ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ እግዚአብሔር ነው” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 06/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤን ባለሙያ ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረጋቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረግ ከመጀመራቸው በፊት የሚላን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በመላው ዓለም ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ በሚገኘውና የበርካት ሰዎችን ነፍስ እየቀጠፈ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በግንባር ቀድምትነት በመዋጋት ላይ ለሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ለበሽተኞች እና በሽተኞችን በእዚህ አስቸጋሪ ወቅት በመንከባከብ ላይ ለሚገኙ የበጎ ምግባር ሥራ ተባባሪ ለሆኑ ሰዎች የሚላን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መስዋዕተ ቅዳሴ በማደረግ በእዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከምዕመናን ጎን መቆማቸው መልካም አርዐያ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት የሚላን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሚላን ከተማ እንብርት ላይ የሚገኘውና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በቤተክርስቲያኑ አናት ላይ ተተክሎ በሚገኘው ዱሞ በመባል በሚታወቀው ቤተክርስቲያን አናት ላይ በመውጣት በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታስወግደው ዘንድ የመማጸኛ ጸሎት እኝሁ የሚላን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመማጸኛ ጸሎት አቅርበው እንደ ነበረ አክለው የገለጹት ቅዱስነታቸው የክርስቲያኖች ረዳት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ወረርሽኝ ከዓለማችን ታጠፋልን ዘንድ እኛም የመማጸኛ ጸሎታችንን ለእርሷ ማቅረብ ይኖርብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ይህንን ወቅታዊ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በተመለከተ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ጸሎት ያደርግ ዘንድ ከተማጸኑ በኋላ ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረግ የጀመሩ ሲሆን በወቅቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት06/2012 ዓ.ም ላይ በተጀመረው ሦስተኛ የዐብይ ጽሞ ሳምንት ላይ ትኩረቱን ያደርገ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ከዮሐንስ ወንጌል 4፡5-42 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ ውሃ አጠጪኝ” ብሎ በጠየቃት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ““ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ እግዚአብሔር ነው” ተገልጹዋል። 

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 06/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በእዚህ አሁን በምንገኝበት ሦስተኛው ሳምንት የዐብይ ጾም ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊ ከሆነች ሴት ጋር ስላደረገው ቆይታ ይናገራል (የሐንስ 4፡5-42)። እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየሄደ ሳለ በሰማርያ አከባቢ በሚገኘው አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ሲደርስ እዚያው ትንሽ እረፍት ለማድረግ ቆሙ። ሳምራውያን በአይሁዳዊያን ዘንድ እንደ መናፍቃን ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፣ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆነው ይታዩ ነበር፣ በጣም የተናቁ ሰዎችም ነበሩ። በወቅቱ ኢየሱስ ደክሞት ነበር፣ ውሃም ጠምቶት ነበር። አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ በመጣች ጊዜ እርሱ “ውሃ አጠጪኝ” ብሎ ጠየቃት (የሐንስ 4፡7)። ስለዚህ እርሱ እያንዳንዱን መሰናክል በመስበር ለዚያች ሴት ሕያው የሆነ ውሃ እንደ ሚሰጣት በመግለጽ  የሕይወት ምስጢር ማለትም የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ምስጢር ለሴትዮዋ ይገልጻል። በእውነቱ ለሴቲየዋ አስገራሚ ምላሽ በመስጠት ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት” (የሐንስ 4፡10)

የእዚህ ውይይት ዋና ነጥብ ውሃ ነው። በአንድ በኩል ውሃ በሕይወት ለመኖር መሰረታዊ የሆነ ነገር ሲሆን እሱም የአካልን ጥማት የሚያረካ እና ህይወትን የሚደግፍ ነው። በሌላ በኩል ውሃ የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ መለኮታዊ ጸጋ ምልክት ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በነቢያት እንደተገለፀው ሕያው የሆነ ውሃ ምንጭ እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ባህል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው፣ በተለይም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት እና በነቢያት መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ እግዚአብሄር ነው፣ ከእርሱ ሕያው የሆነ የውሃ ምንጭ ከሆነው እግዚአብሔር እና ከእርሱ ሕግጋት መራቅ እጅግ የከፋ ድርቀትን ያስከትላል ይሉናል። ይህ በምድረ በዳ የእስራኤል ሕዝብ ገጥሞት የነበረው ተሞክሮ ነው። ወደ ነፃነት ጎዳና በሚወስደው ረዥም መንገድ ላይ ውሃ ስለሌለ በሙሴ እና በእግዚአብሄር ላይ ማጉረምረም ጀምረው ነበር። ከዚያም በእግዚአብሔር ትእዛዝ  ሙሴ ከድንጋይ ውስጥ ውሃ እንዲፈልቅ አደረገ፣ ይህም ከህዝቡ ጋር አብሮ በመሆን ህይወትን ለሕዝቡ እንደሚሰጥ እግዚአብሔር የገለጸበት መለኮታዊ ምልክት ነው (ዘፀ 17፡ 17-7)።

ሐዋርያው ​​ጳውሎስም ያንን ዐለት እንደ ክርስቶስ ምልክት አድርጎ ተርጉሟል። በዚህ መንገድ እንዲህ ይላል: - “ዐለቱም ክርስቶስ ነው” (1 ቆሮ 10 4) በማለት ይናገራል። በርግጥ እሱ በሚራመደው በእግዚአብሔር ህዝብ መካከል መገኘቱ ምስጢራዊ አምሳያ ነው (1 ቆሮ 10፡ 4)። በእርግጥ ክርስቶስ በነቢያቱ ራእይ እንደ ተናገረው መንፈስ ቅዱስ የሚፈስበት፣ እርሱም የሚያነፃና ሕይወት የሚሰጥ፣ የሕይወት ውሃ ነው። ለመዳን የተጠሙ ሰዎች በነፃነት ከኢየሱስ ይህንን የሕይወት ውሃ ሊስቡ ይችላሉ፣ እናም መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ወይም በእርሷ ውስጥ ሙሉ እና የዘላለም ሕይወት ምንጭ ይሆናል። ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት የሰጠው የሕይወት ውሃ የፋሲካ በዓል እውነታን የሚያሳየን ሲሆን እርሱ በመስቀል ላይ በነበረበት ወቅት ጎኑን ሲወጉት ከጎኑ “ውሃ እና ደም ወጣ” (ዮሐንስ 19፡34) የሚለውን አጋጣሚ ያስታውሰናል።  ለእኛ ሲሊ የታረደው በግ እና ከሙታን የተነሳው ክርስቶስ ኃጢአትን ይቅር የሚል እና ወደ አዲስ ሕይወት የሚመልስ መንፈስ ቅዱስ የሚፈልቅበት ምንጭ ነው።

ይህ ስጦታ የምስክርነት ምንጭ ነው። እንደ ሳምራዊቷ ሴት በግል ሕይወታቸው ኢየሱስን ያገኘ  ማንኛውም ሰው ስለኢየሱስ ለሌሎች ሰዎች መናገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ኢየሱስ ራሱ ይሰማዋል፣ በዚህም ምክንያት ስማራዊቷ ሴት ለአገሯ ሰዎች እንደ ተናግረችው ሁሉም የአገሩ ሰዎች ኢየሱስ “በእውነት የዓለም አዳኝ” (ዮሐንስ 4፡42) መሆኑን ለሁሉም ሰው እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል።  እኛም በጥምቀት አዲስ ሕይወት ይዘን የተወለድን፣ በእኛ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት እና ተስፋ እንድንመሰክር ተጠርተናል። ፍለጋችን እና ጥማችን በክርስቶስ ሙሉ በሙል እርካታን ካገኘ በመጨረሻም ደህንነት የሚገኘው በእዚህ ዓለም በሚገኙ ቁስ በሆኑ ነገሮች ላይ አለመሆኑን እናሳያለን፣ ነገር ግን በሚወደን እና ሁል ጊዜም በሚወደን እርሱ ማለትም አዳኛችን ኢየሱስ እሱ በሚሰጠን ሕያው ውሃ ውስጥ እርካታ እንደ ሚገኝ እንገነዘባለን።በልባችን ውስጥ የያዝነውን የህይወትን ጥማት እና ፍቅርን ማርካት የሚችል ብቸኛ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆነውን የክርስቶስን ፍላጎት ለማርካት እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
15 March 2020, 11:27