ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄ የሚያሳየውን ኢየሱስ ምሳሌ ልንከተል ይገባል" አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 20/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤን ባለሙያ ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረጋቸው ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል 11፡ 1-45 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው” በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄውን የሚሰጠንን የኢየሱስ ምሳሌ መከተል እንችል ዘንድ እናቱ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል” ማለታቸው ተገልጹዋል

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅታችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱ እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው (መጋቢት 20/2012 ዓ.ም) በአምስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት እለተ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 11፡1/45) የአልዓዛር ከሞት መነሳት ይገልጻል። አልዓዛር የኢየሱስ ወዳጆች የነበሩት  የማርታ እና የማሪያ ወንድም ነው። ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ያህል ሞልቶት ነበር፣ ማርታ ጌታን ለመገናኘት ሮጣ በመሄድ “እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ አይሞትም ነበር” (ዮሐንስ 11፡ 21) አለችው። ኢየሱስም “ወንድምሽ ይነሳል” (ዩሐንስ 11፡23) በማለት መለሰላት። “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል” (ዩሐንስ 11፡25) በማለት አክሎ ይናገራል። ለሙታን እንኳን ሕይወት የመስጠት ችሎታ ያለው መሆኑን እና ኢየሱስ ራሱን የሕይወት ጌታ መሆኑ ይገልጻል። ከዚያም በኋላ ማርያም እና እርሷን ተከትለዋት የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን “ኢየሱስ መንፈሱ በኀዘን ታወከ፣ ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ” (ዮሐንስ 11፡ 33. 35)። ይህንን የሁከት ስሜት በልቡ ውስጥ ይዞ ወደ መቃብሩ ስፍራ ይሄዳል፣ ሁል ጊዜም ቢሆን ጸሎቱን የሚሰማውን አባቱን እያመሰገነ መቃብሩን አስከፍቶ “አልዓዛር ፣ ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምጽ ተጣራ (ዮሐንስ 11፡43)። አልዓዛርም “እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ”  (ዮሐንስ 11፡44)።

እዚህ ላይ እግዚአብሄር ሕይወት መሆኑን እና ሕይወት ሰጪ መሆኑን ተጨባጭ በሆነ መልኩ እንመለከታለን። ኢየሱስ ወዳጁ የነበረውን የአልዓዛር ሞት አስቀድሞ ማስቅረት ይችል የነበረ ሲሆን ነገር ግን የምንወዳቸው ሰዎች ከእኛ በሞት በሚለዩበት ወቅት የሚሰማንን ከፍተኛ ሐዘን ኢየሱስ የራሱ ሐዘን አድርጎ በመቁጠር እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር በሞት ላይ ያለውን ስልጣን ለማሳየት ይፈልጋል። በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ የሰዎች እምነት እና የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚፈልጉ ሁሉ በመጨረሻም እንደሚያገኙት እናያለን። ማርታ እና ማርያም እንዲሁም ሁላችንም “አንተ አዚህ ብትኖር ኖሮ . . . ” ብለን የምናሰማውን ጩኸት እናያለን። የእግዚአብሔር መልስ ግን ወሬ አልነበረም፣በፍጹ እንዲህ አልነበረም! ሞት ላስከተለው ችግር የእግዚአብሔር መልስ ኢየሱስ ነው-“ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ… በእኔ እምነት ይኑራችሁ! ለቅሶ ሲያጋጥማችሁ በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ፣ ሞት አሸናፊ ሆኖ የሚወጣ ቢምስላችሁ እንኳን በእኔ ማመናችሁን ቀጥሉ። ድንጋዩን ከልባችሁ ላይ አስወግዱት! ሞት ወዳለበት ስፍራ እግዚአብሔር ቃል ገብቶ መልስ ይሰጥ ዘንድ ፍቀዱለት”።

ዛሬም ቢሆን ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሱ” በማለት ይናገራል። እግዚአብሔር ለመቃብር አልፈጠረንም፣ እርሱ የፈጠረን ለሕይወ፣ ለውብት እና ለደስታ ነው የፈጠረን። ነገር ግን መጽሐፈ ጥበብ እንደ ሚናገረው “ሞት ወደ ዓለም የገባው በዲያብሎስ ቅናት ነው” (መ. ጥበብ 2፡24) ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከእዚህ ስይፍ ሊያድነን መጣ።

ስለሆነም የሞት ጣዕም ያላቸውን ድንጋዮች ሁሉ እንድናስወገድ ተጠርተናል፣ ለምሳሌ በእምነታችን ውስጥ ያለው ግብዝነት በራሱ ሞት ነው፣ ሌሎችን የሚጎዳ ትችት በራሱ ሞት ነው፣ በደል መፈጸም፣ ስም ማጥፋት ሞት ነው፣ ድሆችን ማግለል ሞት ነው። ጌታ እነዚህን ድንጋዮች ከልባችን እንድናስወግድ ይጠይቀናል፣ ይህንን በምናደርግበት ወቅት ሁሉ ሕይወት አሁንም በዙሪያችን ያብባል።  ክርስቶስ ህያው ነው ፣ እሱን የተቀበለ እና እሱን የሚከተል ሁሉ ከሕይወት ጋር ይገናኛል። ያለ ክርስቶስ ወይም ከክርስቶስ ውጭ በሕይወት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ አንድ ሰው ወደ ሞት የሚወስደውን መንገድ ይከተላል ማለት ነው።

የአልዓዛር ከሞት መነሳት ደግሞ አማኙ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በክርስቶስ የፋሲካ ምስጢር ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት የእድሳት ምልክት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ተግባር እና ኃይል ክርስቲያን እንደ አዲስ ፍጥረት በመሆን በሕይወቱ የሚራመድ ሰው ነው - ለሕይወት የተፈጠረ እና ወደ ሕይወት የሚሄድ ሰው ነው።

ሐዘናችንን ሐዘኑ በማድረግ ርህራሄውን የሰጠንን ልጇን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን ተምሳሌት በመከተል  ርህሩህ እንድንሆን ድንግል ማርያም እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል። በፈተና እና በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እያንዳንዳችን ቅርብ እንድሆን ዘንድ፣ ለእነሱ ሞትን የሚያሸንፍ እና ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ርህራሄ ነፀብራቅ መሆን እንችል ዘንድ እርሷ እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ይኖርብናል።

29 March 2020, 17:17