አድራጊዎች እንድንሆን ሊረዳን ይገባል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ዘወትር ረቡዕ ለሚገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተንተርሰው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 09/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር ረቡዕ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤና ባለሙያዎች ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ያስተላለፉት ሳምንታዊ አስተምህሮ እንደ ነበረ ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉት አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ላይ በተጠቀሰውና ኢየሱስ በተራራ ላይ ባደረገው ስብከት ዙሪያ ላይ ቀደም ሲል ያደርጉት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” (ማቴ 5፡7) በሚለው በእዚህ ኢየሱስ በተራራው ላይ ባደርገው ስብከት አምስተኛው ጭብጥ ላይ ተንተርሰው ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የእኛ ክርስትና ምሕረት አድራጊዎች እንድንሆን ሊረዳን ይገባል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 09/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት በምናደርገው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ  “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” (ማቴ 5፡7) በሚለው የተራራው ላይ ስብከት ትኩረት እናደርጋለን። በዚህ የተራራው ስብከት ክፍል ውስጥ አንድ ልዩ የሆነ ነገር አለ፣ ይህም ብቸኛው የደስታ ምንጭ ምህረት ማደረግ እንደ ሆነ ይናገራል። ምህረት የማደረግ ተመክሮ ያላቸው ሰዎች እነርሱም በፊናቸው ምሕረት ያገኛሉ።

የይቅር ባይነት ዋና ገጽታ በዚህ የተራራው ላይ ስብከት ውስጥ የተገለጸ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በተለያየ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በተደጋገሚ ተገልጹዋል። ደግሞስ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምሕረት የእግዚአብሔር ልብ ነው! ኢየሱስ “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ” (ሉቃስ 6:37) ብሎ ተናግሩዋል። ብዙ ጊዜም በተመሳሳይ መልኩ ተናግሮናል። የያዕቆብ መልእክት “ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል” (2፡ 13) በማለት ይናገራል።

ነገር ግን ከሁሉም በላይ አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” (ማቴ 6፡12) ብለን የምንጸልየው ጸሎት ከሁሉም በላይ ነው።  እናም የእዚህ ጸሎት መደምደሚያ የሚሆነው “እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም” (ማቴ 6፡14 15) የሚለው ነው።

በእዚህ ረገድ ሁለት የማይለያዩ ነገሮች አሉ፣ እነዚህም ይቅርታን ማደረግ እና ይቅርታን መቀበል ናቸው። ነገር ግን በጣም ብዙ ሰዎች ችግር ላይ ናቸው፣  ምክንያቱም ይቅር ማለት ያስቸግራቸዋልና። ብዙ ጊዜ የተፈጸመብን ክፉ ነገር እጅግ በጣም ከባድ እና በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ይቅር ማለት ያስቸግረናል፣ በእዚህ ረገድ ይቅር ማለት ወደ አንድ እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ ላይ እንደ መውጣት ሆኖ ሊሰማን ይችላል፣ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነገር መስሎ ሊታየን ይችል ይሆናል። በእዚህ ሐሳብ የተነሳ ‘ይቅርታ ማደረግ የማይታሰብ ነገር ነው!’ ወደ ሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፣ ይህ ሊከናወን አይችልም በማለት እናስባለን። ይህ ምህረትን ሰጥቶ ምህረት መቀበል ጥልቀት ያለው እውነታ የሚጠቁመን ቀደም ሲል የተጠቀሰውንና ‘ምህረት ማድረግ ከባድ ነው’ የሚለውን ሐሳብ ወደ ጎን መተው እንዳለብን ያሳየናል። ነገር ግን ብቻችንን ይህንን ማከናወን አንችልም: - የእግዚአብሔርን ፀጋ ማግኘትን ይጠይቃል፣ ይህንን ጸጋ እንዲሰጠን ልንጠይቀው ይገባል። በእውነቱ ኢየሱስ በተራራው ላይ ያደርገው ስብከት አምስተኛው ጭብጥ ምህረትን ለማግኘት ቃል የገባልን እና አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ሁሉ ይቅር በልልን ብለን እንደ ምንጠይቅ ሁሉ ምህረትን ለመቀበል፣ ምሕረት ማድረግ ይጠበቅብናል ማለት ነው!

ሁላችንም ዕዳ አለብን። ሁላችንም! ለጋስ የሆነው የእግዚአብሔር እና የወንድሞቻችን ዕዳ አለብን።  ሁላችንም በሕይወት ውስጥ ድክመቶች አሉን።  ምሕረት ያስፈልገናል። ምንም እንኳን መጥፎ ነገር ብንሠራም  ማድረግ ያለብን በጎ ነገር እንዳለ እና ሁል ጊዜ የሚጎድለን ነገር እንዳለ እናውቃለን።

በትክክል ይህ የእኛ ድህነት ምሕረት አዳራጊዎች እንድንሆን ጥንካሬ ይሆነናል! ቀደም ሲል እንደሰማነው ለሌሎች በምንስፍርበት መስፈሪያ ነው ለእኛም የሚሰፈርልን (ሉቃስ 6፡38)፣ ስለእዚህ መስፈሪያችንን  ማስፋት እና በእዚያው ልክ ዕዳዎችን ይቅር እንዲባሉ ማደርግ ይኖርብናል። ሁሉም ሰው ይቅር ማለት ፣ ይቅታን መሻት እና ትዕግስት ማደረግ እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለበትም። ይህ የምህረት ምስጢር ነው: - ይቅር ማለት ይቅርታ ያስገኛል። አስቀድሞ ምሕረት ያደረገልን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የእርሱን ምሕረት መቀበል በምላሹ ይቅርታ የማድረግ ችሎታ እንዲኖረን ያደርጋል። ስለዚህ የአንድ ሰው መከራ እና የፍትህ እጥረት በራሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድንሻ አጋጣሚውን የሚከፍትልን ሲሆን ​​ወደ እግዚአብሄር ልኬት፣ ማለትም ምህረትን ለመግለጽ እድሉን ይከፍትልናል።

እኛ የምናደርገው ምህረት ከየት ነው የመጣው? ኢየሱስ “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናትም ርኅሩዎች ሁኑ!” (ሉቃ 6፡36) ይለናል። የአባታችንን ፍቅር የበለጠ በተቀበልን ቁጥር የበለጠ መውደድ እንችላለን (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2842)። ምሕረት ከሌሎች ነገሮች መካከል አንዱ ልኬት አይደለም ፣ ነገር ግን የክርስትና ሕይወት ማዕከል ነው፣ ያለ ምሕረት ክርስትና አይኖርም። የእኛ ክርስትና ሁሉ ወደ ምሕረት አንድናመራ የማያደርገን ከሆነ የተሳሳተውን መንገድ ወስደናል ማለት ነው፣ ምክንያቱም ምሕረት የሁሉም መንፈሳዊ ጉዞ እውነተኛ ግብ ነውና። ምሕረት በጣም መልካም ከሆኑ የበጎ አድራጎት ሥራ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ ነው (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1829)።

የእግዚአብሔር ምሕረት ነፃነታችን እና ደስታችን ነው። የምንኖረው በምሕረት ነው፣ እናም ያለ ርህራሄ አቅም የለንም፣ ምሕረት እንደምንተነፍሰው አየር ነው፣ ያስፈልገናል። እኛ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳናስቀምጥ ይቅር ማለት አለብን፣ ምክንያቱም እኛም ምሕረት ማግኘት ይኖርብናልና።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
18 March 2020, 15:54