ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ኢየሱስ ከአካላዊ እና መንፈሳዊ እውርነት ነጻ አድርጎን ወደ ብርሃን ያሻግረናል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በመጋቢት 13/2012 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ተለመደው እና ዘወትር እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አለመከናወኑ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት በጣሊያን እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፋት በመስተዋል ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይህ ቫይረስ እንዳይዛመት ሰዎች በተቻላቸው መጠን በአንድ ቦታ መሰብሰብ የለባቸውም የሚለውን የጤን ባለሙያ ምክር ከግምት በማስገባት እርሳቸው በሚኖሩበት የቅድስት ማርታ ቤት ከሚገኘው ቤተ መጸሐፍት ውስጥ በቪዲዮ ሳምንታዊውን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማደረጋቸው ተገልጹዋል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል 9፡ 1-41 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው እንደ ፈወሰው በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ምሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ይተገለጸ ሲሆን “ኢየሱስ ከአካላዊ እና መንፈሳዊ እውርነት ነጻ አድርጎን ወደ ብርሃን ያሻግረናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅታችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱ እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

በዚህ አራተኛው የዐብይ ጾም እለተ ስንበት ስርዓተ አምልኮ ውስጥ ብርሃንን የሚመለከት ጭብጥ እናገኛለን። በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ  (ዮሐ 9፡1 -14) ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ስለአዳነበት ሁኔታ ይናገራል። ይህ ተዓምራዊ ምልክት “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐንስ 9፡5) በማለት ኢየሱስ ጨለማን የሚያበራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ነው። እርሱም በሁለት ደረጃዎች ብርሃናዊ የሆነ ተዐምራቱን ይሠራል፣ እርሱም በአንድ በኩል አካላዊ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መንፈሳዊ የሆነ ተዐምር ይፈጽማል፣  ዐይነ ስውሩ የነበረው ሰው በመጀመሪያ የዐይን ብርሃን ያገኛል፣ ከዚያም በመቀጠል “የሰው ልጅ” (ዮሐንስ 9፡35) በሆነው ማለትም በኢየሱስ ማመን ይጀምራል። ዛሬ ሁላችሁም ይህንን በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ዘጠኝ ውስጥ የተጠቀሰውን ውብ ይሆነ ታሪክ ብታነቡት መልካም ነው፣ አንድ ጊዜ ወይም ደጋግማችሁ ይህንን የቅዱስ ወንጌል ክፍል ማንበብ መልካም ነው። ኢየሱስ ያደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች አስደናቂ ምልክቶች ቢቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ወደ ውስጣዊ ለውጥ የማምጫ መንገድ  ወደ እምነት የመምራት ዓላማ አላቸው።

ፈሪሳውያንና የሕግ መምሕራን በስፍራው የነበሩ ሲሆን ኢየሱስ የፈጸመውን ተዓምር አምነው ለመቀበል አሻፈረን ብለው ይህ ተዓምር የተፈጸመለትን ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ያቀርቡለታል።  እሱ ግን በእውነተኛ ኃይል ተሞልቶ “አንድ ነገር አውቃለሁ፣ ዐይነ ስውር ነበርኩኝ አሁን ግን አያለሁ” በማለት ይመልስላቸዋል። በዙሪያው ባሉት ሰዎች መካከል በሚሰትዋለው ያለ ማመን ስሜት እና ጥላቻ ተሞልተው ጥያቄ ያቅርቡለት ለነበሩ ሰዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ መልስ በመስጠት ዐይኖቹን በከፈተው እና በእርሱ ላይ እምነትን እንዲያሳድር በጠየቀው ኢየሱስን ለማመን የሚያስችለውን የጉዞ መስመር ቀስ በቀስ ይጀምራል። በመጀመሪያ እሱን እንደ ነቢይ ይቆጥረዋል ( ዮሐንስ 9፡17 ይመልከቱ)፣ ከዚያም እሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላከ ይገነዘባል (ዮሐንስ 9፡33)፣ በመጨረሻም እንደ መሲህ አድርጎ ተቀበለው በፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት (ዮሐንስ 9፡36-38)።  ኢየሱስ የማየት ችሎታውን እንዲያገኝ በማደረግ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጽ” (ዮሐንስ 9፡3) እንዳደረገ ተረድቱዋል።

እኛም ይህንን ተሞክሮ ተግባራዊ እናድርግ! ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ሰው አዲሱን ማንነቱን በእምነት ብርሃን አማካይነት ያገኛል። እሱ አሁን በሕይወቱ እና በዙሪያው ያለውን ዓለም በአዲስ ብርሃን ማየት የሚችል “አዲስ ፍጡር” ነው ፣ ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ሕብረት በመፍጠሩ የተነሳ ሕይወቱ ወደ አዲስ አቅጣጫ ያመራል። እሱ ከአሁን በኋላ በማህበረሰቡ የታወቀ ምጽዋዕት ጠያቂ የእኔ ቢጤ አይደለም፣ እሱ ከአሁን በኋላ የዐይነ ስውርነት ጨለማ እና የጭፍን ጥላቻ ባሪያ አይደለም። የእሱ የተጓዘበት እና ብርሃን ያገኝበት ጉዞ እኛ የተጠራነው ከኃጢኣት ሕይወት ነፃ እንድንሆን መሆኑን የሚገልጽ ምሳሌ ነው። ኃጢአት ፊታችንን እንደሚሸፍን፣ እራሳችንን እና ዓለማችንን በግልጽ እንዳናስተውል የሚጋርደን የጨለማ መሸፈኛ ነው፣ የጌታ ይቅር ባይነት ይህንን የጨለማ ግርዶሽ በማስወገድ አዲስ ብርሃን ይሰጠናል። አሁን የምንገኝበት የዐብይ ጾም ወቅት ወደ ጌታ እንድንቀርብ እድሉን የሚፈጥርልን ወድ የሆነ ጊዜ ሊሆን የገባዋል፣ የእርሱን ምሕረት የምንጠይቅበት፣ ቤተክርስቲያን የምትጠይቀንን የተለያዩ ተግባራትን የምንፈጽምበት አመቺ የሆነ ወቅት ሊሆን ይገባዋል።

ከዓይነ ስውርነት ተፈውሶ በሁለቱም ማለትም በአካላዊ እና በመንፈስ ዐይኖቹ ጭምር ማየት የጀመረው ዓይነ ስውር የነበረ ሰው እያንዳንዱን ምስጢረ ጥምቀት የተቀበለ ሰው የሚያመልክት ሲሆን በጸጋ አማካይነት ከጨለማ ወደ ብርሃን እና ወደ እመንት የተመለሰ ሰው መገለጫ ነው።  ነገር ግን ብርሃን መቀበል ብቻ በቂ አይደለም፣ ብርሃን መሆን ያስፈልጋል። እያንዳንዳችን በሕይወታችን በሙሉ እሱን ለማሳየት መለኮታዊውን ብርሃን እንድንቀበል ተጠርተናል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ የነገረ መለኮት ምሁራን የክርስቲያን ማህበረሰብ ማለትም ቤተክርስቲያን “የጨረቃ ምስጢር” ነች ይሉ ነበር፣ ምክንያቱም ብርሃንን የምትሰጥ እንጂ ራሷ ብርሃን ስላልነበረች ነው፣ የምትሰጠውን ብርሃን የተቀበለችው ራሱ በርሃን ከሆነው ከክርስቶስ በመሆኑ የተነሳ ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ እንደሚለን “ቀድሞ በጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና” (ኤፌሶን 5፡8-9) በማለት ይናገራል። በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በውስጣችን የተቀመጠው አዲሱ የሕይወት ዘር ልክ በመጀመሪያ እኛን የሚያነጻን ፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ክፋት የሚያቃጥል ፣ እና እንድንበራ እና ብርሃን እንድንሰጥ የሚያደርገን የእሳት ነበልባል ነው። የህም የሚከናወነው በኢየሱስ ብርሃን።

በክርስቶስ ብርሃን እንድንሞላ እና ከእርሱ ጋር በደህንነት መንገድ ላይ መራመድ እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዛሬው ቅድስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ታሪክ እንድንላበስ በአማላጅነቷ እንድረዳን ልንማጸናት ይገባል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
22 March 2020, 17:13