ፈልግ

የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የበላይ መስተዳድር በዓብይ ጾም ወቅት ሱባኤ ላይ ሆነው፣  የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የበላይ መስተዳድር በዓብይ ጾም ወቅት ሱባኤ ላይ ሆነው፣  

አባ ፔትሮ ቦቫቲ “መልካም ሥራዎቻችን በሙሉ በእግዚአብሔር እጅ የሚከናወኑ ናቸው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የበላይ መስተዳድር የቅርብ የሥራ ተባባሪዎች ጋር በመሆን በየወቅቱ እንደ አስፈላጊነቱ ሱባኤ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሠረት አሁን የምንገኝበትን የዐብይ ጾም ወቅት ምክንያት በማድረግ ከባለፈው የካቲት 22/2012 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ጣሊያን በምትገኝ አሪቻ በምትባል ስፍራ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  ከቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የበላይ መስተዳድር አካላት ጋር ሆነው የዐብይ ጾም ሱባዔ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገልጹዋል። በጳጳሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሚሽን ውስጥ የነገረ መለኮት ትምህርት ምሁር እና የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል የሆኑት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ የዘንድሮ አመታዊ ሱባዔ መሪ መሆናቸው ታውቋል። አባ ቦቫቲ፣ ትናንት የካቲት 25/2012 ዓ. ም. በዋለው አራተኛ የሱባኤ ቀን ባቀረቡት አስተንትኖ፣ ለሌሎች የምናበረክታቸው መልካም ሥራዎቻችን በሙሉ በእግዚአብሔር እገዛ፣ በእርሱን እጅ የሚከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጽሐፈ ዘፀአት ታሪክ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት አባ ቦቫቲ ፣ ምድረ በዳ የነፃነት ቦታ፣ እግዚአብሔር ለእስራኤላዊያን የገባውን ቃል ኪዳን የገለጸበት፣ ታማኝነቱን እና መልካምነቱን ያሳየበት፣ የሰማይ ኃይሎች የሚታዘዙለት፣ ሁሉን ቻይ እና ገዥ አምላክ መሆኑን የገለጸበት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል። አባ ፔትሮ ቦቫቲ አክለውም እግዚአብሔር ራሱን “የመዳን ታሪክ ባለቤት” እንደሆነ ካሳየ በኋላ በሌላ በኩል ደግሞ “ሰዎች በምድረ በዳ ያላቸውን ነጻነት በመጠቀም በፈጣሪ ላይ እስከማመጽም የሚደርሱበት” ነው ብለዋል። የሰዎችን ተግባር የማይናገር ወይም የማይገልጽ ታሪክ የተዛባ ይሆናል ብለው ሰዎች የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸም የእግዚአብሔር አስደናቂ ተግባር በሥራዎቻቸው መካከል እንዲገለጥ ካላደረጉ ኑሮአቸው ትርጉም አይኖረውም ብለዋል። እግዚአብሔር በሥራው እንዲከብር፣ በፍጥረታቱ እንዲወደስ  የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳልነት እና በተሰጠው ነጻነት በዘመናት ሁሉ ታሪክን በመሥራት መተባበር ይኖርበታል ብለዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስብስብ እና ብዙውን ጊዜ ተጓዳኝ ናቸው ያሉት አባ ቦቫቲ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እግዚአብሔር በሥራዎቹ መካከል ለሰዎች የተለየ ግምት እንደሚሰጥ፣ ለሚያከናውኑት ተግባርም ምላሽ መስጠትን ይፈልጋል ብለው፣ በሚያከናውኑት ተግባራት ላይ ጫናን ሳይፈጥር ከፍጥረታት ጋር ያለውን ትብብር እና አንድነት በማጠናከር በእርሱ የማዳን ሥራ እንዲተባበሩ በማድረግ መመካትን ይፈልጋል ብለዋል።

ምድረ በዳ “የሕይወት ምሳሌ” ነው፣

የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ያሳለፏቸው አርባ ዓመታት፣ ዛሬ የሰው ልጅ በስቃይ ውስጥ የሚገኝበትን ምድራችንን ያመልክታል ያሉት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ በዚህም መካከል እግዚአብሔር ለልጆቹ የራሱን አለኝታነት የሚገልጽበት ነው ብለዋል። በመሆኑ የእርሱ አገልጋይ የሆኑት በሙሉ በሚኖሩበት ምድር የሚያከናውኗቸው ተግባራት በእግዚአብሔር እጅ እና በእርሱ እገዛ የሚከናወኑ ናቸው ብለዋል። የእግዚአብሔርን ድምጽ በሚያዳምጡበት ጊዜ የእርሱ አገልጋዮች ሁለት ነገሮችን ያከናውናሉ ብለው፣ የመጀመሪያው በምድራዊ ኑሮ የእግዚአብሔርን ድምጽ፣ የእርሱን ትዕዛዝ ማዳመጥ ሲሆን ሁለተኛው፣ የእግዚአብሔር አደራ ያለብንን የእርሱን ሕዝብ ስቃይ ማዳመጥ ነው ብለዋል።       

ምድረ በዳ “የሕይወት ምሳሌ” ነው በማለት የገለጹት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ የምድረ በዳ ሕይወት ሰዎች የሚፈተኑበት፣ በምንም መልኩ ይሁን ኑሮአቸውን የሚገፉበት ጊዜ እንደሆነ አስረድተው፣ በዚህ ምድራዊ ሕይወት ሕዝቡ ፈተናን በማለፍ ጥንካሬን የሚያገኙበት፣ በእምነት የምናድግበት፣ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሙሴ ለሕዝቡ እንዳደረገው እርስ በእርስ የምንደጋገፍበት ነው ብለዋል። መልካም ምላሽን ባይስጣቸውም፣ ፍላጎታቸውን ማሟላት ባይችልም ሙሴ በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ሕዝብ ጩኸት ማዳመጡን አስታውሰዋል። ሙሴ የሕዝቡን ድምጽ የሰማበት ዋናው ምክንያት የእግዚአብሔን ፈለግ በመከተል መሆኑን አባ ፔትሮ ቦቫቲ አስረድተዋል። ጸሎቶቻችንም እንኳ ሳይቀር ሁልጊዜ ፍጹም አይደሉም፤ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጩኸትም ብዙን ጊዜ መልስ አያገኝም ያሉት አባ ፔትሮ ቦቫቲ ሙሴ በምድረ በዳ ውስጥ ፈተናን ለማሸነፍ፣ ለጥያቄዎቹም መልስን ለማግኘት እግዚአብሔርን በታማኝነት ይለምን ነበር ብለዋል።

በፍቅር ስንኖር እራሳችንን ፍቅር እናስተምራለን፣

ክቡር አባ ፔትሮ ቦቫቲ የዐብይ ጾም ወቅት ሱባኤ አስተንትኗቸውን በመቀጠል እንዳስረዱት፣ በብሉይ ኪዳን እንደተገለጸው ሁሉ እግዚአብሔር በምድረ በዳ ለላካቸው ሕዝቡ አንድ ሕግ አዘጋጅቶ መስጠቱን አስታውሰው ይህም እርስ በእርስ እንዲተጋገዙ የሚል እና ትዕዛዙን ፈጸመው በመገኘት ከአምላካቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ያጸናሉ ብለዋል። እርስ በእርስ በመተጋገዝ እና በፍቅር ስንኖር እራሳችንን ፍቅር ማስተማር እንጀምራለን ያሉት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ ለስጋችን በምናደርገው የምሕረት ተግባር ለመንፈሳችንም የሚሆን የምሕረት ተግባር ከመፈጸም በተጨማሪ ወደ ሰዎች ልብ ውስጥ በመግባት፣ እግዚአብሔርን ወደ ማመን እንዲደርሱ በማድረግ፣ እርሱ የሚፈልገውን የፍቅር ተግባር እንዲያከናውኑ እናደርጋለን ብለዋል።

ክቡር አባ ፔትሮ ቦቫቲ በዕለቱ ያቀረቡት አስተንትኖ ከማጠቃለላቸው በፊት፣ የመጨረሻውን የፍርድ ቀን የሚያሳታውሰውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስታወስ ባሰሙት ስብከታቸው መላው የፍርድ ሂደት በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ነው ብለው እርሱም ለተቸገሩት እና አቅመ ደካማ ለሆኑት በምናቀርብላቸው እርዳታ ወይም ሳናደርግላቸው በምንቀረው ተግባር ላይ የተመሠረተ ነው ብለው፣ የተቸገረን ለመርዳት በምንሞክርበት ጊዜ ከስጋዊ ስቃይ ለማዳን ብቻ ሳይሆን ልቡንም በፍቅር ማሸነፍ ይቻላል ብለዋል። በተናቁት፣ ስቃይ እና መከራ በደረሰባቸው ሰዎች በስተጀርባ ኢየሱስ ክርስቶስ መኖሩን ያስታወሱት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ “የተቸገሩትን፣ የደኸዩትን እና የተሰቃዩትን በምንረዳበት ጊዜ እግዚአብሔርን እራሱን እንደረዳን በዓይናችን ማየት የሚቻለው እንዴት ነው”? ያሉት አባ ፔትሮ ቦቫቲ፣ ያለ ምስጋና፣ አድናቆትን ሳንጥብቅ በእርግጥ ሌሎችን እንደምንወድ የምናውቀው እስከ ሞት ድረስ ሌሎችን የምንወድበት የፍቅር ስጦታ እንደተሰጠን፣ የተትረፈረፈ የመልካም ነገር ሁሉ ባለቤቶች በመሆናችን እና በእግዚአብሔር የተባረከ ሕይወት ባለቤቶች በመሆናችን ነው በማለት በዕለቱ ያቀረቡትን አስተንትኖአቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 March 2020, 17:12