ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጦርነት ምክንያት የሚሰደዱትን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 22/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ካቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተንትኖ በመቀጠል ከምዕመናን ጋር ሆነው የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በጦርነት ምክንያት የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ የሚገደዱትን ማኅበረሰብ አስታውሰው፣ እነዚህን ስደተኞች በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች፣ ሕጻናት እና እናቶች፣ በጦርነቱ ምክንያት ተበታትነው መገኘታቸውን ፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸውን እና በብዙ አገሮች ውስጥ ጥገኝነትን እና እርዳታን በመለመን ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰዋል። በጦርነት ምክንያት ከአገራቸው እንዲወጡ የሚገደዱ ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህን ቤተሰቦች በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል።

እሑድ የካቲት 15/2012 ዓ. ም. የደቡብ ጣሊያን ከተማ በሆነች ባሪ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ በአንድነት ሆነን በምንጸልይበት፣ ስለ ሰላም በማናስተነትንበት በዚህ ሰዓት፣ ከሜዲቴራንያን  ባሕር ወዲያ የሚገኙ፣ በተለይም በሰሜን ምዕራብ ሶርያ ግዛት በሚገኙ ሕዝቦች ላይ የተነሳው ጦርነት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እያጠፋ እንደሚገኝ ገልጸው በመሆኑም እኛ የሐይማኖት መሪዎች፣ በዚህ አስከፊ ጦርነት የተሳተፉት እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም፣ የሕጻናትን እና የአቅመ ደካሞችን ለቅሶ እና ዋይታን በማዳመጥ፣ የግል ጥቅም ፍለጋን ወደ ጎን አድርገው ፣ የንጹሃን ዘጎች ነፍስ ከሞት አደጋ እንዲያተርፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው ትናንት የካቲት 22/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት የጸሎት ጥሪ፣ በሶርያ ውስጥ በኢድሊብ ከተማ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለ950,000 ሰዎች መፈናቀል ምክንያት በመሆን ፣ ከዚህ በፊት የነበረውን የዓለማችን የስደት ቀውስ ከፍ ማድረጉነስታውቀዋል። በሶርያ ውስጥ፣ በኢድሊብ ግዛት እየተካሄደ ያለ ጦርነት፣ በቱርክ በሚታገዝ የሶርያ አማጺያን እና በሩሲያ በሚታገዝ የሶርያ መንግሥት ጦር ሠራዊት መካከል መሆኑ ታውቋል።

የአውሮጳ ሕብረት አገሮች አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ፣

የቱርክ ፕሬዚደንት የሆኑት ታይፕ ኤርዶጋን፣ ትናንት የካቲት 22/2012 ዓ. ም. በድጋሚ ባቀረቡት የዛቻ ንግግራቸው፣ ድንበራቸውን በሺህዎች ለሚቆጠሩ የሶርያ ስደተኞች ክፍት የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል። አዲስ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ቱርክ እና ግሪክ በሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ መጨመሩ ሲታወቅ፣ የግሪክ መንግሥትም ካለፈው ቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ወደ ክልሉ ለመግባት ጥረት ለሚያደርጉ ወደ 10,000 ለሚጠጉ የሶርያ ስደተኞች ድንበሩን መዝጋቱ ታውቋል። በአውሮፓ ሕብረት አገሮች የስደተኞች ጉዳይ ተጠሪ የሆኑት አቶ ማርጋሪቲስ ሺናስ፣ ለአውሮፓ ሕብረት ፕሬዚደንት አንድሬይ ፕለንኮቪች በላኩት መልዕክት፣ በቱርክ ድንበር አካባቢ በተነሳው ቀውስ ላይ የሚወያይ የአውሮፓ አገሮች የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ እንዲያድረጉ አሳስበዋል።

የባሪ ጉባኤ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፣ የካቲት 15/2012 ዓ. ም. በደቡብ ጣሊያን ከተማ በሆነችው ባሪ በመገኘት “ሰላም የሰፈነበት ሜድትራንያን” በሚል መሪ ቃል በማስተንተን ስብሰባቸውን ላካሄዱት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ባስተላለፉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እንደገለጹት ፣ በሜዲተራኒያ አካባቢ አገሮች ውስጥ በሚታይ የመከፋፈል እና የልዩነት አዝማሚያ ክርስቲያኖች የማይሰለቹ የሰላም መልዕክተኞች እንዲሆኑ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የሜዲቴራንያን ባሕር በሚያዋስኑ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እና ሰሜን አፍሪቃ አገሮች ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት እንዲሁም በተለያዩ ጎሳዎች እና የሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚነሱ ግጭቶችንም አስታውሰው በአካባቢው አገሮች የሚገኝ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ሰላምን እና እርቅን ለማውረድ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
02 March 2020, 16:20