ፈልግ

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመገባደድ ላይ ባለው ሳምንት ውስጥ የተገበሩት ሐዋርያዊ ክንውን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመገባደድ ላይ ባለው ሳምንት ውስጥ የተገበሩት ሐዋርያዊ ክንውን 

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመገባደድ ላይ ባለው ሳምንት ውስጥ የተገበሩት ሐዋርያዊ ክንውን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሳምንታዊውን ሐዋርያዊ ክንውን የጀመሩት ባልፈው እሁድ የካቲት 08/2012 ዓ.ም ሲሆን ቅዱስነታቸው በእለቱ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በእለቱ ከማቴዎስ ወንጌል (5፡17-37) ተወስዶ በተነበበው ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ በሰበከው ስብከት ላይ መሰረቱን ባደርገው አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው ባደረጉት አስተንትኖ “የእግዚኣብሔር ሕግ ከኃጢአት ባርነት ነጻ ሆነን እንድንኖር የሚረዳን መሳሪያ ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“ኢየሱስ በተራራ ላይ ካደርገው ስብከት” የተወሰደ እና ሕግ ሁሉ ፍጻሜን እንደ ሚያገኝ የሚገልጽ ነው፣ እኔ ሕግን በሕይወቴ እንዴት ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለብኝ የሚገልጽ ነው። በሕጉ አማካይነት እውነተኛ ነፃነት እና ኃላፊነቶችን መቀበል እንዳለብን እግዚአብሔርም በእነርሱ ውስጥ እንደሚገኝ በመናገር ለሙሴ የተሰጡት ትእዛዛት ትክክለኛ መንገድ እንዲያገኙ ኢየሱስ አድማጮቹን ሊረዳቸው ይፈልጋል። እሱ እንደ አንድ የነፃነት መሳሪያ ሆኖ መኖር ነው። ይህንን መርሳት የለብንም - ህጉን እንደ ነጻነት መሳሪያ አድርጎ መኖር፣ ነፃ እንድንሆን የሚረዳን፣ ለስሜቶች እና ለኃጢያት ባሪያ ላለመሆን የሚረዳን ሕግ ነው። ስለ ጦርነቶች እናስባለን፣ ጦርነቶች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች እናስባለን፣ በእርስ በእርስ ጦርነት በፈራረሰቺው በሶሪያ በቅዝቃዜ ምክንያት በቅርቡ የሞተችውን ሕጻን ልጅ እናስባለን። እጅግ ብዙ መከራዎች እጅግ ብዙ መከራ። ይህ የፍላጎቶች እና የስሜት ውጤት ነው እናም ጦርነት የሚያደርጉ ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን መቆጣጠር አይችሉም። በእዚህ ረገድ የእግዚኣብሔር ሕግ ሳይፈጽም ቀርቷል። ለፈተናዎች እና ምኞቶች ስንሸነፍ የሕይወታችን ጌታ እና ዋና ገጸ-ባሕሪ መሆናችን ይቀራል፣  ነገሮችን በፍቃዳችን እና በኃላፊነት ለማስተዳደር አንችልም።

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ በቀጠሉበት ወቅት ጨምረው እንደ ገለጹት “ዛሬ ኢየሱስ ባሳየን እና ከልባችን በሚጀምረው የፍቅር መንገድ ላይ እንድጓዝ ኢየሱስ ይጠይቀናል። እንደ ክርስቲያን ለመኖር ከፈለግን መንገዱ ይህ ነው። እውነተኛ ደስታ ለማግኘት እና ፍትህና ሰላምን በሁሉም ቦታ ለማሰራጨት ልጇ የተጓዘበትን መንገድ መከተል እንችል ዘንድ እመቤታችን ድንግል ማርያም እንድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተንትኖ አጠናቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየካቲት 10/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ለልበ ደንዳናነት ፍቱን መድኃኒቱ የእግዚአብሔርን ጸጋ ማስታወስ ነው ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን በዕለቱ ከማርቆስ ወንጌል 8:14-21 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ በተናግረው ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ መጸገባችን የሚታወስ ሲሆን በዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው  ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በደነደነው የሰዎች ልብ እና በርህራሄ በተሞላው በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ መካከል ያለውን ልዩነት ያስረዱት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ርህራሄውን መግለጽ እንደሆነ ገልጸው፣ እግዚአብሔርም “እኔ የምፈልገው ምህረትን እንጂ መስዋእትን አይደለም” ማለቱንም አስታውሰዋል። በርህራሄ ያልተሞላ ልብ በራስ ወዳድነት እና በዓለማዊ ሃሳቦች የተሞላ ነው” ብለዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን የነበሩ አራት ዓለማዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖችን ያስታወሱ ቅዱስነታቸው፣ እነርሱም ፈሪሳውያን ፣ ሰዱቃውያን ፣ ኤሳውያን እና ቀናተኞች እንደነበሩ ገልጸው እነዚህም ልባቸው የደነደነ፣ የራሳቸውን የግለኝነት አስተሳሰብ እና ዓላማ ከማራመድ በቀር ለእግዚአብሔር የርህራሄ መንገድ ምንም ቦታ ያልነበራቸው መሆኑን አስረድተዋል።

“ከልበ ደንዳናነት የሚፈወስ ፍቱን የሆነ መድኃኒት አለ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች እንደተገለጸው ከእግዚአብሔር የሚሰጥ የጸጋ ሙላት ልብን ታማኝ እና ለርህራሄ ክፍት አድርጎ በማቆየት ከደንዳናነት ይፈውሳል” ብለዋል። “ልብ ሲደነድን የእግዚአብሔርን የደህንነት ጸጋ ማስታወስ ያቅተዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው የደነደነ ልብ በውስጡ ርህራሄ በመጥፋቱ በምትኩ ጠብን፣ ጦርነትን፣ ስግብግብነትን እና በወንድም ላይ መነሳትን ስለሚጋብዝ ርህራሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ይከብደዋል” ብለዋል። ከመልዕክት ሁሉ ታላቅ፣ እግዚአብሔር ለልጆቹ ያሳየው ርህራሄ መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በቅዱስ ወንጌልም እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ስቃይ እና መከራ ሲመለከት የሚያሳየው የመጀመሪያ እርዳታ ርህራሄ መሆኑን ገልጸው፣ ኢየሱስ የአባቱ ርህራሄ መገለጫ እና ለደነደነ ልብም ፍቱን መድኃኒት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት  በየካቲት 12/2012 ዓ.ም ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት ክርስቲያን መሆን ማለት  እኛን ለማዳን ኢየሱስ የተጓዘበትን መንገድ መከተል ማለት ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ማነኛውም ክርስቲያን ምዕመን፣ ጳጳስ፣ ካህን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሳይቀር ይህንን ኢየሱስ የተጓዘበትን መንገድ የማይከተሉ ከሆነ መንገድ ስተዋል ማለት ይቻላል ምክንያቱም ክርስቲያን መሆን ማለት እስከ መስቀል ድረስ የኢየሱስን መንገድ መቀበል እና መከተል ማለት ስለሆነ ነው ብለዋል።

“ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?”፣ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” እነዚህ ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማርቆስ 8፡27-9፡1) የሚገኙት ጥያቄዎች ናቸው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በወቅቱ እርሳቸው ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ያጠነጠነው በእነዚህ ሁለት ኢየሱስ ባቀረባቸው ጥያቄዎች ላይ መስረቱን ያደርገ እንደ ነበረም ተገልጹዋል። ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ ሐዋርያቱ በሚገባ ይገነዘቡ ዘንድ ሦስት ደረጃዎችን ይጠቁማል፣ እነዚህም እግዚኣብሔርን ማወቅ፣ እርሱን መመስከር እና እግዚኣብሔር ለኢየሱስ የመረጠውን መንገድ መቀበል የሚሉት እንደ ሆኑ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ኢየሱስን መመስከር ማለት የእርሱን ሞቱን፣ የእሱን ትንሣኤ፣ መመስከር ማለት ነው እንጂ እንዲያው ለይስሙላ “አንተ እግዚአብሔር ነህ” ማለት በራሱ በቂ አይደለም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “አንተ ወደ እዚህ ምድር ለእኛ ስትል መጥተኃል፣ ለእኔ ሞተኃል። ከሙታን ተነስተኃል፣ ሕይወት ተሰጥቶናል፣ በሕይወት ጉዞ የመራን ዘንድ መንፈስ ቅዱስህን እንደ ምትልክልን ቃል ገብተሃል፣ በማለት ልናምን እና ልንመሰክር እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ኢየሱስን መመስከር ማለት አብ ለኢየሱስ የመረጠውን የውርደት መንገድ መቀበል ማለት ነው ብለዋል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ "እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” ብሎ እንደ ገለጸው እኛም ይህንን የኢየሱስን መንገድ እና ለቤዛነት የመረጠውን የውርደት መንገድ ካልተቀበልን እኛ በሙሉ ልባችን ክርስቲያኖች ነን ብለን ለመናገር አንችልም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በካቲት 11/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 5 ውስጥ በተጠቀሰው የኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከት ላይ መሰረት ያደረገ እንደ ነበረ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን “የዋህነት አንድ ሲያደርገን ቁጣ ግን እንድንለያይ ያደርገናል” ማለታቸው ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው አስተምህሮዋቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “የዋህ” የሚለው ቃል፣ እንዲሁ ቃል በቃል ሲተረጎም፣ ሰውን የማያስቀይም፣ ጨዋ ፣ ከግጭት ነፃ የሆነ የሚለው ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። የዋህነት ጎልቶ የሚታየው፣ በሰዎች መካከል ግጭት ወይም ቅራኔ ሲፈጠር እና ይህን ግጭት ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ነው። በሰዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ማንም የዋህ ሆኖ ሊቀርብ ወይም ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የዋህነቱ የሚረጋገጠው የተፈጠረውን ግጭት ለማስወገድ ወይም ለማብረድ በሚከተለው የመፍትሄ መንገድ ነው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ጨምረው ሲገልጹ “የግጭቱ ሰለባ በሚሆንበት ጊዜ ወይም ጥቃት ቢሰነዘርበት የሚያሳየው ስሜት የቁጣ እና የአጸፋ ነው የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል።ሐው. ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱ በምዕ. 10. 1 ላይ “እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ” በማለት ይናገራል። ሐዋርያው ጴጥሮስም በመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 2.23 ላይ የኢየሱስ ክርስቶስን የስቃይ እና የሕማማት ወቅት ስሜት ሲናገር “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” በማለት እንደ ሚገልጽ ተናግረዋል። በማቴ. 5. 5 ላይ “የዋሆች” ምድራዊ ሀብትም የሌላቸው፣ ነገር ግን በየዋህነታቸው “ምድርን ይወርሳሉ” ስለሚል እውነቱን እንድናውቅ ያደርገናል።በእርግጥ በዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የተራራ ላይ ስብከት የተጠቀሰውን የዋህነት፣ ዛሬ በተነበበው እና የመጀመሪያ ንባብ በሆነው በመዝሙረ ዳዊት ምዕ. 37. 3 ላይ “በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ” በማለት ገልጾታል። በዚህ ጥቅስም ቢሆን፣ የዋሆች ምድርን እንደሚወርሷት ይናገራል። እነዚህን ሁለት የሚቃረኑ ነገሮች በማስተዋል መመልከት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ዛሬ በምድራች በድንበር ይገባኛል በሚል ሰበብ አመጾች እና ጦርነቶች ሲቀሰቀሱ እንመለከታለን። በአንዳንድ አካባቢዎች የበላይነትን ለማግኘት ተብሎ ሕዝቦችም ሆኑ መንግሥታት ሲጣሉ፣ የሰው ሕይወት በከንቱ ሲጠፋ እናያለን። እንደሚታወቀው በጦርነቶች መካከል ጠንካራ ሆኖ የተገኘው ድል ያደርግና ሌሎች አገሮችን ወይም አካባቢዎችን መቆጣጠር ይጀምራል።ነገር ግን በቅዱስ ወንጌል ላይ “የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ” በሚለው ዓረፍተ ነገር “ይወርሳሉ” የሚለውን ቃል በሚገባ በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል። በዚህ ጥቅስ ላይ “የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ” ይላል እንጂ ምድርን ይቆጣጠራሉ ወይም ምድርን ይገዟታል የሚል ሃሳብ ወይም ትርጉም አናገኝም። ከዚህም በተጨማሪ በሌላ የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል፣ በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕ. 11.23 እና 13.7 ላይ ስለ ምድር ውርስ እንዲህ ብሎ የተናገረውን እናገኛለን፥ “ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን በሙሉ ያዘ፤ እንደ ነገዳቸው አከፋፈል በመመደብም ርስት አድርጎ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው። ይህንንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል” በማለት እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ያዘጋጀላቸውን የተስፋ ምድር መሆኑን እንመለከታለን” ማለታቸው ተገልጹዋል።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸሶስ ሳምንታዊውን የጠቅላላ አስተምህሮ በቀጠሉበት ወቅት እንደ ግለጹት “ስለዚህ የየዋህ ሰው የምድር ወራሽነት በእጅግ አስደናቂ መንገድ የሚደረግ እንጂ ከችግር ለመላቀቅ ተብሎ በሕገ ወጥ በመጥፎ ሥነ ምግባር የሚያገኘው አይደለም። ማንም ሰው በውርስ ያገኘውን መሬት በከንቱ ሊያጠፋ፣ ሊያጣ ወይም ሊቀማ አይፈልግም። የዋህ ሰው በግል ውርሱ ተደላድሎ ወይም ተስማምቶት የሚቀመጥ አይደለም ፣ ነገር ግን ሌላውንም ምድር ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ የተጠራ ወይም የተዘጋጀ የኢየሱስ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ነው። እርሱ የራሱን ሰላም የሚያስከብር ነው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያከብር፣ ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ስጦታዎች፣ የእግዚአብሔርን የምሕረት ስጦታ፣ ከእርሱ ጋር ያለውን ወዳጅነት፣ ታማኝነት እና ተስፋ በሚገባ የሚጠብቅ ነው።በዚህ አጋጣሚ ስለ ቁጣ እና ቁጣ ስለሚያስከትለው ኃጢያት መጥቀስ ይኖርብናል። ቁጣ ሁላችንም የምናውቀው የግፍ እንቅስቃሴ ነው። በቁጣ የተነሳ ስንት ነገር አውድመናል? በቁጣ የተነሳ ስንት ነገር አጥተናል? ቁጣ በቅጽበት ብዙ ነገሮችን እንድናጣ ያደርጋል ፤ ለሕይወታችን እንኳ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ነገሮች መኖራቸውን እንዳንረዳ ያደርጋል። ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል፣ የመፍትሄ እና የእርቅ መንገዶችን እንዳንፈልግ ያደርገናል።የዋህነት ግን ብዙ ነገሮችን እንድናሸንፍ ያግዘናል። የዋህነት ልብን ያሸንፋል፣ ወዳጅነትን ይጠብቃል። የዋህ ሰው ምንም እንኳ ቢቆጣ እና ቢናደድ ወደልቡ በመመለስ፣ ብዙ ነገሮችን በማገናዘብ ወደ ቀድሞ ማንነቱ ሊመለስ ይችላል። የተበላሸ ነገር ቢኖርም ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል።መውረስ ያለብን ምድር፣ በማቴ. ወንጌል ላይ እንደተገለጸው፣ ከወንድም ጋር ያለውን ወዳጅነት መጠበቅ ነው። “ወንድምህ ቢበድልህ  ሄደህ አንተና እርሱ ብቻ ሆናችሁ ጥፋቱን ንገረው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን እንደ ገና የራስህ ታደርገዋለህ (ማቴ. 18.15)። ልብን ለሌሎች ከማድርግ የበለጠ መልካም ምድር የለም፤ ከወንድምህ ጋር ከምትመሠርተው መልካም ወዳጅነት የበለጠ ምድር የለም። መውረስ ያለብን ምድርም ይህ ነው” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያዘግጁትን አስተምህሮ አጠናቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 12/2012 ዓ. ም. ለካቶሊካዊ ትምህርት ማስፋፍፊያ ምክር ቤት አባላት ባሰሙት ንግግር፣ ምክር ቤቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ላከናወኗቸው ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በቀጣይነትም የሚያከናውኗቸው ተግባራት የዓለማችን ሁኔታ በማገናዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድጉ እና ለውጦችም የሚታዩባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት ሰዎችን ወደ ብርሃን የሚመራ ዘላቂ እንቅስቃሴ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም የሰውን ልጅ ወደ ተሟላ ግላዊል እና ማኅበራዊ እድገት እንዲደርስ የሚያደርግ ልዩ እንቅስቃሴው ነው ብለዋል። ከትምህርት ባሕርያት መካከል አንዱ ሥነ-ምህዳራዊ እንቅስቃሴው ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ባሕሪው የሰውን ልጅ ማዕከላዊነት በመጠበቅ ማሕበራዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እድገቶችን በማምጣት ራሱን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በሚገባ በማወቅ፣ በማኅበረሰቦች መካከል የእርስ በእርስ ወንድማማችነትን እና ለጋራ እድገት ድልድይ የሚሆኑ የባሕሎች ብዝሃነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የትምህርት መስፋፋት በተለያዩ የሥነ-ምህዳር የእድገት ደረጃው፣ ከሁሉ አስቀድሞ የሰው ልጅ ከራሱ ጋር፣ ከሌላው  ጋር በመተባበር ፣ በሕይወት ካሉ ፍጡራን ሁሉ ጋር፣ ከእግዚአብሔርም ጋር መንፈሳዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። ይህን የትምህርት ሂደት ተግባራዊ ለማድረግ በበቂ ዕውቀት የታገዙ፣ ስነ-ምግባራዊ መንገዶችን በመከተል በርህራሄ ላይ የተመሠረተ አንድነትን ፣ ሀላፊነትን እና እንክብካቤን ማሳደግ የሚችሉ መምህራን ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ትምህርት የእድገት መንገድ እንደመሆኑ፣ ሁሉን ሊያሳትፍ ይገባል ያሉት ርዕሠሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በድህነት፣ በጦርነት እና በመጽ ፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በማኅበራዊ የኑሮ አለመመጣጠን እና በቤተሰባዊ ችግሮች የደረሰባቸውንም የሚያሳትፍ መሆን አለበት ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት የሚገኝ እድገት፣ የጾታ፣ የዘር እና የሐይማኖት ልዩነት ሳያደርግ፣ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የማሕበረሰብ ክፍሎች፣ ከእነዚህም መካከል በሕገው አጥ የሰዎች ዝውውር ውንጀል ሰለባ የሆኑትን፣ ስደት ላይ የሚገኙትንም የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ይህ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የማካተት ተግባር ዘመናዊ ፈጠራ ሳይሆን የክርስቲያናዊ ድነት መልእክት አካል ነው ብለው፣ በትምህርት የሚገኝ የማሕበረሰብ እድገትን ማፋጠን ያስፈለገበት ምክንያት በማኅበረሰብ መካከል ወንድማዊ ፍቅርን በማሳደግ የማግለል ባሕልን ለማስቀረት ነው ብለዋል።

የትምህርት እንቅስቃሴ ሌላው ባሕርይ በዓለማችን ውስጥ ሰላምን ማምጣት ነው በማለት፣ እንደ ጎርግሮሳዊያኑ አቆጣጠር ጥር 9/2020 ዓ. ም. በቅድስት መንበር በኩል የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ያስተላለፉትን መልዕክት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ተስፋ በምኞት ብቻ የሚቀር አለ መሆኑን እና በርትተው ከሠሩ ሰላምም ሊገኝ የሚችል መሆኑን ወጣቶች ራሳቸው መናገራቸውን አስታውሰዋል። ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉ ትምህርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ በሕዝቦች መካከል፣ በትውልዶች መካከል፣ በባሕሎች መካከል፣ በሃፍታም እና ደሃ መካከል፣ በወንዶች እና ሴቶች መካከል፣ በምጣኔ ሃብት እና በግብረ ገብ መካከል፣ በሰው እና በአካባቢ መካከል የሚከሰቱ ልዩነቶችን ለማስወገድ  ያግዛል ብለዋል። በእነዚህ ወገኖች መካከል የሚታዩ ክፍተቶች በውስጣቸው ያለው ፍርሃት እንዳይታይ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። በዚህም መሠረት ትምህርት፣ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን፣ በመካከላቸው አንድነት እንዳይኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶችን እና በልዩነት መካከል ያለውን ውበት ሃብት ተገንዝበው ሰላምን ለመፍጠር የሚችሉ  ወገኖችን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ሌላው የትምህርት ዓይነተኛ መገለጫ የቡድን እንቅስቃሴ መሆኑ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትምህርት በአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን አስረድተው፣ የትምህርት ማስፋፊያ ምክር ቤት መግለጫ እንደሚያሳስበው፣ ትምህርት ቤት፣ እንደ እውቀት ማዕከል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ እነርሱም ወላጅ ቤተሰብ፣ መምህራን፣ የባሕል፣ የሕዝብ እና የሐይማኖት እድገት ማህበራት እና መላው የሰው ልጅ የሚሳተፍበት መሆን አለበት ብለዋል። ዘንድሮ የምስረታውን 30ኛ ዓመት የሚያስታውስ የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ህገ-መንግስት በበኩሉ፣ ከፍተኛ ካቶሊካዊ ተቋማት ወይም ዩኒቨርሲቲዎች በቆመለት ዓላማ በመመራት፣ ቀዳሚ ተልዕኮው በመንፈስ ቅዱስ የሚታገዝ እውነተኛ ሰብዓዊ ማኅበረሰብን ማዘጋጀት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ከምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ተውጣተው ለጥናት እና ለጉብኝት ወደ ሮም ከተማ የመጡ ወጣት ካህናት እና መነኩሳት ጋር በየካቲት 13/2012 ዓ.ም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በቫቲካን መገናኘታቸው ተገልጹዋል። በግንኙነቱ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ባደረጉት ንግግር እንደ ግለጹት “ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ለደስታ እና ለጋራ ጥቅም የሚሆናቸው የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይዘዋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (2ቆሮ 1፡2)። እነዚህን የሐዋሪያው ጳውሎስ ቃላት ተጠቅሜ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሞቅ ያለ ሰላምታዬን እያቀረብኩኝ የእናተ ጉብኝት ያሳደረብኝን ደስታ ከእናተ ጋር ለመካፈል እወዳለሁ። ከእናተ ጋር ሁነው እዚህ የተገኙትን ሊቀ ጳጳስ በርሳማኒ እና ጳጳስ ኤል-ሶሪያን ከልብ በመነጨ መልኩ ለእነርሱም ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በአናንተ በኩል ለተከበሩ እና ውድ ወንድሞቼ ለሆኑት የምስራቃዊ ኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት ሃላፊዎች ልዩ ሰላምታዬ እንዲደርሳቸው እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲቀጥሉ “እያንዳንዱ ጉብኝት ያሉንን ስጦታዎቻችንን እንድንጋራ ያደርጋል። የእግዚአብሔር እናት ኤልሳቤጥን ጎበኘቻት፣ የተቀበለችሁን እግዚአብሔርን ስጦታ ለእርሷም አጋራቻት። ማርያም ሰላምታ ባቀረበችላት ወቅት በማህፀኗ ውስጥ ያለው ጽንስ በደስታ ዘለለ፣ እርሷም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተሞልታ የአጎቷን ልጅ ባረከች (ሉቃ 1 39-42)። እንደ ማርያምና ኤልሳቤጥ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ለደስታ እና ለጋራ ጥቅም የሚሆናቸው የተለያዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይዘዋል። እኛ ክርስቲያኖች እርስ በራሳችን ስንጠያየቅ እና በጌታ ፍቅር አንዳችን ሌላውን ስንገናኝ እነዚህን ስጦታዎች መለዋወጥ በመቻላችን ተባርከናል። መንፈስ ቅዱስ በሌሎች ውስጥ የዘራውን እንደራሳችን ስጦታ አድርገን መቀበል እንችላለን። ስለዚህ የእናተ ጉብኝት ስለካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ያላችሁን እውቀት ለማሳደግ እድል የሚሰጣችሁ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እኛም ካቶሊኮች እናንተ የምታመጡልንን የመንፈስን ቅዱስ ስጦታ የማግኘት ዕድል ይሰጠናል። እዚህ መገኘታችሁ ይህንን ስጦታ እንድንጋራ እድሉን ይሰጠናል እናም የደስታ ምንጭ ይሆናል” ማለታቸውን መግለጻችን ይታወሳል።

22 February 2020, 12:44