ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል መሪ ቃል ለተከበረው ሳምንት ያስተላለፉት መልእክት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካቲት 24/2012 ዓ. ም. ለመላው ዓለም ካቶሊካዊ ምዕመናን በላኩት የቪዲዮ መልዕክት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚል ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ይፋ ያደረጉበት አምስተኛ ዓመት፣ ከግንቦት 8 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ እንዲከበር በማለት ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ይህ ተነሳሽነት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች፣ ማህበረሰቦች ፣ ሀገረ ስብከቶች ፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማትም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያግዛል ተብሏል። 

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንትን ካቶሊካዊ ምዕመናን እንዲያከብሩት በመጠየቅ በላኩት የቪዲዮ መልዕክታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሳሰቡት፥ “ከእኛ ቀጥሎ ለሚመጣ ትውልድ፣ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሕጻናት ምን ዓይነት ዓለምን ማውረስ እንፈልጋለን? በዚህ ጥያቄ በመነሳሳት ከግንቦት 8-16/2012 ዓ. ም. ድረስ በሚከበረው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ እንድትሳተፉ አደራ እላለሁ። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ የሆነበት አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤን እና ጥበቃን እንድናደርግላት የሚያሳስብ መልካም አጋጣሚ ነው። በዚህ አጋጣሚ ምድራችንን ላጋጠማት ከፍተኛ ቀውስ ፈጣን ምላሽ እንድንሰጥ በማለት ያቀረብኩትን ጥሪ በድጋሚ ማቅረብ እወዳለሁ። የምድራችን ስቃይ እና የድሆች እንባ ማብቂያ ሊኖረው ይገባል። የፍጥረታት ጸጋ፣ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር የተሰጠን መልካም እና ውብ ስጦታ በመሆኑ፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ ልናደርግለት ይገባል። በመሆኑም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል በጋራ እናክብር። ሁላችሁንም እግዚአብሔር ይባርካችሁ እያልኩ በጸሎታችሁ አስታውሱኝ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።       

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ ከሆነ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ አምስት ዓመታት ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ማኅበራት ሁለ ገብ ሥነ-ምህዳራዊ እይታን በተግባር ለመግለጽ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል።

ሆኖም በመኖሪያ አካባቢያችን እና በምድራችን ላይ እየደረሰ ያለው ቀውስ ፍጥነቱን ጨምሮ በመገስገስ ላይ መሆኑ ተስተውሏል። በተፈጥሮ ላይ እየደረሰ ያለ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የተመለከቱት የዓለማችን ሕዝቦች፣ ለችግሩ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አስቸኳይ መመሪያን መፈለጋቸው ታውቋል።

ይህን የመላው ዓለም ሕዝብ ጥያቄ መሠረት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር፣ መላውን ካቶሊካዊ ምዕመናን በማበረታታት፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከገባችበት ቀውስ እንዲያወጧት የሚያግዝ፣ ከግንቦት 8 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚከበር “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ክብረ በዓል ማዘጋጀታቸው ታውቋል። በዚህም መሠረት መላው ምዕመናን ከበዓሉ በኋላ ኃይሉን በማስተባበር የበኩሉን እርምጃ እንዲወስድ በማለት ቅዱስነታቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።   

ከተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች በኩል የሚወሰዱ ገንቢ እርምጃዎች ተቀባይነት እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን እነዚህን እርምጃዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ መመሪያዎች “ውዳሴ ላንተ ይሁን ሳምንት” ወይም “Laudato Si’ Week” በሚለው ድረ ገጽ ላይ በዝርዝር መቀመጡ ታውቋል። በዚህም መሠረት የተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ጠቅላላ መመሪያዎችን ከድረ-ገጹ በመቀበል እንዲታገዙ እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር መጋራት የሚችሉ መሆናቸውን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ከግንቦት 8 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚከበር “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል፣ የአካባቢ ጥበቃን  ከሚመለከቱ ሌሎች በዓላት ጋር በሕብረት የሚውል መሆኑ ሲታወቅ፣ የያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. የዓለም መንግሥታት፣ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ግቦችን ለማሳካት ያወጡትን ዕቅዶች የሚያሳውቁበት ዓመት መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በብዝሀ ሕይወት ላይ የሚወያይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ፣ የሰው ልጅ የሚኖርበትን አካባቢ እና የነፍሳትዘሮችን በሙሉ ከጥፋት ለመከላከል ያቀዳቸውን እቅዶች ወደ ግብ ለማድረስ የሚያስችል ውጤታማ ውይይቶችን ለማድረግ መልካም አጋጣሚ የሚያመቻች መሆኑ ታውቋል።         

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግንቦት ወር የሚከበረውን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል፣ በደቡባዊ ምዕራብ ጣሊያን በሚገኝ “ቴራ ደይ ፉዎኪ” በተባለ፣ በአንድ ወቅት የተለያዩ ዕጽዋዕት የሚበቅልበት ለም ሥፍራ፣ ዛሬ ግን አመድ እና ጭስ በሚወጣበት ሥፍራ ተገኝተው የሚያከብሩ መሆኑ ታውቋል።

ከግንቦት 8 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አምስተኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ያዘጋጀው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከ“ግሎባል ካቶሊክ ክላይሜት ሙቭሜንት” እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 March 2020, 16:48